የእንጦጦ ተራራ ጫካና የእንጨት ተሸካሚዋ ምስጢር

ገና በአፍላ እድሜዋ እንጨት ለቅሞ እና ሸጦ የማደርን ስራ የተለማመደችው ልጅ እንጨት ለቀማ የእድሜ ልክ ስራዋ ሊሆን እንደሚችል አላሰበችም ነበር። አንድ ቀን የተሻለ ነገር ይመጣል በሚለል ማልዳ ከቤቷ ወጥታ እንጨት ለቅማ ሸጣ ቤት መግባት የምታውቀው ብቸኛ ስራዋ ነው።

በመዲናችን የወይዘሮዋን ሥራ የሚጋሩ፣ በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ቀሪ ሕይወታቸውን የሚገፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች አሉ። ሴቶቹ ቀን ከሌት ይለፋሉ፣ ይጥራሉ፤ በየቋጥኙ ለእንጨት ለቀማ ጎንበስ ቀና ይላሉ። በአማካይ በአንዴ አርባ ኪሎ ግራም የሚመዝን የማገዶ እንጨት ተሸክመውም አቀበት ይወጣሉ፤ ቁልቁለት ይወርዳሉ።

የእንጨት ተሸካሚ ሴቶች ሕይወት ጣጣው ብዙ ነው። ድካም ልፋቱም እንደዚያው፡፡ ከዚህ ባሻገር ለሰው ሰራሽ ችግሮች ተጋላጭነታቸውም የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። ምን ይህ ብቻ የእንጦጦን ጫካ ለሴቶቹ የእለተ ጉርስ ማገኛ ቢሆንም በዛው ለክ ክብራቸወን የሚነካ ማንነታቸውን የሚዳፈረ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርሰው አካላዊና ሞራላዊ ጉዳቱ የቱን ያህል ዘግናኝ ቢሆንም ጫካው ገብተው እስኪወጡ ድረስ ወይ ገንዘብ ወይም ሴትነታቸው የሚጠይቁ የጫካው ውስጥ ጎሮምሶችና ደን ጠባቂዎች ከስራቸው ክብደት በላይ የየእለት ራስ መታት ሆነውባቸዋል።

የኑሮ ውጣ ውረዱ የዚህን ያህል አስቸጋሪ ነው። ሊቋቋሟቸው የሚከብዱ ችግሮችን መጋፈጡ፤ ለተለያዩ ማህበራዊ ጥቃቶች መጋለጡ ሴቶቹ የሚጠብቋቸው እለታዊ ክስተቶች ናቸው።

በዚህ ዓይነቱ በማያወላዳ የኑሮ ዑደት ውስጥ ሕይወታቸውን እየመሩ ያሉ በርካቶች አሉ። የማገዶ እንጨት ለቅመው፣ ተሸክመውና ሸጠው ቤተሰብ ከማስተዳደር አልፈው ልጆቻቸውን ኮሌጅ ድረስ አስገብተው በማስተማር ለወግ ማዕረግ ያበቁም እንዲሁ። ከዚህ አድካሚ ሥራ ተላቀው በሌላ የተሻለ ሙያ ዘርፍ በመሰማራት በኑሮአቸው ለውጥ ማየትን የጀመሩ ጥቂት የማይባሉም አሉ።

ለዛሬ የሴቶች አምድ ባለታሪክ አድርገን ያቀረብናቸው ሴትን ያገኘናቸው ጉለሌ እንጀራ ማዕከል ውስጥ ነበር። ትናንት የገፉትን የመከራ ዳገት የኋሊት ትተው ነገን ተሰፋ የሚያደረጉት ወይዘሮ ታሪካቸውን አውግተውናል። መልካም ቆይታ።

ወይዘሮ አባይነሽ አበበ ይባላሉ። ከተወለዱባት ጎሃ ፅዮን ወደ አዲስ አበባ የመጡት ገና በህፃንነት እድሜያቸው ነበር። የእናታቸውን እግር ተከትለው አዲስ አበባን የረገጡት እኚህ ሴት እድሜያቸው ወደ ስልሳዎቹ መባቻ ላይ እንደሚገኝ ይገመታል። እኚህ ሴት ሰባት ልጆች ያሏቸው ሲሆን ነፍስ ካወቁ ጊዜ ጀምሮ የሚያውቁትን እንጨት ለቅሞ መሸጥ ስራን የልጆቻቸው ማሳደጊያ ዋና መተዳደሪያቸው አደርገውት ነበር የኖሩት። ኑሮን ለመግፋት ሲሉ ከአውሬ ጋር እየታገሉ እንጨት ለቅመው በመሸጥ ሕይወትን በእንጦጦ ተራራ ላይ እየገፉ የኖሩት እኝህንና ሌሎች እናቶችን ዛሬ በጉለሌ እንጀራ ማዕከል ውስጥ ተደላድለው እየኖሩ ቢሆንም የኋላ ታሪካቸው ግን በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡

ወደ ጉለሌ እንጀራ ማዕከል ከመምጣታቸው በፊት እኩለ ሌሊት ካለፈ እንቅልፍ ተኝተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። ከዘጠኝ ሰአት ጀምረው ተጠራርተው አቀበቱን ወጥተው፤ ቁልቁለቱን ወርደው ቅጠል ጠርገው፤ ጭራሮ ለቅመው ፤ ከእንጨት ቆራጮች የሚተራርፉ የእንጨት ጉራጆችን ለቅመው የገበያው ሰአት ሳያልፍ ተሸክመው ይሮጣሉ። ይህን ተግባር ደግመው ደጋግመው ተመላልሰውበታል። ከልምዳቸው የተነሳ አድካሚው ጋራን በፍጥነት ሲያልፉ ድካም አይታይባቸውም።

ወይዘሮ አባይነሽን የመሰሉ እንስቶች በውድቅት ጨለማ ከጅብና ከወሮበላ ጋር በመተናነቅ ቤተሰባቸው ሰብሳቢ አጥቶ እንዳይበተን ጥረዋል ደክመዋል። የሌላ እጅ ጠባቂ ላለመሆን ላባቸው በጀርባቸው እየተንቆረቆረ ለዚያውም በሸክም ጭምር ክንድ እና እግሮቻቸው እየዛሉ በየጥሻው ባዝነዋል። ያገኟትንም አሳስረው ወጥተው ወርደዋል፤ከመኖሪያ ቀያቸው እንጦጦ፤ ከእንጦጦም ያሰባሰቡትን ይዘው ገዥ አግኝተው እስኪቀናቸው በመሐል ከተማ ሳይቀር ተዛዙረዋል።

ሕይወት ፈተና ብትሆንባቸውም ከእንጦጦ ተሻርከው፤ ብርታትንና ጥንካሬን ተላብሰው በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በየእለቱ እስከ አርባ ኪሎ ሜትር በእግር ጉዞ መመላለሱ የኑሮ እጣ ፋንታ ሆኖባቸዋል። እንጦጦ የየእለት ፈተና ቢሆንባቸውም የእለተ ጉርስ ግን እንካቸሁ ይላቸዋል።

በሽሮ ሜዳ ወፍ ገና አልተንጫጫም፤ ሌሊቱም ቢሆን ለንጋት ሥፍራውን ለመልቀቅ አልተሰናዳም። የቤተሰቡ የእለት ጉርስ የማሰናጃ ወቅት ነውና ወይዘሮ አባይነሽ መኖሪያ ቤታቸው በጢስ ተሟሙቃለች። ከሙቀቱ ውስጥ ወጥቶ መሄድ ባያስመኝም ከእንጦጦ ጋር የያዙት ቀጠሮ እንዳይረፍድ መሮጥ ግድ ሆኖባቸዋል።

የቤት ውስጥ ጣጣውም የወደቀው በወይዘሮዋ ትከሻ ላይ ነው። ቀን ላይ የሚቋደሷትን ስንቅ ቆጣጥረው፣ የሚጠጧትን ውሃ ሸክፈው ፣ የሥራ ትጥቃቸውንም አሰማምረው ሌሊት አሥር ሰዓት ከመሆኑ በፊት ለአድካሚው ስራ መንደራቸውን የኋሊት ትተው ጉዟቸውን ወደ እንጦጦ ጫካ ያደርጋሉ።

ገና በማለዳው የእድሜ መነሻ እናታቸውን ተከትለው ጫካ የወጡት ወይዘሮ እናታቸው እንጨት ለመሰበር ዞር ከማለታቸው ነበር የደፋሪዎች ሰለባ የሆኑት። ገና በአስራ አምስት አመት እድሜያቸው ተደፈሩ፡፡ አባቱን የማያውቁት ህፃን በማህፀናቸው ተሸክመው ለመዝለቅ ተገደዱ፡፡በዚህ ላይ ማህበረሰቡ የሚያደርስባቸው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡

ዲቃላ ወለደች ከሚለው ከመንደርተኛው አፍ አንስቶ የጓደኞቻቸው መጠቋቆሚያ እስኪሆኑ ድረስ በሚያሸማቅቅ ሁኔታ ውስጥ ያለፉት ወይዘሮ፤ ልጃቸው ከማንም ልጅ እንዳያንስ ቀድመው የጀመሩትን ስራ እየሰሩ ለብቻቸው ልጃቸውን በቆራጥነት ማሳደግ ጀመሩ።

ማልደው ከአውሬ ጋር እየተጋፉ ተራራውን መወጣቱ፤ በየመንገዱ ቆመው የሚጠብቋቸው የጫካውን ካቦዎች በገንዘብ ማለፉ፤ ሰው ተተናኮለኝ አልተተናኮለኝ የሚለውን ሰቆቃን መሻገሩ እንዳለ ሆኖ እንጨት የሚሸጡበት አራት ኪሎ ቤተመንግስት አካባቢ ፊት በር እየተባለ የሚጠራው ሰፈር አራት ሰአት ሳይሞላ ለመድረስ የነበረውን ሩጫ ያስታውሳሉ።

̋አራት ሰአት ከሞላ ቦታው ላይ የጉሊት ንግድ ይሰራ ስለነበር እነሱ መጥተው ሳያባረሩን መቅደም ነበረብን፤ ካልቀደምን ግን እንጨቱ ሳይሸጥ እንዳይመለስ በጀርባችን ተሸክመን መንደሩን በሙሉ ስናካልል ነበር የምንውለው ̋ ይላሉ።

መንደርተኛው እንጨት ካልፈለገ ከእንጨት ለቃሚዎቹ ሴቶች ተረክበው ለሚቸረችሩ ሰዎች ከዋጋ በታች በመሸጥ፤ ለልጆች የሚሆን ነገር ቋጥረው በአስራ አምስት ሳንቲም አቶቢስ ተሳፍረው ወደ መንደራቸው እንደሚመለሱ ያስታውሳሉ።

የመጀመሪያውን ልጅ ለብቻቸው በጥንካሬ ሲያሳድጉ የተመለከቷቸው ጥበበኛው ባለቤታቸው የትዳር ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል። ቀድሞ የደረሰባቸው ቁስል ያልደረቀላቸው እኚህ ሴት በእንቢታ ቢፀኑም፤ ወዳጅ ጎረቤቶቻቸው ከአንድ ሁለት ይሻላል ትዳር መተጋገዣ ነው እያሉ በመምከር ወደ ትዳር ህይወት እንዲገቡ ያደርጓቸዋል።

በወቅቱ ለብቻቸው ታግለው ልጃቸውን ሲያሳድጉ የሞላላቸው ባይሆኑም ምንም አልጎደለባቸውም ነበርና ትዳር ቢያስፈራቸውም ተጨማሪ ልጆች ለመውለድ፤ ብሎም አጋር ለማግኘት በማለት አገቡ።

ባለቤታቸው በሽመና ስራ እሳቸው እንጨት ለቅሞ በመሸጥ ኑራቸውን ለማቅናት ደፋ ቀና ሲሉ የኖሩ ሲሆን በትዳራቸውም ስድስት ልጆችን ለማፍራት በቅተዋል። እርጉዝ ሆነው እንኳን ጓዳቸው እንዳትጎድል ሲሉ የእንጦጦን ተራራ ሳይረግጡ እንደማይወሉ የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ የዛሬ አስር አመት አካባቢ አደጋ እስኪደርስባቸው ድረስ ለአመታት እንጨት ለቅመው ሸጠዋል።

አንድ ቀን እንደልማዳቸው ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ነገር አሰናድተው በጠዋት ከቤታቸው ይወጣሉ። በእለቱ በለስ ቀንቷቸው እንጨት ቆራጮች ሲቆረጡ መሬት የወዳደቀ ጉቶ በብዛት አግኝተው በመዳበሪያ ሞልተው ለገበያ ለመድረስ ጣደፍ ጣደፍ ሲሉ ነበር ወድቀው ክፉኛ የተጎዱት፤ የአጥንት መሰበር የገጠማቸው እኚህ ሴት አጥንቱ እስኪገጥም ድረስ ቤት ዋሉ።

በወቅቱ ልጆቻቸውም ደርሰው ስለነበር ባገኙት ገንዘብ ለአጥንት መጠገኛ እያሉ ሲመግቧቸው፤ ከስራ ተነጥሎ የማያውቀው ገላቸው ሲያርፍና ሌሎች ምክንያቶች ተጨማምረው የስኳር ታማሚ ሆኑ። በዚህ ምክንያት ከልጅነት እስከ እውቀት ከሚሰሩት ስራ ተለያይተው ቤት ቀሩ።

በዚህ መካከል ጤናቸው እየተመለሰ ሲሄድ አንድ የአካባቢው ልጅ ቀበሌ ውስጥ ለሳቸው የሚሆን ስራ መኖርን ነግሮ ወደ ወረዳ ፅህፈት ቤት እንደወሳደችውና እዛም የማስተባበር ስራን ሲሰሩ መቆየታቸውን ያብራራሉ።

በሽመና የሚተዳደሩት ባላቸው አቅም እየደከመ ሲሄድ ለመኖሪያ የሚከፈል ሲጠፋ ወደ ባላቸው ዘመዶች ተጠግተው መኖር እንደጀመሩ የሚናገሩት ወይዘሮዋ ልጆቻቸው እድገው ራሳቸውን ቢችሉም ለእርጅና ዘመን መጦሪያ ያለማፍራታቸው ሁልጊዜ ሆዳቸውን እንደሚበላቸው ይናገራሉ።

ልጆቻቸው ገሚሶቹ አረብ ሀገር ደርሰው የመጡ ያሰቡትን ያህል ኑሮ ያልሞላላቸው መሆኑን ይናገራሉ። ገሚሶቹ ደግሞ በአነስተኛ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉ ናቸው። የመጨረሻው ልጃቸው አሁን አስራ ዘጠኝ አመቱ ሲሆን በስተመጨረሻ ያገኙት ልጅ ጥሩ ውጤት አምጥቶ አሁን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑን ያስረዳሉ።

የአራት ወንዶችና የሶሰት ሴቶች እናት የሆኑት እኚህ ሴት ዳግም ሌሎች ሴቶች ወደዚህ ህይወት እንዳይገቡ መንግሥት ኃላፊነትን መወጣት አለበት ይላሉ። እኚህ እናት አሁን የተጀመረው በጎ ጅማሪ መቀጠል እንዳለበት ይናገራሉ።

አሁን ላይ በአዲስ አበባ በሁለት ቦታ የተከፈቱት እንጀራ መጋገሪያ ማእከላት በውስጣቸው በርካታ ስራ እየፈለጉ ያጡ፤ ብሎም በጥረታቸው ልጆች ለመሳደግ የሚታገሉ፤ እንጨት ከመሸከም አንስቶ ልብስ እስከ ማጠብ በየሰው ቤት እየዞር ከባባድ ስራዎችን በመስራት ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ሴቶችን ይደግፋል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

እነዚህ ሴቶች በድካምና በጉስቁልና ያለ እድሜያቸው እንዳይሞቱ፤ በህመም ቤት ውለው ለቤተሰብም ሆነ ለሀገር ሸክም እንዳይሆኑ እንደ እንጀራ መጋገሪያ ማእከሉ አይነት የተለያዩ በአቅማቸው ሰርተው ጥሪት የሚያፈሩባቸውን ተቋማት ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።

ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ድረ ገፅ ባገኘነው መረጃ መሰረት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ የተገነባውን የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎችን በማስመረቅ ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። ከእነዚህ ማእከላትም መካከል ጉለሌ እንጀራ ማዕከል አንዱ ነው።

ፕሮጀክቶቹ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምረው የተጠናቀቁ የልማት ስራዎች ናቸው::

ጉለሌ እንጀራ ማዕከል ለመዲናዋ ከለሚ ኩራ የእንጀራ ማዕከል በመቀጠል ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካ ሲሆን በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የስራ እድል የፈጠረ ነው።

የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ህንጻዎች ፣ የህጻናት ማቆያ ፣ የእህል ማከማቻ ፣ ወፍጮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተ ነው። 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ተገጥሞለታል፤ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፤ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን፤ ሁለት ወፍጮዎች፤ 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው ይሰሩበታል።

በእንጀራ ማዕከሉ ውስጥ የስራ እድል የተፈጠረላቸው እናቶች ከዚህ በፊት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ሲተዳደሩ የነበሩ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው እና የኑሮ ጫና የበረታባቸው እናቶች ናቸው። ይህ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክት እንደ ወይዘሮ አባይነሽ ያሉትን እናቶች ተስፋ ያለመለመ በመሆኑ ይደግ ይጎልብት ብለናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You