ደሎ መና፡- በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ሦስት ሺ 500 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችልና አንድ ሺ 836 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከፍተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ተጀመረ፡፡ ለፕሮጀክቱ ሥራ ስኬታማት የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የፕሮጀክቱን የመሠረት ድንጋይ ከትናንት በስቲያ ባስቀመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ወደሥራ የሚገባ ሲሆን፣ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ደግሞ የአካባቢው ኅብረተሰብ ድጋፍና ክትትል ያስፈልገዋል፡፡
ከአገር ለመውጣትና ለመሰደድ የሚዳርገው አንድም ድህነት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፣ ከዚህ በኋላ ግን የኦሮሞ ልጆች ለመሰደድ በሚያደርጉት ጥረት በውኃ እንዳይበሉና በሰው አገርም እንዳይንከራተቱ በሚፈጠረው የልማት በር ሁሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ ሌት ተቀን በመስራትና ድህነትን በማስወገድ አንድነትን ማጠናከር የግድ እንደሚልም አስገንዝበዋል፡፡ ወገብ እስኪጎብጥ እጅ ለእጅ በመያያዝ ያለ እረፍት መስራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የወረዳው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መዲና አብዱሬ እንደገለጹት፤ በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሚሆነው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሲሆን፣ በተለይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
አቶ ሽመልስ ያሉትን በመጥቀስም ድህነትን ለማጥፋት ጠንክረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአካባቢውም ያሉት ሴቶች ጠንካራና በራሳቸው ጥረት ሰርተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህንኑ ጥንካሬያቸውን እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው ለም መሆኑን በመጥቀስም፣ ሁሉንም ማብቀል እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ እህልም ሆነ ለሽያጭ ማቅረብ የሚችሉትንም አትክልትና ሌሎችን በማምረት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡
በግንባታው ከሚሳተፉት ተቋራጮች አንዱ የሆነው የጋሻው በንቲ የውሃ ሥራዎች ጠቅላላ ተቋራጭ ኃላፊ አቶ ጋሻው በንቲ በበኩላቸው «በስፍራው የተገኘነው ከፍተኛ የመስኖ ግንባታ ሥራ ለመጀመር ነው» ሲሉ ጠቅሰው፤ «ድርጅታችን ጋሻው በንቲ የውሃ ሥራዎች ጠቅላላ ተቋራጭ ከድሪባ ደፈርሻ ጠቅላላ ተቋራጭ ጋር በመሆን የዚህን የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ጀምሯል» ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ጋሻው ገለፃ፤ ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በተቀመጠው የሦስት ዓመት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራውን አጠናቀው ለማስረከብ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ ወደ 255 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ወደ 3ሺ500 ሄክታር መሬት ማልማት ያስችላል፤1ሺ836 የሚሆኑ በሁለት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ሥር የሚገኙ የዋበሮና ጨሪ ገበሬ ማህበራት አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የፕሮጀክቱ የውሃ ጠለፋው የሚካሄደው ከያዶት ወንዝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዕለቱ አቶ ሽመልስ በባሌ ዞን በመደ ወላቡ ወረዳ በ60 ሚሊዮን ብር የተገነባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን መርቀው የከፈቱ ሲሆን፣ በመላ ኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓትም በደሎ መና ወረዳ በዋበሮ ቀበሌ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
አስቴር ኤልያስ