ለመንግሥት የሠላም ጥሪ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይገባል!

የሰው ልጆች የተለያዩ ፍላጎቶች አሏቸው። እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካትም በየራሳቸው መንገድ ሊጓዙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ፍላጎቶቻቸውም ሆኑ፣ የፍላጎት ማሳኪያ መንገዶች በሌሎች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት አዎንታዊ አልያም አሉታዊ ጉዳዮች ስለመኖር አለመኖራቸው በወጉ ማጤን የተገባ ነው።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን (እንደ ግለሰብ፣ ቡድን ብሎም እንደ ሕዝብ) በዘመናት ጉዞ ውስጥ የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች ለማሳካት አያሌ ትግሎችን አድርገዋል፤ በርካታ ውጣ ውረዶችንም አልፈዋል። በዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ ከመምከር፣ በጠብመንጃ አፈሙዝ እስከ መዋደቅ የደረሱ ስልቶችንም ተከትለዋል።

በዚህም ነፃነትና ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀው ኖረዋል፤ ጭቆናን አስወግደዋል፤ እኩልነትና ፍትሐዊነት እንዲሰፍን የድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ በወንድማማችነትና ብዝኃነት አብረው እንዲኖሩ፤ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ጸንታ እንድትኖር አስችለዋል።

ይሄን መሰሉ የወል ጥቅምና ፍላጎቶች የፈጠሩት የሕልውና መንገድ እና የመንገዱ መዳረሻ የሆነው አብሮነት እና ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዚህ በተቃራኒው በ“እኔ” እና “እኛ” ብቻ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ያልተገባ አካሄድ ሕዝብንም ሀገርንም ዋጋ እያስከፈለ የዘለቀ ሐቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።

በዚህ ረገድ ግለሰቦች አልያም ቡድኖች፤ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ አለመግባባትን፤ መገፋፋትን፣ አለፍ ሲልም ግጭትና ጦርነትን እየቀሰቀሱ ያልተገባ ሰብዓዊም ቁሳዊም ዋጋን ሲያስከፍሉ ኖረዋል።

“ትግል” የሚል የዳቦ ስም የሚሰጠው ይሄን መሰሉ ግለሰባዊ ብሎም ቡድናዊ ጥቅምን ብቻ ማዕከል ያደረገው ስልተ መንገድ፤ የትግልን ዓላማ እና ግብ ባልተረዳ መልኩ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ከፍ ያለ ቀውስ እና ያለመረጋጋት ውስጥ እንዲገቡ፤ ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ኪሳራንም ሳይፈልጉ እንዲያስተናግዱ እያደረገ ዛሬም ድረስ ዘልቋል።

ይሁን እንጂ የትግል ዓላማ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ችግር ውስጥ የሚከትት፣ ሀገርንም እንደ ሀገር የሕልውና ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ ሲገጥም፤ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ቢባል ያንን ችግርና አደጋ ለመቀልበስ ዜጎች ዋጋ ለመክፈል ወስነው የሚከተሉት አካሄድ ነው። ይሁን እንጂ ላለፉት አምስት እና ከዚያ በላይ ለሆኑ አስርተ ዓመታት እየሆነ ያለው ግን ከዚህ እውነት ያፈነገጠ ነው።

ምክንያቱም፣ ነፃነቱ በተከበረለት ማኅበረሰብ ውስጥ ሆኖ በነፃ አውጪ ስም ተደራጅቶ ነፃውን ሕዝብ ነፃነት የማሳጣት አካሄዶች ተበራክተው ታይተዋል። ልማትና ማኅበራዊ ክብሩ በተጠበቀለት ማኅበረሰብ ውስጥ ሆነው፤ የማኅበራዊ ደኅንነት ዋስትና አረጋጋጭ ኃይል ሆነው በመከሰት ሕዝቡን ላልተገባ ማኅበራዊም፣ ኢኮኖሚያውም፣ ሥነልቦናዊም ቀውስ ሲዳረጉ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

በእነዚህና መሰል ጉዳዮች እንደ “መታገያ” አጀንዳ በመያዝ በተለይ ደግሞ ከ2010ሩ ለውጥ ማግስት አያሌ ቡድኖች ራሳቸውን የሕዝብ ሕልውና አስጠባቂ አድርገው ስለዋል። በዚህም ሕዝብ እና መንግሥት መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር፤ ይልቁንም ሕዝብ በደኅንነት ስጋት ውስጥ እንዲገባ እና መንግሥትም ከልማት ይልቅ ሠላምን ማስከበር ዋነኛ አጀንዳው እንዲሆን የማድረግ ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

በርካታ ግጭቶችን ፈጥረዋል፤ ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነትም ተከናውኗል። ዛሬም ይሄው በእነዚህ ቡድኖች ዘዋሪነት የሚከወን የግጭት አዙሪት ከማኅበረሰቡ ላይ እንዳይወርድ አድርገዋል። በአማራ፣ ኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።

መንግሥት ዛሬም ችግሮችን እነሱ ባነሱት የጠብመንጃ አፈሙዝ ብቻ ለመፍታት መሞከሩ ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን በማመን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥያቄ አለን ከሚሉ ነፍጥ አንሺዎች ጋር ለመነጋገር ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን እያደረገ ይገኛል። በዚህ ጥረቱም የተወሰኑት ተቀብለው ወደ መፍትሔ ሲሄዱ፤ አንዳንዶቹ ግን ዛሬም በጫካ ሆነው ነፍጥን እንደ መፍትሔ ቆጥረው ይገኛሉ።

ሆኖም በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚካሄድ ትግልም ሆነ እንዲመለስ የሚፈለግ ጥያቄ፣ በውይይትና ድርድር ከሚገኘው በፍጹም የተሻለ አይደለም። ይልቁንም የትግል ዓላማው ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘት፤ የሀገርንም ሕልውና ለማጽናት ከሆነ፤ ምርጫ ሊሆን የሚገባው ቁጭ ብሎ በሠላማዊ መንገድ መነጋገርና መፍትሔ ማምጣት ነው።

ምክንያቱም በሠላም መነጋገር የዜጎችን ሞትና መፈናቀል እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስን ያስቀራል። በአንጻሩ ጦርነት፣ ንብረት ያወድማል፣ አካል ያጎድላል፣ ክቡሩን የሰው ሕይወትም ይበላል፤ ከፍ ያለ ማኅበራዊና ሥነልቡናዊ ቀውስንም ያስከትላል። ይሄን የሚፈልግ የሕዝብ ጥያቄ አንጋቢ ኃይል ደግሞ ሊኖር አይችልም፤ አይገባምም።

ምክንያቱም ከጦርነት የሚያተርፈው የሀገር እና የሕዝብ ጠላት እንጂ፤ የሕዝብ ልጅና ሀገር አይደሉምና። መንግሥትም እንደ መንግሥት ለእነዚህ ኃይሎች ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ የሚያቀርበው የሚሄዱበት ያልተገባ አካሄድ ተገንዝበው ወደሠላሙ መንገድ ይመለሳሉ በሚል እሳቤ ነው።

በመሆኑም ጠብመንጃ አንግተው በጫካ ሆነው የሚዋጉ ሁሉ፤ ጫካ የመግባታቸው ምክንያት፣ ጠብመንጃ የማንሳታቸው ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄ ከሆነ፤ የሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው በጦርነት ውስጥ ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉ ሳይሆን፤ በሠላም ቁጭ ብሎ በመነጋገር እና ከራስ ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥቅምን በማስቀደም መሆኑን በመገንዘብ፤ በመንግሥት ለሚቀርቡ ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይገባል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You