ወጣት ሆሄያት ብርሃኑ እና ዮሐንስ ዋሲሁን ከቡና ገለባ እና ከሰጋቱራ ከሰል የሚያመርት ማሽን እንዲሁም ‹‹ቅልብጭ›› የተሰኘ የከሰል ምድጃ የፈጠራ ባለቤቶች ናቸው። እነዚህን የፈጠራ ሥራቸውን ለማሳደግ በማሰብ በ2015 ዓ.ም ‹‹ኸስኪ ኢነርጂ እና ቴክኖሎጂ ፒኤልሲ›› የተሰኘ ድርጅት መስርተዋል። ድርጅቱም የታዳሽ ኃይልና ንፁህ የማብሰያ መፍትሔዎች ለማቅረብ የተመሰረተ ነው።
ባለሙያዎቹ በታዳሽ ኃይል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ ሲሆን፤ ከቡና ገለባ እና ከሰጋቱራ ከሰልን የሚተኩ ማገዶዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። በተጨማሪም ‹‹ቅልብጭ›› የሚል ስያሜ የሰጡትን የከሰል ምድጃ እያመረቱ በማከፋፈል ላይ ይገኛል።
እነ ሆሄያት የፈጠራ ስራውን ከጀመሩ ሦስት ዓመታት ያህል አስቆጥረዋል። የፈጠራ ሀሳቡን ለማመንጨት መነሻ የሆናቸውን አጋጣሚ የተፈጠረላቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ምህንድስና ትምህርት ተማሪ በነበሩት ወቅት ነው።
በወቅቱ ለሥራ ላይ ልምምድ (internship) የቡና አምራች አርሶ አደሮች አካባቢ የመሄድ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል። በገዝወ ለቡና አምራች አርሶ አደሮች ስልጠና የመስጠት እድልም ያገኛሉ። ስልጠናውን በሚሰጡበት ወቅት ‘አርሶ አደሮች ቡና ሲያመርቱ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የሆነው የቡና ገለባ ክምችት መብዛት’ እንደሆነ አርሶ አደሮቹ ሲናገሩ ይሰማሉ። የአርሶ አደሮቹን ችግር ካዳመጡ ጊዜ ጀምሮ እነ ሆሂያት አላረፉም፤ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ በጥልቀት በማሰብ የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጨት ውስጥ ይገባሉ።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ሆሄያት እንደሚለው፤ ኢትዮጵያ በቡና ምርት በዓለም አምስተኛ ስትሆን በአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ናት። በመሆኑም በዓመት በጣም ብዙ የቡና ምርት ይመረታል። ከሚፈለፈለው ቡና የሚወጣው ገለባ ደግሞ በርካታ ነው። ይህም በቡና አምራች አርሶ አደሩ አካባቢ ላይ ብዙ ችግሮች እያደረሰ ይገኛል። ‹‹የቡና ገለባው አካባቢውን በመሙላት ቦታ ይይዛል፤ ሲቆይ ደግሞ የሚሸት ሲሆን የአካባቢ ላይ ለሚኖረው ማህበረሰብ ለተለያዩ አይነት ህመም ይዳርጋል። እንዲሁም ብዙ ተያያዥ ችግሮች ሊያስከትል እንደሚችል አርሶ አደሮቹ በሰጡን መረጃ መረዳት ችለናል›› ይላል።
እነ ሆሄያት ለአርሶ አደሩ ችግር መፍትሔ ለመፈለገ ባደረጉት ጥረት የቡና ገለባን ወደ ኢነርጂ መቀየር የሚችል ማሽን ዲዛይን በማድረግ ለመስራት ችለዋል። አዲሱ ማሽን ከቡና ገለባ ፔሌት የሚባሉ እንደ ከሰል አይነት የማገዶ እንክብሎችን ማምረት የሚችል ነው። ማሽኑን በሀገር ውስጥ ያሉ ጥራት ያላቸው ቁሳቁስን ተጠቅመው የሰሩ ሲሆን፤ በየጊዜውም ማሻሻያ እየተደረገለት እያደገና አሁን ያለውን ቅርጽና ይዘት ሊኖረው ችሏል።
ማሽኑን የመስራቱ ሀሳብ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተጸነሰ ሀሳብ እንደመሆኑ እቅዱን በማዳበር ዲዛይን በማውጣት ወደ ሥራ ለማስገባት ሦስት ዓመታት መፈጀቱን ሆሄያት ያመላክታል። ይህ ከቡና ገለባና ሰጋቱራ የማገዶ እንክብሎችን ማምረት የሚችለው ማሽን በመጀመሪያ በትንሹ ለሙከራ ያህል የተሰራ ሲሆን፤ ይህንን አሻሽሎ በትልቁ በመስራት ከሰጋቱራ የማገዶ እንክብሎችን እንደሚያመርት ያስረዳል።
አሁን ማሽኑ ከቡና ገለባ ማገዶ እያመረተ ባይሆንም፣ ከሰጋቱራ ማገዶን በማምረት ወደ ጥቃቅን ማገዶ (ወደ ፔሌቶች) እየቀየረ ይገኛል። ማሽኑ ከቡና ገለባ ማምረት አቅቶት ሳይሆን አሁን ባለበት አካባቢ ሰፊ ክምችት ያለው ሰጋቱራ በመሆኑ ነው ብሏል። በቀጣይ ደግሞ ከቡና ገለባ ፔሌቶች ያመርታል ሲል ሆሄያት አስታውቋል።
ሌላው የፈጠራ ውጤታቸው ደግሞ ‹‹ቅልብጭ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የከሰል ምድጃ ነው። ምድጃው የተሰራው ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቁሳቁስ ሲሆን፣ ብረት፣ ፋይበር ግላስ እና ጋልባናይዝድ ስቴል በመጠቀም ተሰርቷል፡ ‹‹ቅልብጭ ምድጃ›› ከሰል ቆጣቢ ነው፤ ዙሪያው የተሞላው ኦቪን፣ ዳቦ መጋገሪያ እና ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ የሚገኝ ፋይበር ግላስ በተሰኘ ቁስ ነው። ‹‹ንጹህ የማብሰያ መፍትሔዎች ማቅረብ ሲባል ማገዶውን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ምድጃም በጣም ወሳኝ ነው፤ እኛም ሁለቱንም ማቅረብ ችለናል›› ይላል ሆሄያት።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የቤት ውስጥ የአየር መበከል ዓለም ችግር እየሆነ መጥቷል፤ የቤት ውስጥ የአየር ብክለት በዓለም በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን ሰዎች እየገደለ ነው። በኢትዮጵያም እንዲሁ የቤት ውስጥ የአየር መበከል(indoor pollution) ችግር እየሆነ ከመምጣቱ በላይ በዓመት ከ50ሺ በላይ ሰዎች በዋናነት ደግሞ ሴቶችን ይገድላል። የአገሪቱን የሞት ምጣኔ አምስት በመቶውን የሚይዘውም ይሄው የቤት ውስጥ የአየር መበከል ሆኗል።
ጉዳቱ የሚከሰተው በቤት ውስጥ ለማገዶነት በምንጠቀመው የከሰል እና የእንጨት ጭስ ምክንያት ነው። ለዚህ ችግር መፍትሔ ለማበጀት የተሻሻለ ምዳጃ ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን በማመን እነ ሆሂያት ይህን የፈጠራ ቴክኖሎጂ ሰርተዋል።
ሆሄያት እንደሚለው፤ ምድጃው ከተለያዩ ጥራት ካላቸው ቁሳቁስ ነው የሚመረተው። ምድጃው በጥራት የሚመረት ሲሆን፤ ጥራትን ከዋጋ ጋር አዋህዶ በተመጣጣኝ ዋጋ ህብረተሰቡ ሊጠቀምበት እንዲችል ተደርጎ ተሰርቷል። ሌሎች ከውጭ የሚገቡ የተሻሻሉ ምድጃዎች እንዱ ጠቅሶ፤ ይህ ምድጃ ግን ከእነዚህ በጣም በተሻለ ጥራት እና በቅናሽ ዋጋ ተመርቶ ለህብረተሰቡ የቀረበ ነው ብሏል።
ምድጃዎቹም ትንሹ አንድ ሺ 300 ብር፣ መካከለኛው አንድ ሺ700 ብር እና በመጠን ከፍ ያለው ደግሞ ሁለት ሺ300 ብር የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ለገበያ እየቀረቡ መሆናቸውን ወጣት ሆሄያት አስታውቋል። ምድጃውን ህብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ በማድረግ ለገበያ ማቅረብ ከተጀመረ ሰባት ወራት ያህል እንደተቆጠሩ ጠቅሶ፤ ምድጃው ከሰልን በጣም እንደሚቆጥብ ተናግሯል። ይህ ጠቀሜታው በፍጥነት ተቀባይነትና ተወዳጅነት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው አስታውቆ፣ ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት እንዳለም ይገልፃል ።
እንደ ሆሄያት ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ምድጃው በአዲስ አበባ እና በዙሪያ ባሉ ከተሞች እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ እና በተለያዩ ከተሞች ተደራሽ እየተደረገ ነው። ምድጃው ጥራት ካለው ቁሳቁስ ስለሚሰራ ማገዶ ቆጣቢ ነው። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ700 በላይ ምድጃዎች ለገበያ ቀርበው ተሸጠዋል።
‹‹ምድጃውን እየተጠቀሙ ያሉ ደንበኞችም ምድጃው ከሰል እንደቆጠበላቸው እና ሲታይም ውበት እንዳለው ይነግሩናል›› የሚለው ሆሄያት፤ ይህን ታዳሽ ኃይል በተለይ ለገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል። ባለፉት ሳምንታት መንግሥታዊ ካልሆነ አንድ ድርጅት ጋር በመተባበር በዳውሮ፣ በበደሌ እና በመሳሳሉት የገጠሪቱ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ማህበረሰቦች ምድጃውን የማስተዋወቅ ሥራ መስራቱን አስታውቋል።
የምድጃውን አጠቃቀም ጭምሮ በማሳየት ህብረተሰቡ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንን አብራርቶ፣ ህብረተሰቡ ቁጠባ ማድረግ እንዲችልና ብድር ተመቻችቶለት ምድጃዎቹን መግዛት የሚችልበት ሁኔታ እየመቻቸ እንደሆነም አስታወቋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችንም መስራታቸውን የሚገልጸው ሆሂያት፤ በገጠሪቷ የአገሪቱ አካባቢዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ‹‹ሮኬት ስቶቭ›› የተሰኘ በእንጨት የሚሰራ ምድጃ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የፈጠራ ሥራ የማገዶ ፍጆታ በጣም ይቀንሳል፤ ጭስ የሚቀንስና ጥራት ያለው ምርት መሆኑንም ተናግሯል።
እነ ሆሄያት ‹‹ኢንስቲትዩሽናል ስቶቭ›› የተሰኘ ሌላ ምድጃንም እያመረቱ ይገኛሉ። ይህ ምድጃ በተለይ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለትምህርት ቤቶች ፣ለስደተኛ ኮምፓች እና ለብዙ ሰዎች ምግብ ለሚያዘጋጁ መሰል ተቋማት የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህ ምድጃ በሰፊው ምግብ ለማብሰል የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ማገዶ ቆጣቢ መሆኑን ተናግሯል።
እነ ሆሄያት፤ የታዳሽ ሃይልና የማብሰያ ቴክኖሎጂ ላይ ብዙ ሥራዎች ለመስራት እቅደዋል። በዚህ ረገድም እስካሁን ሠርተው ለገበያ ያቀረቧቸውን የፈጠራ ውጤቶች /Technology/ በየጊዜው ለማሻሻልና ለማዘመን እንደሚሰሩ ጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡን ኑሮ ሊያሻሽሉና ሊያቀሉ የሚችሉ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች መስራቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎችንም በብዛት በማምረት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ይገልጻል።
‹‹አሁንም በሙከራ እና ዲዛይን ደረጃ ላይ ያሉ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን እየሰራን ነው›› የሚለው ሆሄያት፤ እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ቀስ በቀስ እያሳደጉ የሚፈለገው ውጤት ላይ ሲደርሱ ለህብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቋል። በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሉ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የፈጠራ ሥራዎች እቅድ እንዳላቸው አመላክቷል።
ከመነሻ ንግድ ስራ የፈጠረ ሀሳብ /Startup/ ተነስተው እየሰሩ ያሉት ሥራ ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሶ ውጤት እያመጣ መሆኑን በተጨባጭ እየተመለከቱ መሆናቸውንም ሆሂያት ጠቅሶ፣ ይህ ደግሞ ለስራው የበለጠ መነሳሳት እንደሚፈጥር ተናግሯል። ህብረተሰቡ ምድጃዎቹን ለመጠቀም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ ምድጃዎቹን በስፋት በማምረት ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።
አሁን እነዚህን ምርቶች በተለያዩ የገበያ ቦታዎች እየተሸጡ መሆናቸውን ገልጾ፤ ምርቶቹን ሰዎች የሚፈልጉበት ቦታ ድረስ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ይናገራል። ‹‹የህብረተሰቡን ፍላጎት በማርካትና ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለሚያደርጉት ጥረት ሀሳባቸውን በመደገፍ አብሮ መስራት የሚፈልግ ድርጅት ካሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ሆሄያት እንደሚለው፤ የፈጠራ ስራቸውን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ብዙ ወጣ ወረዶችን ማለፍ የግድ ብሏቸው እንደነበር አስታውሶ በተደጋጋሚ በመሞከር እና ብዙ ጥረት በማድረግ የሚፈልጉትን ማሳካት እንደቻሉ ሌሎቸም ይህንን መንገድ ቢከተሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግሯል።
‹‹የፈጠራ ሥራ ሁልጊዜ መሻሻል ማሳየትን ይጠይቃል፤ ሥራዎቻችን በአንዴ ጊዜ እዚህ ደረጃ ላይ አልደረሱም፤ ከአራትና ከአምስት ጊዜያት በላይ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፤ የማሻሻል ሂደት አይቆምም፤ አሁንም የምናሻሽለው ካለ ይቀጥላል›› የሚለው ሆሄያት፤ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በየጊዜው ለማሻሻል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክቷል።
የኢኖቬዝ-ኬ ኢትዮጵያ ማዕከል እና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት መነሻ ንግድ ስራ የፈጠረ ሀሳብ /Startup/ ፕሮግራም ላይ ሀሳባቸው አሸናፊ ሆኖ ለመሳተፍ እድሉ ማግኘታቸውን ሆሄያት ጠቅሶ፣ በዚህም በየሁለት ሳምንቱ ባለሙያዎች ያሉበትን ሂደት በመመልከት ድጋፍ እያደረጉላቸው ለአምስት ወራት ያህል የማማከር አገልግሎት እንደተሰጣቸው አስታውቋል። ይህ ብዙ ነገሮች እንዲያስተካክሉ እንደረዳቸው እና ከጀማሪ የስራ ፈጣሪነት ተነስተው አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ እንደቻሉ ሆሂያት ተናግሯል።
በፈጠራ ሥራ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች የመነሻ ንግድ ስራ የፈጠረ ሀሳብ ያላቸው /Startup/ መጀመሪያ ለመፍታት የሚፈልጉት ችግር በደንብ አውቀው መፍትሔ ለማምጣት መስራት አለባቸው ሲል ሆሂያት ይገልጻል፤ በአካባቢያቸው እና በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በሚገባ ከመረዳት ባሻገር ለችግሩ የተገኘን መፍትሔ ህብረተሰቡ ተቀብሎ ሊጠቀምበት የሚችለው ነው እንዴ የሚለውን በጥልቀት ማጤን አስቀድሞ መስራት ያለበት የቤት ሥራ መሆኑን ይጠቁማል።
ምርታቸው አንድ ጊዜ እንደተሰራ በዚያው የሚቀጥል ሳይሆን፣ ሁልጊዜ እያሻሻሉ እና ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ እያዘመኑ መምጣት ያስፈልጋቸዋልም ብሏል። ሥራቸው ውጤት አፍርቶ ምርቶታቸው ለገበያ ላይ ሲቀርቡ ደግሞ የምርቶቻቸውን ተጠቃሚዎች አስተያየት በመቀበል የተሻለ ሥራ መስራት አለባቸው። ለዚህም ሁሌጊዜም ምርቶቻቸውን እያሻሻሉ መገኘት አለባቸው ሲል ይመክራል።
ጀማሪዎች ያላቸው የቴክኖሎጂ እውቀት ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገልጾ፤ ከዚህ ጋር ቢዝነሱን አብሮ ማስኬድ እንደሚጠይቅም አመልክቷል። ከቢዝነስ አማካሪ ተቋማት ጋር መስራት ሥራቸውን ወደ ገበያ ማሳደግ እንደሚያስችላቸው አስገንዝቧል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም