ሕዝብን ዕረፍት የሚነሱ የጥፋት ተግባራት ሊቆሙ ይገባል

ኢትዮጵያን አላላውስ ብለው እግር እና እጇን ቀፍድደው ካሰሯት ጉዳዮች መካከል ልዩ ልዩ ጥቅሞችን እያሰቡ በተለያየ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ተግባር ዋነኛው ነው። እነዚህ ኃይሎች በተለያየ አቅጣጫ የራሳቸውን ብቻ ጥቅም አስበው የሚንቀሳቀሱ ስግብግቦች ናቸው። እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ በሌላ በኩል ማመዛዘን ባለመቻል፤ ‹‹እኔ ብቻ ተወዳጅ፣ እኔ ብቻ ተደማጭ፣ እኔ ብቻ መሪ ልሁን›› የሚሉም አሉ። እነዚህ ጉዶች ሕዝብን ዕረፍት እየነሱ፤ ኢትዮጵያዊነትን እያደበዘዙ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው።

ከሆዳቸው ውጪ የማይታያቸው ስግብግቦች፤ አገር ካልቆመች ማንም እንደማይቆም፤ እነርሱም ቢሆኑ የዘረፉትን መብላት እንደማይችሉ ለማወቅ እንኳ ጭንቅላታቸውን የማይጠቀሙበት ጭፍኖች መብዛታቸው ሀገርን በብዙ መልኩ ዋጋ እያስከፈላት ነው። በየአቅጣጫው በየጫካው ተደራጅተው፤ በቡድን ተሸሽገው መኪና እያስቆሙ የሚዘርፉ እና ሕዝብ የሚያሰቃዩ፤ አልፈው ተርፈው መኪና ከማቃጠል ባሻገር ልጆችን ያለአባት እና ያለእናት የሚያስቀሩ የሰውን ሕይወት የሚቀጥፉ ጥጋበኞች በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብም እባካችሁ አቁሙ ቢባሉም ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ሕዝብ አያውቅም ማለት አይቻልም። ለጊዜው ቢሸፋፈንም መገለጡ አይቀርም። በየመንገዱ ከሚካሄደው ዘረፋ ባሻገር ሰው እያሰማሩ የሚያስገድሉ እና የሚገድሉም አሉ። ከላይ ከላይ በቡድን ተደራጅተው የዕለት ዘረፋ እና የዕለት ሆድ መሙያ አስፀያፊ ድርጊት የሚፈፅሙ ቢመስሉም፤ አሰማሪዎቹ ለውጪ ኃይል የተገዙ የኢትዮጵያ ጠላትን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም።

እነዚህ ተራ ሆነው በየቦታው መንገድ ዘርፈው ሀገር እና ሕዝብን የሚያሰቃዩትም ሆኑ፤ በውጪ ጠላቶች ተገዝተው ኢትዮጵያን የሚበድሉ እኩዮች ለጊዜው የተሳካላቸው ቢመስላቸውም በሕዝብ ታፍነው እንደሚጠፉ አያጠያይቅም።

በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዘራፊ ቡድኖች በየመንገዱ ሕዝብ እያስጨነቁ፤ በሚፈፅሙት ንጥቂያ እና ዝርፊያ አሁን ላይ ሕዝብ እየተማረረ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የተዘረፈና የተበደለ ሕዝብ ዘራፊን ማጥፋቱ አይቀርም፤ ምክንያቱም ተዘራፊ ለጊዜው እንጂ ዘለዓለሙን ሲዘረፍ አይኖርም።

ሀገር ለማፍረስ የተነሱና ሕዝብን ዕረፍት የሚነሱ ከድርጊታቸው ካልታቀቡ ሁኔታው አደገኛ ይሆናል። ይህ ሲባል ጦሱ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል። በየቀኑ የሚፈፅሙት ድርጊት የሚዘረፈው ሰው ላይ እና የሚሞተው ሰው ቤተሰብ ላይ መጥፎ የጥላቻ መርፌን ብቻ ሳይሆን ሚስማር እየመቱ ነው። ሚስማሩ በበዛ ቁጥር ሰው እንጨት አይደለም፤ ሥጋ እና አጥንት በመሆኑ ቁስሉ ያመዋል። ቁስሉ አመርቅዞ አደጋ ከማስከተሉ በፊት አቁሳዮቹን ማስወገዱ አይቀርም።

መንግሥት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። ሕዝብ መተባበር አለበት። በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በሌሎችም በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝብን እያማረሩ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ቡድኖች አደብ ሊገዙ የሚችሉት ሕዝብና መንግሥት ሲተባበሩ ብቻ ነው።

በብሔርና በሃይማኖት ስም በየሰፈሩ የተለያዩ ቡድኖችን በነፃ አውጪ ስም በማደራጀት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ሆኖም በሠላም ወዳዱ ሕዝብ ጥረት ኢትዮጵያ ዛሬም አልፈረሰችም። ኢትዮጵያዊነት ሲጎላ እና ሕዝቡ በአንድ ላይ ለማደግ ሲጓጓ፤ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊነትን ከመንደር አሳንሰው ማየት በሚፈልጉ አካላት ኢትዮጵያ በርካታ ገፈቶችን ስትቀምስ ቆይታለች። ዛሬም እየቀመሰች ነው። ከኢትዮጵያዊነት በላይ ብሔር እና ኃይማኖት መጉላት አለበት እያሉ ኢትዮጵያዊነትን ለመጥለፍ ገመድ ለሚጥሉት መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ደግሞ ለጊዜው ሕዝብን ዕረፍት ቢነሱም ቆይተው መጋለጣቸው እና በፍርድ አደባባይ መቆማቸው አይቀርም።

የሰው ልጅ በአፉ እያወራ በጭንቅላቱ ምን እንደሚያስብ አይታወቅም። ነገር ግን በየዋህነት ሴረኞችን እና ጥቅም አሳዳጆችን ቀርበው የሚከተሉ፤ የተነገረውን ሁሉ የሚያምኑ ደግሞ ብዙ ናቸው። ጉዳዩ ተራ በኪስ ስለሚገባ ገንዘብ አይደለም። እንደውም የሀገር ጥቅም ጉዳይ ብቻም አይደለም። እንደሀገር የመቆም አለመቆም ጉዳይ ነው። ስለሀገር ሲሉ ራሳቸውን የሰው ብዙ ናቸው።

ለዚህ ነው፤ ሕዝብ አይን አፍጥጦ ጆሮውን አቁሞ የሚሰማው ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት ጉዳይ ነው። ሕዝብ የሚፈልገው ኦሮሞ ከአማራው፣ አማራ ከትግሬው፣ ትግሬው ከአፋሩ፣ አፋር ከሱማሌው፣ ሱማሌ ከቤንሻንጉሉ፣ ቤንሻንጉል ከጋምቤላ፤ ጋምቤላ ከደቡቡ እና ሌሎቹም በአንድነት ሲኖሩ ማየት ነው። የኢትዮጵያ ትልቅነት ጉዳይ ሲነሳ ትኩስ እንባ በጉንጫቸው የሚያፈሱ ዜጎች የምናየውም ከዚሁ የሀገር ፍቅርና የአብሮነት ዕሳቤ አንጻር ነው።

የሕዝብን አንድነት ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የሞት የሽረት ጉዳይ ነው። የሕዝብ አንድነት መሸርሸር የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በእውቀት እጦት የታመሙ ጤነኛ መስለው መታመማቸውን ተረድተው ከመታከም እና ተገቢውን መድኃኒት በቅጡ ከመውሰድ ይልቅ በተለያዩ አካባቢዎች ቡድን አደራጅተው ሕዝብን ዕረፍት መንሳታቸውን ማቆምም ሆነ ማስቆም የግድ ነው። ይህን ድርጊታቸውን ካላቆሙ በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ እንደቆሙ ይቆጠራል። ስለዚህም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን አረሞች ነቅሎ ሊጥላቸው ይገባል።

መተማመን ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። እነዚህ አረሞች ተነቅለው መጣል እንዳለባቸው ሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝብ ሊተማመንና ወደ እርምጃ ሊገባ ይገባል። መንግሥት ሁሉንም ነገር እንዲያደርግ መጠበቅ የሚያዋጣ አይደለም። መንግሥት የሚያደርገውን መደገፍና አብሮ የጋራ ጠላቶችን ማጥፋት ለማንም የሚተው ተግባር አይደለም።

በሕገወጥነት እና በወንጀል በመጨማለቅ ዘላቂ ትርፍ ማግኘት አይቻልም። ቤተሰብ እንደቤተሰብ እንዲቆም፤ በእኩል መብት መንቀሳቀስ እንጂ አንዱ ሌላውን መደፍጠጥ አይችልም። እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ነው ብሎ ካልተቀበላችሁኝ አድራሻችሁን ላጥፋ የሚለው አባባል ቤት ያፈርሳል እንጂ ቤት አያፀናም።

ኢትዮጵያዊነት የአሸናፊነት እና የነፃነት ምልክት ነው። አሸናፊው የሆነ ቡድን ወይም ብሔር አይደለም። አሸናፊው መላው ሕዝብ ነው። ለሆዱ ያደረም ሆነ እብሪተኛ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ቦታ የላቸውም። አሁን ላይ የሚያሸንፈው ኢትዮጵያዊነት ብቻ በመሆኑ ከጠላት ጋር ተደራድረው አገር ለማፍረስ የሚሠሩም ሆኑ እኔ ብቻ ልንገሥ የሚሉ ግብዞች ከድርጊታቸው ይታቀቡ። ሕዝብን ዕረፍት የሚነሱ የጥፋት ተግባራት ሊቆሙ ይገባል። ካልሆነ በሀገሩ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስትንፋሳቸውን መበጠሱ የማይቀር ነው።

ፌኔት (ከመሳለሚያ)

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You