አዲስ አበባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ8 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን አስተናግዳለች

አዲስ አበባ፡– ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማስተናድ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በኢኮኖሚው ላይ ፈሰስ መደረጉን የከተማዋ ባሕል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሁን ላይ የከተማዋ የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ የተሻለ እና በጥሩ ደረጃ ላይ ነው።

በከተማዋ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪስት ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን የተናሩት ቢሮ ኃላፊዋ፤ በዚህም ባለው ቀመር ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተማዋን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

በዘጠኝ ወር ውስጥ ከታቀደው በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከተማዋን መጎብኘታቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ በገቢ ደረጃም በፊት በነበረው ዝቅተኛ ቀመር ተሰልቶ 49 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በጎብኚዎቹ አማካኝነት በተለያየ መልኩ ኢኮኖሚው ላይ ፈሰስ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ ናት ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ፤ ሀገሩን ለማወቅ ከሚመጣው ቱሪስት አንጻር በተለይ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ምርቃት በኋላ የመጣው የቱሪስት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ከሱዳን፣ ከሶማሌ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራ እና ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ለሕክምና እና ለቢዝነስ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ መዲናዋ እንደሚመጡ ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ስድስት ወር ውስጥ 465 ሺ 366 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች አዲስ አበባን መጎብኘታቸውንም ገልፀዋል። በዚህም 29 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በተለያየ መልኩ ከጎብኚዎቹ መገኘቱንና ኢኮኖሚው ላይ ፈሰስ መደረጉን አስረድተዋል።

ከተማዋ በተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተመራጭነቷ እያደገ መምጣቱን የሚናገሩት ዶክተር ሂሩት ካሣው፤ ሁሉም በከተማዋ የሚገኙት አዳዲስ መስሕቦች ለውጭ ሀገር እና ለሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ምቹ እና ሳቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቱሪስቶች መጥተው የሚስተናገዱባቸው ሆቴሎች እንዲሁም የከተማዋ መንገዶች ምቹ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤ የቱሪስት ከተሞች በጨለማ ጭምር ሰው የሚዝናናባቸውና በቂ ብርሃን ያላቸው ናቸው። የኮሪደር ልማቱ ሥራ ሲጠናቀቅ መንገዶች ለእግረኞች ምቹ ስለሚሆኑ ጎብኚዎች በእግር ጉዞ ከተማዋን የሚጎበኙበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል። አጠቃላይ በአዲስ አበባ የሚሠራው የልማት ሥራ ከተማዋ የቱሪዝምን መስፈርት የምታሟላ ምቹ ከተማ እንድትሆን የሚያስችላት ነው።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You