ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ትልልቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ እነዚህ ውጤቶቸ ግን አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ የተገኙ አይደሉም፡፡ በብዙ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች ውስጥ እንጂ፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሠላም መደፍረስ እንደሀገር በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት እንደመሆኑ፣ የሚስተዋለውን የሠላም እጦት በጊዜ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ ትልቅ ሀገራዊ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል የዘርፉ ምሑራን ማሳሰብ ከጀመሩ ውለ ው አድረዋል፡፡
መንግሥት ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ሁሉ ለውይይት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጣ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከየትኛውም ወገን ጋር ለመወያየትና ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነትም አሳውቋል፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞም ወደ ሥራ ገብቷል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ከማን ምን ይጠበቃል? በተለይ ችግሮቻችንን በሠላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ምን መሠራት አለበት? በሚለው ላይ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ እንደሚሉት፤ እንደ ሀገር ሠላምን ለማጽናት ከቤተሰብ ጀምሮ የሁላችንንም ርብርብና መልካም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። በተለይ መንግሥት ሠላምን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ እንደመሆኑ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በሆደሰፊነት መንቀሳቀስ አለበት።
መብቴ ተነክቷል፤ ጥቅሜ አልተረጋገጠልኝም የሚል ቅሬታ ያለው አካልም ሁሉም ችግሮች መፍትሔ ማግኘት የሚገባቸው በምክክርና ውይይት መሆን እንዳለበት አምኖ የሌሎችን ሀሳብ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል።
ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የምናደርገው እንቅስቃሴም ሠላማዊ ወገኖቻችንን ችግር ውስጥ የሚጥል እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሕሮ ውስጥ ወርቃማው ሕግ የሚባል እሳቤ መኖሩን የሚጠቅሱት ፓስተር ፃድቁ፤ ይህም ላንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ነገር ለሌላው አድርግ፣ አንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውንም በሌላው ላይ አታድርግ የሚል ነው።
ይህን ሕግ አክብሮ መንቀሳቀስ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት እንቅፋት የሚሆኑ ተግዳሮቶችን ሁሉ መሻገር ያስችላል።
ሠላምን በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ ለማረጋገጥ መሞከር በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ የሚቆጠር መሆኑን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግሥት፣ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሕዝቡና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለሠላም መስፈን የየድርሻቸውን ጠጠር መጣል ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን ሁሉ ለሠላም ዘብ እንዲቆሙ ማስተማር እንዳለባቸው የሚጠቅሱት ፓስተር ፃድቁ፤ አስተማሪዎች ነን የምንል የሃይማኖቱ ሰዎችም የምናስተምረውን ትምህርት በሕይወት በመግለጥ ለተከታዮቻችን አርዓያ ልንሆን ይገባል።
ለችግር መፈጠር ጥቂት ሰዎች አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ሁሉ እያንዳንዳችን የምናደርገው እንቅስቃሴ ለሠላም መጥፋትም ለሠላም መስፈንም አስተዋፅዖ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል የሚሉት ፓስተሩ፤ በኃይል መፍትሔ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች በሕዝቡ ላይ ጉዳት ከማስከተል ያለፈ ውጤት አያመጡም ብለዋል።
በመሆኑም አንዳችን በሌላችን ቦታ ሆነን ሌሎችን ማዳመጥ እና በምክክርና ውይይት ለችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመረጋጋትና ግጭቶች በሰው ሕይወት፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀልና ሰብዓዊ ቀውሶችን እያስከተሉ ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው አንዳችን ሌላችንን ማዳመጥ ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ አካታች የውይይትና ምክክር መድረኮችን መፍጠር ያስፈልጋል።
ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥት ንቁ ታሳታፊ እንዲሆኑ ይጠበቃል የሚሉት መብራቱ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አሁን ላይ እየሠራ ያለውም ግጭትን ለማስቆምና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ማኅበራዊ መስተጋብር ለማጠናከር ነው ብለዋል።
ስለሆነም ወደየትኛውም ግጭት ከማምራታችን በፊት አሉኝ የምንላቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ወደፊት ማምጣትና በሠላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ በቁርጠኝት መታገል ያስፈልጋል።
ሌላኛው ለሠላም መረጋገጥ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄድ ነው የሚሉት ፖለቲከኛው፤ በዚህም ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ተቋማትን መፈተሽና የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል።
በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የታሪክ ቁርሾዎችን መፍታትና በሚፈጠሩ ግጭቶች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ለንግግርና ውይይት ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ይጠበቅብናል ይላሉ።
አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓታችን ጤናማ እንዲሆን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ለማኅበራዊ አንቂዎችና ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የመነጋገርና የመቻቻል ባሕላችንን በምን መልኩ ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ የሚጠቁሙት መብራቱ (ዶ/ር)፤ ሠላምን በተወሰኑ አካላት ፍላጎትና እንቅስቃሴ ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ማብራሪያ፤ የትኛውም ጥያቄ መፍትሔ ማግኘት የሚችለው በሠላማዊ ውይይትና ምክክር ነው።
ሠላም የሚረጋገጠውም በጥቂት ወገኖች ፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻዎች ትብብርና ጥረት ሲታከልበት ነው።
ስለሆነም ዘላቂ ሀገራዊ ሠላም ለማስፈን መንግሥት፣ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሕዝቡና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም