በሸገር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ115 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

ሸገር፡በሸገር ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ለ115 ሺ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ አስታወቁ።

ምክትል ከንቲባው ሰሞኑን በሸገር ከተማ እየተካሔደ ባለው የመስክ ምልከታ ላይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የሸገር ከተማ የቀጣዩ ትውልድ ከተማ በሚል የሕዝብን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄ ለመመለስ ሲባል በለውጡ መንግሥት ታቅዶ የተመሠረተ ሲሆን ከተማው አንዱ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ሲሠራ የቆየው ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም መሠረት በተያዘው በጀት ዓመት ወደ 140 ሺ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ በዘጠኝ ወር ውስጥ ለ115 ሺ ሥራ አጥ ወጣት የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።

የሥራ ዕድል ፈጠራው የሚጀምረው ከሥልጠና ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ሠልጥነው ከተደራጁ በኋላ መሥሪያ ቦታ የሚሆን ከ166 በላይ ሔክታር መሬት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። በቀጣይ ሌሎች ሼዶችም የሚያስፈልጉ በመሆናቸው በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሼዶችን በማስለቀቅና ሌሎችንም በመሥራት በጥቅሉ ወደ አንድ ሺ 200 ሼዶችን እንዳቀረቡላቸው ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የሥራ ዕድሉ የተፈጠረላቸው ወጣቶች የብድር አቅርቦት ስለሚያስፈልጋቸው በዚያ በኩል በስፋት ሲሠራበት ቆይቷል። ከብድር ጋር ተያይዞ እስካሁን በበጀት ዓመቱ ከታቀደው 400 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተመቻችቶላቸዋል።

አቶ ጉዮ፣ የሥራ አጡ ቁጥር ከፍ ያለ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ይሁንና በበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተደረገው እንቅስቃሴ የተሻለ ነው ብለዋል። እቅዱን በቀጣዮቹ ወራት በመሥራት ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑም አስረድተዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው የግብርና ተነሳሽነት ላይ ነው። እነርሱም ሲሠሩበት የቆዩት አንዱ የግብርና ተነሳሽነት ላይ ነው። ለዚህም ስኬታማነት ከአንድ ሺ 900 በላይ ክላስተሮችን እና ከሦስት ሺ 800 በላይ ሼዶችን ገንብተው ሙሉ በሙሉ ለወጣቶች ሰጥተዋል። አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች የአርሶ አደሩ ልጆች ሲሆኑ፣ ሌሎችም ወጣቶች ተካትተውበታል።

በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ሕዝቡ እያሳየ ያለው ተሳትፎ አበረታች ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ሕዝቡ በሚሠራቸው በእያንዳንዱ የልማት ሥራዎች ከጎናችን በመሆን እያገዘን ነው። ክላስተሮቹና ሼዶቹ የተሠሩትም በሕዝብ ተሳትፎም ጭምር ነው። በልማቱም ሆነ በፀጥታ ሥራው ላይ ተባባሪነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልቆ የታየበት ነው። እያደረገ ባለውና በሚያደርገውም ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ነገ ለሚደረገው የብልፅግና ጉዞም ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ በጋራ በመሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታን ለጋዜጠኞች እያስጎበኙ ይገኛሉ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You