ጥያቄዎችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሕገወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው!

በሀገሪቱ የአስተዳደር ወሰን እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ጥያቄዎች ትናንት ተነስተዋል፤ ዛሬም እየተነሱ ነው። ለጥያቄዎቹ አግባብ ባለው መንገድ፣ አግባብ ያለው መልስ መስጠት ካልተቻለ ጥያቄዎቹ ነገም ጥያቄ ሆነው መቀጠላቸው የማይቀር ነው። የግጭት እና አለመግባባት ምንጭ የመሆናቸውም አጋጣሚም የሰፋ ነው ።

ማናቸውንም ጥያቄዎችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ፣ የጥያቄዎቹን የግጭት ምንጭነት ከፍ ከማድረግ፣ በሕዝቦች መካከል ያልተገባ ቁርሾን እና የጠላትነት መንፈስን ከመፍጠር ባለፈ ዘለቂ መፍትሔ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም ።በዚህ መንገድ የተፈታ ችግርም የለም ።

ከለውጡ በፊትም ሆነ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ የአስተዳደር ወሰን እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ በሕዝበ ውሳኔ የሚፈቱበትን መንገድ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ጥያቄዎቹ ወደ ግጭት እንዳይወስዱም በብዙ ጥንቃቄ ተስተናግደዋል ።

በተለይም በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች፣ የሀገራዊ ግጭት ምንጭ እንዳይሆኑ በለውጥ ኃይሉ በኩል በገለልተኝነት፣ በሰከነ መንፈስ ለማየትና ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የተሞከረበት መንገድ፣ በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጭ እንደነበርም የሚታወስ ነው ።

ይህ ችግር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ ቀጣይና ተጨማሪ የግጭት ምንጭ እንዳይሆን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ በተደረገው የሠላም በስምምነት በቂ ትኩረት ከተሰጣቸው የስምምነቱ አካሎች አንዱ እንደነበርም ይታወቃል ።

መንግሥት በክልሎቹ መካከል ያሉ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች የሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ባካተተ መልኩ በሠላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን የመፍትሔ ሀሳብ በግልጽ አስቀምጧል። ይህም ችግሩን በመፍታት ሂደት ውስጥም ክልሎቹ የሕዝብን ፍላጎት እና ምርጫ አክብረው የሚንቀሳቀሱበትን የኃላፊነት አሠራር ያስቀመጠ ነው።

የፌዴራል መንግሥትም ችግሩን በዘላቂነት በሕዝበ ውሳኔ ለመፍታት ጥያቄ በሚነሳባቸው አከባቢዎች የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች እንዲወጡ፣ በግጭት ምክንያት ከየአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ ፣ እስከዚያም አካባቢዎቹ ከጉዳዩ ገለልተኛ በሆነው የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት እንዲጠበቅ አቅጣጫ አስቀምጧል ።

መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ፣ ጥያቄዎቹ ወደ ግጭት እንዳያመሩ ከመከላከል ባለፈ፣ ጥያቄዎቹ የሕዝብ ከመሆናቸው አኳያ ዘላቂ ሕዝባዊ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያስችል፤ በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታት እንደ አንድ ትልቅ ተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል ነው ።

ይህ በአካባቢውም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሠላም አጽንቶ ከማስቀጠል አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን የመንግሥት ውሳኔ በአግባቡ ተረድቶ ማስፈጸም፣ ከሁሉም በላይ የክልሎቹ አመራሮች ኃላፊነት ነው። ይህንን ባለማድረግ ለሚፈጠር ችግርም ቀዳሚ ተጠያቂ የሚሆኑት እነዚሁ አካላት ናቸው ።

ብዙ ወገኖቻችንን የቀጠፈ የሰሜኑ ጦርነት የፈጠረው ጠባሳ ገና ባላገገመበት፣ የብዙ እናቶች የልብ ስብራት ሰቆቃ ባልተፈወሰበት፣ ሀገር እንደሀገር ጦርነቱ በፈጠረው የኅዘን ቁዘማ ባልወጣችበት አሁናዊ እውነታ፣ ጥያቄዎችን በኃይል ለመፍታት መሞከር የተጨማሪ ሀገራዊ ስብራት ምንጭ ከመሆን ባለፈ ትርጉም ያለው መፍትሔ ሊሆን አይችልም ።

ያለንበት አሁናዊ ሀገራዊ እውነታ በጉልበት እንፈታተን የሚባልበት አይደለም፣ ይህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ እስከዛሬ ያስከፈለን ያልተገባ ዋጋ በቂ እና ከበቂ በላይ ነው። ስለሆነም በማናቸውም ሁኔታ ጥያቄዎችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት የሚጥሩ ኃይሎችን መላ ሕዝባችን በቃችሁ ሊላቸው ይገባል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You