አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ሁለት ነጥብ 16 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ኤክስፖርት ከተደረጉ የወጪ ንግድ ምርቶች ሦስት ነጥብ 14 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ሁለት ነጥብ 16 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር 69 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸርም የ164 ነጥብ 18 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አለው ብለዋል።
በስምንት ወሩ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በዋናነት ከግብርና ምርቶች ከማኑፋክቸሪንግና ከማዕድን እንዲሁም ከሌሎች ምርቶች መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።
ገቢው በምርት አይነት ሲታይ ቡና 716 ነጥብ 423 ሚሊዮን ዶላር፣ አበባ 311 ነጥብ 496 ሚሊዮን ዶላር፣ የጥራጥሬ ምርቶች 229 ነጥብ 877 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የቅባት እህሎች 225 ነጥብ 75 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ ምርቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የጫት ኬላዎች መበራከትና ተደራራቢ ታክስና ቀረጥ መኖር፣ በድርቅ ምክንያት የቁም እንስሳት አቅርቦት እጥረትና በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች፣ ኮንትሮባንድና ሕገወጥነት በስፋት ለወጪ ንግድ እቅዱ መዳከም ምክንያቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በልዩ ሁኔታ ክትትል የሚያደርግባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ ክትትል ከሚያደርግባቸው ምርቶች ወጪ ንግድ 617 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
የወልና ኢንቨስትመንት እርሻ መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ፣ የአኩሪ አተር፣ ቀይ ቦሎቄና ማሾ ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት መሻሻሉ እንዲሁም የሰሊጥ ምርት መጨመሩ በበጎነት ከታዩ ውጤታማ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን አመላክተዋል።
አዳዲስ ምርቶችን ወደ ወጪ ንግድ ሥርዓቱ ለማስገባት፣ የወጪ ንግዱ ከሕገ ወጥነት ተላቆ በሕጋዊ የአሠራር ሥርዓትና የሕግ ማዕቀፍ ብቻ እንዲመራ የማድረግ የወጪ ንግድ ምርቶችን ብዝኃነት፣ ጥራትናና መጠን የማሳደግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም