ስታርትአፕ የወጣቱ የአዲስ ሕይወት አቅጣጫ

መንግሥት በኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ላይ በተለይም የወጣቱን ሕይወት የሚቀይሩ፣ የተሻሉ አቅጣጫዎችን በመትለም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መንግሥታዊ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች መሀል ስታርትአፕ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ የቃሉ ትርጓሜ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪነት ሲሆን ማዕከል አድርጎ የሚነሳውም ወጣቱን ነው፡፡

ወጣትነትና ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ናቸው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወጣት ቁጥር ባለባቸው ሀገራት ትርጉሙ ሚዛን ደፍቶ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ይሄን አዲስ አስተሳሰብ ወደመሬት ሲያወርድ ወጣቱን ማዕከል ባደረገ እና ሀገራዊ የልማት ለውጦችን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡

ስታርትአፕ መነሻው ሃሳብ ነው መድረሻው ደግሞ ሀገርና ማህበረሰብ ነው፡፡ እኚህ የለውጥ ጥልፍልፎች ከወጣቱ የሥራ ፈጣሪነት ተነስተው በትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና ግብር ከፋይነት አልፈው ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ ትስስርን በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ለሀገር ግንባታ ምሰሶ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡

አፍሪካን ጨምሮ ብዙ የዓለም ሀገራት አሁን ላይ በዚህ ወጣት ተኮር በሆነ የሥራ ፈጣሪነት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥትም የነበሩ ለሥራ ፈጣሪዎች የማይመቹ ሕጎችን በማስተካከል ሃሳብ ላላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ምህዳርን በመፍጠር የስታርትአፖችን የለውጥ ምዕራፍ በማቀላጠፍ ላይ ይገኛል፡፡

በሃሳብ ፈጣሪነት ዳብረው ከቅርብ በመነሳት ሩቅ መድረስን አላማቸው ያደረጉ ወጣቶች ራሳቸውን ቀይረው ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት አቅጣጫ በመሆኑ አሁን ላይ እንደ አንድ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ እየተሠራበት ነው፡፡

ኢኮኖሚ ለአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሄ እውነታ አካል ለብሶ እውን የሚሆነው ደግሞ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ባሉ ለሥራ እድል መፍጠሪያ በተዘረጉ ክፍት፣ ነፃና አዋጪ መድረኮች ነው፡፡ ወጣቱን ተሳታፊ ባደረገ፣ ለላቀ ሃሳብ ቅድሚያ በሰጠ የሥራ ክህሎት ዳብሮና በልጽጎ ኢኮኖሚውን ሞተር ሆኖ የሚያሳድግ ነው።

እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋልን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ወጣቱን ባነቃ የስታርትአፕ የሥራ ፈጠራ በኩል ሀገራቸውን ከውጪው ማህበረሰብ ጋር በማስተሳሰር ተጨማሪ ገቢን እያገኙ መጥተዋል፡፡ በእኛም ሀገር እንደራይድ ያሉ የትራንስፖርት አማራጮች በወጣቱ የሥራ ፈጣሪነት የመጡ ናቸው። ከተቀጣሪነት ወደቀጣሪነት በመሸጋገር ከፍተኛ ግብር ከፋይም ናቸው፡፡

ስታርትአፕ እንደሀገር ፋይዳው ከዚህም የላቀ ነው፡፡ ከግለሰብ የሃሳብ ልህቀት ተነስቶ ዓለም አቀፋዊነትን የሚይዝ ነው፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የሚነሱት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ እንደአፕልና ማይክሮ ሶፍትን የመሳሰሉ ካምፓኒዎች ናቸው፡፡ እኚህ ካምፓኒዎች ባለቤት አላቸው፡፡ መነሻቸው ግለሰብ ሲሆን መድረሻቸው ግን ዓለም አቀፋዊነት ሆኗል፡፡

ሲነሱ በሃሳብ ሲያበቁ ደግሞ በለውጥና በላቀ ትርፍ ነው፡፡ ብልጌትም ሆነ ቤዞስ ወደዚህ ሥራ ፈጣሪነት ሲገቡ ተራማጅ በሆነ እና በማይገታ ህልም ነው፡፡ ህልማቸው ፍሬ አፍርቶ ለብዙዎቻችን እንጀራ ሆኖ በየቤታችን ገብቷል፡፡ የስታርትአፕ ጽንሰ ሃሳብም እንዲሁ ነው፡፡ ከሃሳብ መንጭቶ የሚፈስ የትጋት፣ የንቃትና የጽናት ንቅናቄ ነው፡፡

ንቅናቄው እንዳይቆምና እንዳለፈው ጊዜ ሥራ ፈጣሪዎች ተስፋ ቆርጠው ትግላቸውን እንዳይተው አሁን ላይ መንግሥት ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣ የብድር አቅርቦቶችን በማመቻቸት፣ የቦታና የንግድ ፍቃድ አሠራርን በማዘመን፣ የባለሙያ ክትትሎችን በማድረግ ወጣቱን ከህልሙ ጋር ሊያገናኝ ታጥቆ የተነሳበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ባለፈው ጊዜ የነበረው ሁኔታ ለጀማሪ ቀርቶ ለነባር ሥራ ፈጣሪዎች አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቱ ወደሥራ እንዳይገባ፣ ነባር ሥራ ፈጣሪዎች ተስፋ ቆርጠው በነበሩበት እንዲቆሙ ያስገደደ ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ተግዳሮቶች ተቀርፈው ሁሉም ነገር በተስተካከለ ምቹ ሁኔታ ላይ ባለተሰጥኦዎች መክሊታቸውን እንዲጠቀሙ መንገዶች ተከፍተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በርካታ ወጣቶች በአነስተኛና በጥቃቅን ከፍ ባለ ደረጃም ተደራጅተውና ተቧድነው የእድሉ ተጠቃሚ በመሆን ጅማሮ ላይ ናቸው፡፡ የተጀመረው የአቅጣጫ ለውጥ ለነባርና ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ተስፋን የሚሰጥ፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይም ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ በብዙዎች ተተንብየዋል፡፡

የመንግሥትን ጅማሮ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ጉልበት የሚሆኑ ቀሪ የቤት ሥራዎች ሲጠናቀቁ በኢኮኖሚ ግንባታው ላይ የተሻለ እምርታ ይኖረዋል፤ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ የተፈቀደላቸው እንደ የውጭ ሀገር ባንኮች ዓይነት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ያላቸው ተቋማት ስታርትአፕን በማበረታታት ረገድ የጎላ ሚና ሊያበረክቱ የሚችሉበትም እድል ሰፊ ነው፡፡

የሀገር ቤት ባንኮች ብድር የመስጠት ሂደት በቅድመ ሁኔታዎች የተሞሉ መሆናቸው፤ የውጭ ሀገር ባንኮች ግን ከዚህ በተሻለ መንገድ የተበዳሪውን ግለሰብ ሃሳብ፣ የሥራ ፈጣሪነት ክህሎት ታሳቢ ማድረጉ ለእስታርትአፖች እጅግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ሀገር ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ የሚሄድ የሃሳብ፣ የክዋኔ ውህድ ናት፡፡ የእያንዳንዱ ሥራ ፈጣሪ ወጣት ሃሳብ ማረፊያው ማህበረሰብ ነው። ብልጌትና ቤዞስ ከሆነች አንድ መንደር ተነስተው በሃሳባቸው በኩል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግልጋሎት እየሰጡ ነው። የእኛም ሀገር የሥራ ፈጣሪነት ጽንሰ ሃሳብ ከዚህ ተለይቶ ሊታይ አይገባም፡፡

ባለፈው ጊዜ በቢሮክራሲ ሆነ በማይመች አካሄድ መንገድ የዘጋንባቸው ሥራ ፈጣሪዎች ለሀገር የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንደከለከልናቸው ሊታሰብ ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ወጣቱ በሃሳቡ፣ በተሰጥኦው፣ በመክሊቱ፣ በእውቀቱ በተመቻቸ መንገድ ላይ ራሱን ጠቅሞ፣ ቤተሰቡን አገልግሎ ለሀገር የሚሰጥበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ስታርትአፕስ ከሥራ ፈጣሪነት እኩል ሊነሳ የሚገባው ሌላኛ መገለጫው ‹ከሥራ አጥነት ወደሥራ ፈጣሪነት፣ ከጠባቂነት ወደሰጪነት፣ ከልመና ወደልግስና፣ ከተቀጣሪነት ወደቀጣሪነት› መሸጋገር የሚለው ነው፡፡

ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በተሻሻለ ፖሊሲና ተስፋን በሚሰጥ መበረታታት አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ካላደረግን፣ በአንቂና በአብቂ ሕገ ደንቦች፣ ከጠባቂነት በሚያወጣ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳብ ስር ካልተሰለፍን፣ ከአንድ ዓይነት ልምምድ ርቀን ሥራ ፈላጊነትን ወደሥራ ፈጣሪነት የሚቀይር ማህበራዊ ንቃትን ካልፈጠርን በጀመርንው አሮጌ መንገድ ልውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ስታርትአፖች የሀገር የኢኮኖሚ ተስፋዎች እንደሆኑ በመንግሥት ታምኖበታል ይሄ እውነታ በክዋኔ ታግዞ ለውጥ ለበስ እንዲሆን የሁላችንም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል።

አንድ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ሥራ ፈጥሮ ሲሰራ በስሩ ምን ያክል ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድር አስበንዋል? አንድ ግለሰብ በተመቻቸ ፖሊሲና በተቃና መንገድ ላይ ራሱን ሲያቆም በስሩ ምን ያክል ነፍሶችን እንደሚያስጠልል ገብቶናል? ይሄ ተራ የሚመስል ግን ደግሞ እንደ አንድ ሰፊና ግዙፍ ሀገር፣ ብዙሃኑ ወጣት እንደሆነባት ሀገርና ከድህነት ለመውጣት እንደሚታትር ማህበረሰብ ተቀዳሚ ጥያቄ ነው፡፡ የአንድ ሥራ ፈጣሪ መነሳት የብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች ተስፋ መጀመሪያ ነው፡፡ አንዱ አንዱን ይዞ እየተነሳ ሲሄድ ይሄ ነው ሀገራዊ ለውጥ ማለት፡፡ ይሄ ነው የኢኮኖሚ ግንባታ የሚባለው፡፡

በተመረቅን ማግስት ብዙዎቻችን የትምህርት ማስረጃችንን ይዘን እንዲቀጥረን የምንሄድበት ድርጅት የሃሳብ ውጤት ነው፡፡ ለብዙዎቻችን እንጀራ የሆኑ ተቋማት በሃሳብ የበለጸጉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ የእስታርትአፕ ዋነኛ አላማም ይሄ ነው፡፡ ትውልዱ ሥራ ፈጣሪ ሆኖ ከተረጂነት እንዲወጣ፣ አቅሙን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና እውቀቱን በሀገር ግንባታ ላይ እንዲያውል አቅም የሚፈጥር አስተሳሰብ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የሥራ አጥ ቁጥር ጨመረ ብለን ስናወራ ቀዳማይ መነሻችን ሊሆን የሚችለው የሥራ ፈጣሪዎች አለመኖር ነው፡፡ ሥራ ፈጣሪዎች አሉ ማለት የሥራ አጥ ቁጥር አይኖርም አሊያም ይቀንሳል። አሁን ላይ እንደሀገር የደረሰብን የኢኮኖሚ ድቀት፣ የድህነት መስፋፋት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ማጣት እንዲሁም የጠባቂነት ልክፍት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ካልሆነ ሁኔታዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡

ስታርትአፕስ የኢኮኖሚ ሞተር ነው ካልን ሥራ ፈጣሪዎች በብዛትና በጥራት ሊኖሩን ይገባል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በሌሉበት ሁኔታ ስታርትአፕ የኢኮኖሚ ሞተር መሆን አይችልም፡፡ የጀመርናቸው ወጣት ተኮር የልህቀት ጅማሬዎች ሰፍተውና ገዝፈው ከድህነት እንደሚታደጉን እሙን ነው፡፡ ከልመና ወደልግስና በምናደርገው ግስጋሴም የራሳቸውን በጎ ዐሻራ አሳርፈው እንደሚታዩ ይታመናል፡፡

የለውጥ ቀስቱ ከግለሰብ ወደማህበረሰብ ነው፡፡ ማህበረሰብ እንዲለወጥ የግለሰብ ለውጥ ቀዳሚው ነው፡፡ ግለሰብ እንዲለወጥ ደግሞ እንደስታርትአፕ ያሉ የሥራ ፈጣሪ ምቹ መድረኮች እንዲበዙ ግድ ይላል፡፡ ይሄ እንዲሆን ምቹ ፖሊሲ፣ ምቹ ሁኔታ ወሳኝነት አለው፡፡ በለመድነውና ለማንም ምቹ ባልሆኑ መንገዶች ላይ ተጉዘን ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ነባር አስተሳሰቦቻችን መቀየር፣ ሳር ያላበቀሉ ኮቴዎቻችንን መለወጥ ያስፈልገናል፡፡

ፈረንጆች “ከፍጥነት አቅጣጫ ይበልጣል” ይላሉ፡፡ የቱንም ያክል ብንፈጥን የአቅጣጫ ለውጥ ካላደረግን ትርጉም የለውም፡፡ መንግሥት በጀት በመመደብ፣ ምቹ ምህዳርን በመፍጠር የአቅጣጫ ለውጥ አድርጓል፡፡ ሌሎች የተሻለ እምርታን ሊያመጡ ለሚችሉ ሁኔታዎች ካሉም ያንን በማድረግ ወጣቱን የሥራ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ ቆርጫለሁ ብሏል፡፡ ከየትኛውም ሥራ ፈጣሪ ወጣት ጎን በመሆን አጋርነቱን ለማሳየትም ቃሉን ሰጥቷል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶች የአቅጣጫ ለውጦች ናቸው ከነባሩ ልምምድ አርቀው አዲስ ተሃድሶን የሚያጎናጽፉን፡፡

ለዚህ የተለያዩ የግልና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እድገት በህብረት እንደሚመጣ ሁሉ የወጣቱ የነገ ተስፋም በሁላችንም ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፡፡ በተለይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የመንግሥትን የአቅጣጫ ለውጥ በመከተል የሥራ ፈጣሪዎችን ጉዳይ እንደተቀዳሚ የቤት ሥራው ወስዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ድረስ ላሉ ሥራ ፈጣሪዎች ፖሊሲ ከመቅረጽ ጀምሮ የትኛውንም አስፈላጊ ግልጋሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

መጪውን ጊዜ እንዲህ ባሉ በተሻሉና ለውጥ ተኮር በሆኑ እንቅስቃሴዎች መቃኘት እንደ ሀገር የማደጋችን፣ እንደ ማህበረሰብ ደግሞ ከተረጂነት የምንላቀቅባቸው አጋጣሚዎች መሆን ይችላሉ። ዓለም በሃሳብ ነው የተቀየረችው፣ ሃሳባውያን ሃሳባቸውን ወደተግባር እንዲቀይሩ መንገድ ጠራጊ ሥርዓት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በስታርትአፖች የሥራ ፈጣሪነት ሀገራችን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንደምትገባ እምነቴ ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You