አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደክልሉ ገብቷል

አዲስ አበባ፡- ለዘንድሮ የምርት ዘመን አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 100 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፋይሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት የምርት ዘመን አምስት ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል።

በዘንድሮ ዓመት ለበልግና ለመኸር ምርቶች ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት መታቀዱን አስታውሰዋል።

የግዢ ሂደቱ በግብርና ሚኒስቴር በኩል የሚፈጸም እንደመሆኑ ለኦሮሚያ ክልልም የሚያስፈልገው ቀርቧል፤ በዚህም እስካሁን አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ገብቷል ብለዋል።

እንደ አቶ በሪሶ ገለጻ፤ ወደ ክልሉ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው በማኅበራት በኩል ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል።

ከክልሉ ስፋት አንጻር የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ በቂ ባይሆንም የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ሥራም ተሠርቷል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሁለም ወረዳዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚያዘጋጁበት ማዕከል መቋቋሙን አንስተው፤ እስካሁን ድረስም 100 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ኮምፖስት በክልሉ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም እንደአፈሩ ይዘት ቢለያይም ከውጭ ከሚመጣው የተሻለ ጥቅም ይሰጣል ያሉት አቶ በሪሶ፤ በቀጣይነት የኬሚካል ይዘት ያላቸውን የአፈር ማዳበሪያዎች መጠን በመቀነስ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከመጠቀም አንጻር ለአርሶ አደሮች መድረኮችን በማዘጋጀት ሆነ በተገኙ አጋጣሚዎች የግንዛቤ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም በየወረዳው ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ጋር እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

እንደአጠቃላይ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱ በስፋት የሚከናወንበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ በሪሶ፤ የማዳበሪያ ስርጭቱን እስከሚያዚያ ወር መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እቅድ መቀመጡን ጠቁመዋል። ለዚህም ከማኅበራትና በየደረጃው ከሚገኙ የግብርና አመራሮች ጋር እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በኤክስቴንሽን ተጠቃሚ የሆኑ አርሶአደሮች ቁጥር ከዚህ በፊት በተሠራ መረጃ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ነበሩ ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል። የኤክስቴንሽን ተጠቃሚ የሆኑ አርሶአደሮች በሙሉ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።

አቶ በሪሶ እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ የማዳበሪያ ንግድና እንቅስቃሴን ለመከላከል የአርሶ አደሩን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያመጣና የከፈለበትን የባንክ ደረሰኝ እንዲያስገባ ይደረጋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You