እንዴት ናችሁ ልጆችዬ? ሳምንቱን ትምህርታችሁን በሚገባ በመከታተል እንዳሳለፋችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ ዛሬ የእረፍት ቀናችሁ ነው አይደል? የዛሬዋን ቀን በማንበብ፣ በጥናትና በጨዋታ እንደምታሳልፋ ተስፋ አደርጋለሁ። ለዛሬ ምን ልናቀረብንላችሁ የፈለግን ይመስላችኋል? በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ልጆችን በማነጋገር ለእናንተ ያስተላለፉትን ቆንጆ ምክር ነው እሺ ልጆች።
ተማሪ በአምላክ አለማየሁ ትባላለች:: በመጀመሪያው መንፈቅ አመት በትምህርቷ ሁለተኛ ነው የወጣችው:: ወደፊት ሳይንቲስትና መምህር መሆን ትፈልጋለች:: ሳይቲስት ሆና ሀገሯን የማገልገል ህልምም አላት። የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ባላት የትርፍ ጊዜ መሞከር ያስደስታታል።
መምህር መሆን የፈለገችበት ምክንያት ደግሞ ፍትህንና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ለማስማር እንደሚቻል በማሰብ ነው። ታዲያ ልጆችዬ ተማሪ ባምላክ ይህን ፍላጎቷን ለማሳካት በርትታ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።
ሰብሪን ነቢል ደግሞ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደፊት ትምህርቷን ጨርሳ ዶክተር መሆን ትፈልጋለች:: የሚወልዱ እናቶችን የማገልገል ሃሳብም አላት:: ልጆችዬ ሃሳቧ እንዲሳካለት ሰበሪን ዘወትር ታነባለች፣ ታጠናለች፣ ያልገባትንም መምህሮቿን ትጠይቃለች:: ሰብሪን ለሌሎች ተማሪዎች የምታስተላልፈው መልዕክት አላት:: መልዕክቷ ምን መሰላችሁ? ትምህርታችሁን በደንብ ተከታተሉ፣ ወላጆቻችሁ የሚሏችሁን ነገር ስሟቸው፣ ታዘዟችው፣ አክብሯቸው የሚል ነው:: ልጆችዬ ጥሩ መልዕክት ነው አይደል? በሚገባ እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ።
በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት በትምህርቷ አንደኛ የወጣችውን ተማሪ እናስተዋውቃችሁ:: ስሟ አርሴማ ወርቅነህ ይባላል:: የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: በርትታ በማጥናቷና በትኩረት በማንበቧ በትምህርቷ አንደኛ መውጣት ችላለች:: አርሴማ ተጠቀመችበት የራሷ የሆነ የአጠናን ስልት ውጤታማ አድርጓታል:: ሌሎች ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በትኩረት ትምህርታቸውን ቢከታተሉ፣ቢያጠኑና በትኩረት ቢያነቡ እንደእሷ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ትናገራለች:: ጨዋታ መቀነስ እንዳለባቸውም ትመክራለች:: ወላጆችም ልጆቻቸውን መደገፍ እንዳለባቸው ትናገራለች:: ለወደፊት ሳይንቲስት የመሆን ፍላጎት ያላት አርሴማ ተመራማሪ ሆና ሀገሯን የማስጠራት ፍላጎት አላት::
ሌላኛዋን ተማሪ ደግሞ እናስተዋውቃችሁ። ተማሪ ልያት ሙለቀን አራተኝ ክፍል ናት:: እድሜዋ አስር ነው:: ከዚህ ቀደም በትምህርቷ ስምንተኛ ነበር የወጣችው:: አሁን ደግሞ ስድተኛ ወጥታለች:: ልያት ደረጃዋን ያሻሻለችው በርትታ በማጥናቷ እና በትኩረት በማንበቧ እንዲሁም የእናቷን ምክር በመስማቷ፣ከጎበዝ ልጆች ጋር በጋራ በመረዳዳቷ ነው:: ከዚህ የበለጠ በማጥናት ዶክተር የመሆን ፍላጎትም አላት::
ተማሪ ልያት ለልጆች የምለው አለኝ ትላለች:: ልጆች እንደ ጌም እና ቴሌቪዥን ያሉ ነገሮች ትኩረታቸውን እንደሚስብ ባውቅም እንደማይጠቅማቸው በመገንዘብ ትምህርታቸው ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው ትላለች:: እርሷ በሳይንስና ቴክሎጂ ክበብ በተጨማሪ በግብረ ገብ ክበብ በንቃት ትሳተፋለች:: በነዚህ ክበባት በመሳተፏ ብዙ ጥቅም አግኝታበታለች:: በሳይንስና ቴክኖሎጂው ስለሳይንስ ብዙ እንድታውቅ ረድቷታል:: በግብረ ገብ ክበብ በማሳተፏ ደግሞ ሥነ ሥርዓት መልካም ስነ ምግባር ተምሬበታለሁ ትላለች::
ሌላኛው ጎበዝ ተማሪ ሄኖክ ቀጸላ ይባላል። የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በትምህርቱ አንደኛ የወጣ ጎበዝ ተማሪ ነው። ልጆችዬ እናንተ ልምድ እንድትቀስሙ በማሰብ እንዴት አንደኛ ወጣህ ብለን ጠይቅነው። ምላሹም ምን መሰላችሁ? ክፍል ውስጥ በሚገባ ትምህርቱን በመከታተሉ፣ከትምህርት ቤት ሲመለስም በማጥናቱና ፈተና ሲደርስ ደግሞ በሚገባ በመዘጋጀቱ እንደሆነ ይናገራል። ለወደፊት ሳይንቲስት የመሆን ፍላጎት ያለው ሲሆን የሕዋ ምርምሮችን በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ያልማል። ሌሎች ተማሪዎችም እንደርሱ ጎበዝ እንዲሆኑ በርትተው እንዲያጠኑና ጨዋታ እንዳያበዙ ይመክራል። የእርሱ ወላጆች እንደሚደግፉት የሚናገረው ጎበዙ ተማሪ ሄኖክ ወላጆች ልጆቻቸውን መደገፍ እንዳለባቸው ይመክራል።
ልጆችዬ የጎበዝ ተማሪዎችን መልዕክት እንዴት አገኛችሁት? ምንስ ተማራችሁ? “በርትተን ማጥናት እንዳለብን፣በክፍል ውስጥ በንቃት መከታተል እንዳለብን፣ጨዋታ አለማብዛት፣ያልገባንን መጠየቅ እንዳለብን፣የወላጆቻችንን እና የመምህሮቻችን እገዛ ማግኘት እንዳለብን በሚገባ ተምረናል” የሚል ምላሽ እንደምትሰጡ እናምናለን:: ልጆችዬ መልካም የእረፍት ቀን እንዲሆንላችሁ እንመኛለን:: ሳምንት እስከምንገናኝ ሰላም!!
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም