ሄዶ ከኮሪያ ዘማች ሲመለስ
ያወሳል ናፍቆቱን በክራሩ ድምጽ
ብሏል ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ):: ‹‹የኮሪያ ዘማች›› የሚለው ቃል በትልልቅ አዛውንቶች ዛሬ ድረስ ይነገራል:: በወቅቱ የ7 ዓመት ልጅ የነበረ እና ዛሬ የ80 ዓመት አዛውንት የሆነ ሰው ክስተቱን ያስታውሳል ማለት ነው:: በኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ታሪክ ውስጥ ተደጋግሞ ስሙ ይነሳል:: በታሪክ ሰነዶችና በታሪክ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በዜናዎችና ትንታኔዎችም የዲፕሎማሲ ቋንቋ ጭምር ሆኖ ያገለግላል:: ይህ የኢትዮጵያውያን የኮሪያ ዘመች ታሪክ ነው::
በዚህ ሳምንት ከምናስታውሳቸው የታሪክ ክስተቶች አንዱ ከ73 ዓመታት በፊት የተከሰተው የኮሪያ ዘማች ታሪክ ነው:: የኮሪያ ዘማች ትውስታ ባለክራሩን የሙዚቃ አርበኛ ካሳ ተሰማን አስከትሎ ወደ ኮሪያ የሄደው የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ነው:: በስሙ የተሰየመ ፓርክ አፍንጮ በር አጠገብ እንዳለ ልብ ይሏል::
የኮሪያ ዘመቻ ከሚያዚያ 8 ቀን 1943 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ሳምንት የተከናወነ ነበር:: 2 ሺህ 168 ወታደር ያሰለፈው የኢትዮጵያ የክቡር ዘበኛ ሠራዊት፣ ቃኘው የሻለቃ ጦር ወደ ኮሪያ ዘመተ። ከዘማቾቹ መካከል አንዱ የነበረው ‹‹የክራሩ ጌታ›› 50 አለቃ ካሣ ተሰማ ይገኝበታል:: ‹‹እልም አለ ባቡሩ›› በሚለው ዘፈኑም ክስተቱን ለታሪክ አስቀምጦታል::
የመጀመሪያው ዙር የኮሪያ ዘማቾች አንድ ሺህ 153 ሲሆኑ፤ ቀኑ ግን በትክክል አልተገለጸም:: አብዛኞቹ መረጃዎች የሚያሳዩት በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ መሆኑን ነው:: የኢትዮጵያ ፕሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከአምስት ዓመት በፊት በሰራው ዘገባ መጋቢት 30 የሚል አለው:: ምናልባት እሱ የመጀመሪያው ከሆነ የሚያዝያ ስምንትና ዘጠኝ አካባቢ ያለው ሁለተኛው ዙር ይሆናል ማለት ነው:: ያም ሆነ ይህ የኮሪያ ዘማቾች በዚህ ሳምንት ይታወሳል ማለት ነው::
የኮሪያ ዘማች እና ከኮሪያ ዘማቾች ማህበር መሥራች አንዱ የሆኑት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፣ በተመሳሳይ ከዘማቾች አንዱ የሆኑት አስር አለቃ ዘነበወርቅ በላይነህ የኮሪያ ዘማቾች 60ኛ ዓመት ሲከበር ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር::
ዘማቾቹ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ዘመቻው በአምስት ዙር ነበር:: በአጠቃላይ ከስድስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የዘመቱ ሲሆን 122 የሚሆኑት ተሰውተዋል:: ከኢትዮጵያ ወታደሮች አንድም የተማረከ አልነበረም፤ ‹‹ሬሳ እንኳን አልተማረከብንም›› ይላሉ ዘማቾቹ::
በ2005 ዓ.ም የኮሪያ ጦርነት 60ኛ ዓመት ሲዘከር ዓለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ‹‹ኢትዮጵያዊው ጀግና በኮሪያ ጦርነት›› በሚል ርዕስ የኮሪያ ዘማች ስለነበሩት ሌተናል ማሞ ሀብተወልድ ሰፊ ሐተታ አስነብቧል:: በዚህም የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ለዓለም አሳውቋል:: የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ሐተታ የመግቢያው ጽሑፍ ደመቅ (Bold) ተደርጎ እንዲህ ተጽፏል::
‹‹ከ60 ዓመታት በፊት፤ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ነበረች:: ጦርነቱ አፍሪካ ውስጥ እንዳይመስላችሁ! ይልቁንም በሺዎች የሚቆጠር ማይል ርቀት ላይ ኮሪያ ውስጥ ነው…›› እያለ ይቀጥላል::
ቢቢሲ በዚያው ሐተታው እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያውያን በኮሪያ 253 ውጊያዎችን (battles) አድርገዋል:: ‹‹በጦር ሜዳ እጅ አንሰጥም!›› የሚል መሪ ቃል ነበራቸው:: መሪ ቃላቸውንም በተግባር አሳይተዋል::
እነሆ ኢትዮጵያም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ሰላም በማስከበር እንድትታወቅ አደረጋት:: እነዚህ የኮሪያ ዘማች ጀግኖችም ሲታወሱ ይኖራሉ::
በልደቱም፣ በሞቱም፣ በዘፈኑም የበዓል አድማቂው የሙዚቃ ንጉሥ
የዚህ ሰው ነገር ይገርማል! ከውልደቱ ይጀምራል:: የተወለደው በዕለተ መስቀል መስከረም 17 ቀን ነው:: ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደግሞ የፋሲካ በዓል ዕለት ሚያዚያ 11 ቀን ነው:: የዚያን ዓመት የፋሲካ በዓል በሀዘን ድባብ የተዋጠ እንዲሆን አድርጎታል:: በዘፈኑ ደግሞ በዓላትን ሲያደምቅ ኖሯል:: በሕያው ሥራው የወደፊት በዓላትንም ያደምቃል:: ይህ ሰው የሙዚቃው ንጉሥ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ነው::
ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከ15 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በፋሲካ በዓል ዕለት ነው:: የፋሲካ በዓል ቀኑ ስለሚቀያየር በየዓመቱ ሚያዚያ 11 አይሆንም:: የ2001 ዓ.ም የፋሲካ በዓል የተከበረው በጥላሁን ገሠሠ ሞት ሀዘን ነው:: ያም ሆኖ ግን የጀግና ሞት ሀዘን አይደለምና መገናኛ ብዙኃንን ለአንድ ሳምንት ያህል በአንድ ጉዳይ ብቻ አድምቆ ይዞ ቆይቷል:: ሥርዓተ ቀብሩም የተፈጸመው ለሳምንት ያህል ሰፊ ሽፋን ከተሰጠው በኋላ ነው::
የ15ኛ ዓመት የጥላሁን ገሠሠን የሙት ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ከሕይወትና ሥራዎቹ ጥቂቶችን እናስታውስ::
ጥላሁን ገሠሠ ከእናቱ ከወይዘሮ ጌጤ ጉሩሙ እና ከአባቱ ከአቶ ገሠሠ ንጉሤ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጠመንጃ ያዥ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የመስቀል ዕለት ተወለደ። ዕድሜው 14 ዓመት እንደሆነ ከአያቱ ጋር እንዲኖር ወደ ወሊሶ ተወሰደ፤ ራስ ጎበና በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ጀመረ።
በትምህርት ቤት ሳለ፤ ጥላሁን ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍቅር እያሳየ መጣ። አያቱ ግን ትኩረቱን በሙሉ በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ይመክሩት ነበር። የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ የነበሩት ሱዳናዊው አቶ ሼዳድ ደግሞ የጥላሁንን የሙዚቃ ፍቅር በማየት ወደ ሱዳን እንዲሄድና በዚያም ሙዚቃ እንዲያጠና ይመክሩት ነበር። ጥላሁን ወደ ሱዳን ባይሄድም ምክራቸውን ግን ትልቅ ቦታ ሰጥቶት ነበር።
ከሀገር ፍቅር ቲያትር ንጋትዋ ከልካይ እና ኢዮኤል ዮሐንስ ሌሎችም የሀገር ፍቅር ተዋንያን በትምህርት ቤታቸው ትርኢት ሊያሳዩ በመጡ ጊዜ፤ ይህን እድል በመጠቀም ጥላሁን ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር ኢዮኤል ጋር ባደረገው ውይይት በሙዚቃ መግፋት ከፈለገ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለበት መከሩት። ጥላሁን ትምህርቱን አቋርጦ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አቀና። ኩብለላውን በእግር የጀመረው ለአያቱ ሳይነግር ስለነበር ከቤት ሲጠፋ አያቱ ለአጎቱ ሁኔታውን በመንገር ጥላሁንን ይጠብቁ ጀመር። ጥላሁንም የአሥራ አምስት ኪሎ ሜትር መንገዱን ጨርሶ ቱሉ ቦሎ ደረሰ፤ ከዚያም ከአክስቱ ከወይዘሮ ተመኔ ባንቱ ቤት አድሮ ወደመጣበት ወደ ወሊሶ አያቱ ዘንድ ተይዞ ተመለሰ ።
በሙዚቃ ፍቅር በጣም የተቃጠለው ጥላሁን አያቱ ቤት አንድ ቀን ብቻ በማደር ጉዞውን እንደገና ወደ አዲስ አበባ አቀና፤ በዚህ ጊዜ ግን በጭነት መኪና ላይ በመንጠልጠል ነበር። ጥላሁን አዲስ አበባ እንደገባ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ። በዚያም ጥቂት አመታት ከሰራ በኋላ ወደ ክብር ዘበኛ ባንድ በመቀላቀል እነሆ ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን በቃ።
በ1953 ዓ.ም የታኅሳስ ግርግር ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር ። ለጥቂት ጊዜም ታስሮ ተፈቷል። ከዚያም ወደ ቀድሞው ሀገር ፍቅር በመመለስ ተወዳጅና ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤትን በጎበኙበት ጊዜ ሦስት ጊዜ ወጥቶ ዘፍኗል፤ ንጉሠ ነገሥቱም ‹‹ጥሩ ድምጽ አለህ፤ እንዳታበላሸው›› የሚል አስተያየትም እንደሰጡት ይነገራል ።
ከጥላሁን ዘፈኖች አብዛኞቹ የአማርኛ ሲሆኑ፤ የተወሰኑ ዘፈኖችን ደግሞ በኦሮምኛ እና በሱዳንኛ ዘፍኗል። ጥላሁን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቶታል:: ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና የብዙኃን መገናኛ ሽልማት ድርጅት የሙሉ ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል::
ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ
ይህ ነው የሞትኩለት የኔ ማስታወሻ።
ውበቷን ሳሞግስ የለምለም ሀገሬን
ማንም አይዘነጋም በጩኸት መኖሬን!
ዜማ እንጉርጉሮዬም የግሌ ቅላጼ
ተቀርጾ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ።
ያስቀየምኩት ቢኖር የጠላኝ በቁሜ
ድምጼን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አጽሜ።
እኔን ለበደሉኝ ሰርዣለሁ ቂሜን
በኔም የከፋችሁ ይቅር በሉት አጽሜን!
ስንዱ ገብሩ
ሌላኛዋ የዚህ ሳምንት ክስተት ስንዱ ገብሩ ናት:: ከ15 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም (ጥላሁን ገሠሠ ባረፈ በነጋታው ማለት ነው) ታዋቂዋ አርበኛ እና ደራሲ ስንዱ ገብሩ አረፈች:: የዚያን ዓመት ፋሲካ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን ያስተናገደ ነበር ማለት ይቻላል:: ለብዙ ሴቶች አርዓያ የሆነችውን ስንዱ ገብሩ ታሪክም በጥቂቱ እናስታውስ::
የክብር ዶክተር የሆኑት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ የተወለዱት ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም በቀድሞው አጠራር በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ አለም ከተማ ነው:: አባታቸውም ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ናቸው::
ስንዱ እድሜአቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት ከቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህርት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተምረዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።
አባታቸው ከንቲባ ገብሩ፤ ስንዱን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጋር እንዳስተዋወቋቸው ስለ ስንዱ የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ:: አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ ሀገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ በ1921 ዓ.ም ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በመጨረሻም በስዊስ እና በፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዚያው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
የጣሊያን ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝብን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ አማክረው በተሰጣቸው 500 ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በጣልያን ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸው የቁም እስረኛ ሆነዋል።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ ወይዘሮ ስንዱ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብ ‹‹አዚናራ›› ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ።
ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥምና ወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ ‹‹ኮከብ ያለው ያበራል ገና››፣ ‹‹የየካቲት ቀኖች››፣ ‹‹የኑሮ ስህተት›› የሚሉ ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።
ወይዘሮ ስንዱ ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና ‹‹የወንድ ዓለም›› በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።
ስንዱ ገብሩ ከተሳተፉባቸው ጥቂቶችን እንጥቀስ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ ሆነው አገልግለዋል::
ከመጽሐፎቻቸው ደግሞ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ::
ኮከብህ ያውና ያበራል ገና፣ በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች (1947 ዓ.ም)፣ የታደለች ህልም (1948 ዓ.ም)፣ ርእስ የሌለው ትዳር (1948 ዓ.ም)፣ የኔሮ ስህተት (1948 ዓ.ም)፣ ከማይጨው መልስ (1949 ዓ.ም)፣ ፊታውራሪ ረታ አዳሙ (1949 ዓ.ም) እና የመሳሰሉት ሌሎች ጽሑፎቻቸው ይጠቀሳሉ::
የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግና እና ፀረ ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ (የክቡር ዶክተር) ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተዋል:: ሥርዓተ ቀብራቸውም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም