በቀጣናው ጂኦፖለቲካ ላይ ህያው አሻራውን ትቶ ያለፈው ሾተላዩ ሰላይ

ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በFB መንደር ስባዝን አንድ መርዶ ተመለከትሁ። መቼም በዚህ መንደር የታየው ሁሉ አይታመንም። ለማረጋገጥ ወደ አንድ አብሮ አደጌና ጓደኛዬ ሀሎ አልሁ። በማለዳው ስለተመለከትሁት መርዶ ሳረዳው እሱም እንደኔ ደንግጦ አለመስማቱን ነግሮኝ አጣርቼ ልደውልልህ ብሎኝ ተለያየን። እኔም መርዶውን ሟርት ያድርገው ብዬ እየተመኘሁ ወደ FB መንደር ተመልሰሁ። መርዶውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች በስፋት እየተዘዋወሩ ስለሆነ ምኞቴ ከንቱ መቅረቱን ተረዳሁ።

ያ ልጆች ሆነን ፍኖተ ሰላም ላይ ጀብዱን ጉብዝናውና ትህትናው እንደ ዳዊት ተደጋግሞ እየሰማን ያሳደገን አርዓያችን፣ዝነኛችን/ሌጀንዳሪ/እና ምሳሌያችን የሆነው አምባሳደር ኮሎኔል አስማማው ቀለሙ 60 ዓመታትን ሌት ተቀን በታማኝነት በፍጹም ፍቅር ያገለገላትንና የሚወዳትን ሀገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለይቷታል። አሁንም ያየሁትን ማመን ቢቸግረኝ ወደ 8ኛ ክፍል የእንግሊዘኛ መምህሬ ጋሽ ዘላለም ልየው(Phd)ሀሎ አልሁ ገና ሀሎ ሲለኝ ያ የምሥራቅ አፍሪካን ጂኦፖለቲካ እንደ አዲስ የበየነው ሾተላዩ ሰላይ ማረፉ ታወቀኝ።

እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ የአምባሳደር ኮሎኔል አስማማው ሞት በመደበኛው ሚዲያ በሰበር ሊነገር የሚገባው ነበር። በሞቱ አዘንሁ። መልሼ ደግሞ ተጽናናሁ። ለሀገሩና ለወገኑ ባበረከተው ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ስራው ስሙን ከመቃብር በላይ ከፍ አድርጎ ስለሰቀለው አልሞተም ብዬ ተጽናናሁ።ጋሼ ፕሮፌሰር ዘላለም ልየው ደግሞ ሀገር ግዙፍ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጽሐፍት አጣች ሲል ቁጭቱን ገለጸልኝ። እውነት ነው። አምባሳደር የቀጣናው ድክመት እንበለው ህመም መፍትሔ አልያም ፈውስ በእጁ ነበር። በልኩ ሳንጠቀምበት አመለጠን እንጂ።

አምባሳደር ኮሎኔል አስማማው ዝናን ያተረፈ/ሌጀንደሪ/ቢሆን ሲበዛ ትሁትና ቅን ነበር። ጓደኛዬ አዳሙ አንለይ ነው ሀዋሳ ላይ ከ20 ዓመት በፊት ከአምባሳደር ጋር ያስተዋወቀኝ። በእርግጥ ኮሎኔል አስማማው በአካል ባላውቀውም በስምና በዝና አውቀው ነበር። ሀዋሳ ላይ ስተዋወቀው ግን ያን ሁሉ ገድልና ዝና ተሸክሞ ግን ሲበዛ ትሁት ሆኖ ስመለከተው ለራሴ ገረመኝ። እንደገና እንደ አዲስ አከበርሁት። የታላቁ ዲፕሎማትና የደህንነት ሰው ታሪክ ዳጎስ ዳጎስ ያሉ መጽሐፍት ቢወጣውም ፤ ከተለያዩ ምንጮች የቀራረምሁትን ነው እያጋራኋችሁ ያለሁት። ቤተሰቦቹ አልያም የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወይም የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ኮሎኔል አስማማው የህይወት ታሪክ እና ሀገራዊ አስተዋጾዎችን በመጽሐፍ መልክ ሰንደው ለትውልድም ለታሪክም ያቆዩታል ብዬ አምናለሁ።

ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን ሌት ተቀን ይሰራ የነበረውን የሳያድባሬን መንግሥት በመጣልና ሀገሪቱ ዛሬ ድረስ እንዳትረጋጋ ያደረገውን እርሾ በመጣል ፤ሱዳን ሻእቢያንና ወያኔን በማስታጠቅ ሀገራችንን እንዳዳከመችው ሁሉ ፤ ብድር በምድር እንዲሉ የደቡብ ሱዳንን አማጽያን በማደራጀትና በማሰልጠን እንዲገነጠሉ በማድረግና ሱዳንን በማዳከም ኮሎኔል አስማማው የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። በድህረ ደርግ የሽግግር መንግስቱ ከገዛ ዜጋው ይልቅ ለሶማሊያ ተቆርቁሮ ሶማሊያን በመበተን እና የሶማሊያን ሕዝብ በማጎሳቆል ወንጅሎ ለ12 ዓመታት አስሮታል። በወቅቱ ይህ ውንጀላ ብዙ ያወዛግብና ያነጋግር ነበር።

በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ ፍኖተ ሰላም ከተማ የተወለደው ዶ/ር አስማማው ቀለሙ የአርበኛ ቤተሰብ ልጅ መሆኑን ይናገራል:: አያቱ ፊታውራሪ ዓለማየሁ ኦጋዴን መሞታቸውን፣ አባቱ በጣሊያን ወረራ ተምጫ ሸለቆ ሦስት ሺህ ጦር ይዘው ከጠላት ጋር የተዋጉ አርበኛ እንደነበሩ ያስረዳል:: ‹‹አባታችን የቤተክህነት ትምህርት ስለነበረው ከገጠር ወደ ከተማ ገብተው በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ማገልገል ሲጀምሩ እኛም ተማርን:: ከስምንት ልጆች አሁን የቀረነው አራት ነን፣ ሆኖም ሁላችንም በትምህርት ብዙ ገፍተናል:: በቤተሰባችን ብዙ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች አሉ፤››በማለት ስለቤተሰቡ ያወጋል::

አምባሳደር ኮሎኔል አስማማውን ያወቀ ሁሉ በአፍታ ስለሚቀራረብ ከቤተሰቡ እንደ አንዱ ስለሚቆጠር ነው እስካሁን አንተ ያልሁት። እሱም የሚወደው ስለነበር። በተረፈ በእድሜም ሆነ ለሀገር በዋለው ውለታ አንቱ ቢባል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ማግኘቱን፣ ማኔጅመንት ተምሮ በዲግሪ መመረቁን፣ ወደ እስራኤል አቅንቶ በሪሶርስ አሎኬሽን ዘርፍ ከቤንጎሪዮን ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መከታተሉንና በኢንተርናሽናል ሎው ሌላ የማስተርስ ዲግሪ መቀበሉን ይገልጻል::

በሆርቲካልቸር ቢኤስሲ ዲግሪ፣ ከዚያም ወደ ቡልጋሪያ በማምራት ከካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪውን ሠርቷል:: ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የፖስት ዶክቶራል ፕሮግራም መከታተሉን፣ ከቀለም ትምህርቱ እኩል በወታደራዊ ሳይንስ ዘርፍም ብዙ ዓይነት ትምህርቶች መቅሰሙን ይናገራል:: በፖሊስ ሳይንስ በአድቫንስድ ዲፕሎማ በመጀመሪያ መመረቁንና የፖሊስ መኮንን ለመሆን መብቃቱን ያወሳል::

በትምህርት ላይ ትምህርት፣ በማዕረግ ላይ ማዕረግ እያከለ በሒደት እስከ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሰው አንጋፋው ምሁር ወደ ደኅንነት ተቋምም ገብቶ በብዙ የኃላፊነት ደረጃዎች መሥራቱን አስረድቷል:: ‹‹የደኅንነቱን ዕቅድ (ፕላኒንግ) ዘርፍ መርቻለሁ፣ የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ተሰማርቻለሁ፣ በምክትል ሚኒስትርነትም አገልግያለሁ፤›› ይላል። ለሦስት ዓመታት በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበር:: ስታር አምባሳደር ከመባል ባለፈ በሶማሊያ የተማረኩ የኢትዮጵያ ዜጎችን በልዩ ኦፕሬሽን ለማስለቀቅ የተወጣው የስድስት ወራት ዘመቻ ለብቻው ረጅም ታሪክ ያለው ነው ሲልም ይደመጣል:: በሌሎች ሀገሮችም ልዩ የስለላ ተልዕኮዎችን ሲወጣ መቆየቱን፣ በሀገር ጉዳይና በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ ያካበተው ዕውቀት ሰፊ መሆኑንም ይጠቅሳል::

የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ›› በተሰኘው ግዙፍ መጽሐፋቸው ስለ ኮሎኔል አስማማው ሰብእና እንዲህ ከትበዋል:: ‹‹በጣም ጎበዝ፣ ታታሪ፣ አዲስ ሃሳብ አፍላቂ ብቻ ሳይሆን ወዲያው በተግባር የሚተረጉም እንደሆነ አስመስክሯል:: ሠርቶ አይደክመውም:: በጣም ትጉ ነው:: በዚህም ምክንያት አለቆቹ ያደንቁታል:: በመሆኑም መንግሥቱ ሳይቀር አውቆታል::

አምባሳደር የኮሎኔል አስማማውን የሶማሊያ አምባሳደር እንዲሆኑ ማሰባቸውን ለርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲነግሯቸው “ጥሩ ምርጫ ነው::” በጣም ጎበዝ ልጅ ነው:: ማደግ የሚገባው ልጅ ነው:: ለእርሱ ተብሎ ሳይሆን ለሥራው:: ምንም ሥራ ይሰጠው ከሚጠበቀው በላይ ነው የሚፈጽመው:: እኔ እንኳን ለሌላ ሥራ ነው አስቤው የነበረው:: ጓድ ተስፋዬን የሚተካ እሱ እንዲሆን ነው…:: ብለዋቸዋል::

የአምባሳደር የኮሎኔል አስማማው ጠንቃቃነት የሚያሳይ አንድ ሰበዝንም ኮሎኔል ብርሃኑ እንዲህ መዘዋል:: ‹‹የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሆንኩ ዶክተር አስማማው ወደ ቢሮዬ ብቅ ብሎ ነበር:: በወቅቱ አንዲት የኤሌክትሪክ መሣሪያ ይዞ ነበር:: ትንሽ እንደተነጋገርን የቢሮዬ ግድግዳ ጣሪያ በመሣሪያዋ መረመረው:: የተደበቀ የድምፅ መቅረጫ ወይም ሌላ ነገር አለመኖሩን ለማረጋገጥ:: ፍተሻውን ሲጨርስ፤ ‹ምንም ነገር የለም ነፃ ነው፤› አለኝ:: እኔ ሳልጠይቀው ራሱ አስቦ የምናገረው፣ የምወያየው የምወስነው የምሰጠው ትዕዛዝ በሌላ እጅ እንዳይወድቅ፤ ምናልባትም በጠላት ሰላዮች እጅ እንዳይወድቅ ይኽን በማድረጉ ውለታውን አልረሳውም::››

በኢትዮጵያ ሦስት መንግሥታት ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በፖሊስ፣ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ሀገራዊና ሙያዊ አገልግሎትን አስማምተው ለስድስት አሠርታት ያክል ሠርተዋል ይለናል የአማርኛው ሪፖርተር በማስከተል:: ሀገራዊ የደኅንነቱን ዕቅድ (ፕላኒንግ) ዘርፍን በመምራት፣ ድንበር ተሻጋሪ የኦፕሬሸን ሥራዎች ላይ በመሰማራትም ተጠቃሽ ናቸው:: የፖሊስ ኮሎኔሉ አስማማው ቀለሙ:: በቀለሙም (በአካዴሚያ) እስከ ዱክትርና ዘልቀዋል::

ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ በንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከሀገር ግዛት ሚኒስቴር እስከ ዘመነ ደርግ (ኢሕዲሪ) ከደኅንነት ሚኒስቴር ቀጥሎም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ምክትል ሚኒስትርነት የደረሰው የኮሎኔል አስማማው አገልግሎት፣ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የታወቀ ነው ሲል ጋዜጠኛ ሔኖክ በሪፖርተር ባስነበበን መጣጥፍ ይዘክራል::

በ1960ዎቹ መጨረሻና በ70ዎቹ መጀመሪያ ከሶማሊያ ጋር በነበረው ጦርነት የተማረኩ ኢትዮጵያውያንን በልዩ ኦፕሬሽን ለማስለቀቅ የተወጡት የስድስት ወራት ዘመቻ ስማቸውን በግዙፍ ያነሳዋል:: በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላም ከሰፈነ በኋላ፣ ቀደም ሲል ‹‹ፔድሮ›› ተብለው በሞዛምቢካዊ ጋዜጠኛነት በሰለሏት ሶማሊያ የመጀመሪያው ባለሙሉሥልጣን አምባሳደርነት አገልግለዋል::

የኢትዮጵያ አብዮት እንደፈነዳ (1966) የፖሊስ መቶ አለቃ ሆነው በሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ ውስጥ የሠሩት አምባሳደር ኮሎኔል አስማማው ፤ የፖሊስ ሳይንስን የተማሩት በአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በ9ኛው ኮርስ ሲሆን፤ በመቶ አለቅነት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተመረቁት ታኅሣሥ 14 ቀን 1961 ዓ.ም. ነበር:: የመረጃና ደኅንነት ሙያን በይበልጥ ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ በተለያዩ ሀገሮች በተለይም በእስራኤልና በጀርመን ሠልጥነዋል::

ሁለንተናዊ ዕውቀታቸውን ለትውልዱ ለማስረፅም ይረዳ ዘንድ የኮተቤ የደኅንነት ትምህርት ቤትን በመመሥረትና በኃላፊነት በመምራት ከመሥራታቸው በተጨማሪ በ1974 ዓ.ም. የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይወሳል:: ድኅረ ደርግ በሽግግር መንግሥቱ (በኋላ ኢፌዴሪ) ለ12 ዓመታት ያለክስ፣ ያለፍርድ የታሰሩት ኮሎኔል አስማማው፣ እስረኞች እንዲማሩ፣ ትምህርቱም በዚያው እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ይገለጻል:: የ2010 ዓ.ም ለውጥን ተከትሎ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተጋባዥ ሌክቸረርም ነበሩ::

የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ የቆዩት አምባሳደር ኮሎኔል አስማማው፤ በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ያረፉት ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን ነው:: ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ የሐዘን መግለጫውን ያስተላለፈው የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት፣ ኮሎኔል አስማማው ቀለሙ ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በማስጠበቅ ለ60 ዓመታት ያህል በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ሰፊ አበርክቶት አድርገዋል ብሏል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም በተጋባዥ መምህርነት (ገስት ሌክቸረር) ያገለገሉት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ኅልፈትን ተከትሎ ተቋሙ ለሪፖርተር በላከው መግለጫው እንዲህ አለ፡- ‹‹አምባሳደር ዶ/ር አስማማው ቀለሙን ቀርቦ ከሕይወትና ከሥራ ልምዳቸው ለመማር በሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም የምንገኝ መምህራን የወሰንነው የአቶ በላይ ገብረ ጻድቅ መጽሐፍ (‹‹የመረጃና ደኅንነት ሙያና የኢትዮጵያ ገጽታ››) በ2014 በተመረቀበት ዕለት ነው::

በዝግጅቱ ላይ የነበሩት የሥራ ጓዶቻቸው ሲያመሰግኗቸውና ሲያሞኳሿቸው ስናይ በፊትም ከምናውቀው በላይ ለሙያቸው የተሰጡና በዚህም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ገባን:: ‹‹ከስልክና የመጀመሪያ የዝግጅት ውይይቶች በኋላ በአራት ወራት ውስጥ ለ17 ቀናት ከ1፡30 እስከ 2፡00 ሰዓት የፈጁ ቃለ መጠይቆች አድርገንላቸዋል:: በኋላም ለድኅረ ምረቃ ተማሪዎቻችን ገስት ሌክቸረር ሆነው አገልግለዋል:: በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተገኘበት ፐብሊክ ሌክቸር አዘጋጅተንላቸዋል::

ከዚህ ሁሉ ምን ተማርን ምንስ አገኘን ከተባለ አንድ፦ ከልጅነት እስከ እስር ቤት የዘለቀ አዲስ ነገር ለመማር ለመፍጠርና ቁልፍ ተግባሮችን ለመሥራት በጥናትና ሙከራ ላይ የተመሠረተ መጋፈጥና በግል ተነሳሽነት ታላላቅ ሃሳቦችን መጀመርና ለፍሬ ማብቃት፤ሁለት፦ሀገርን ከምንም ነገር አስቀድመው በሙያቸው ያካበቱትን ያላቸውን ሁሉ መስጠትና ማገልገል፤ሶስት፦ በጣም ውሱን የሆነ የሀብት መሠረትና ያልተመቻቸ ሁኔታ ላይ ሆኖም ቢሆን ተቋም መገንባትና ማጠናከር ላይ ትኩረት መስጠት፤አራት፦ የመንፈስ ጥንካሬ፣ ያልተገባ እስር (12 ዓመት) ከምቾት ወጥቶ ተራ ሰው መሆን፣ በስተእርጅና ጤና ማጣት ሳይበግራቸው ሁሌም ማንበብ፣ መማርና እስከ መጨረሻው ቀናት ለሀገር መስጠትን ተምረናል።››

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You