ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና የዜጎች አንድነትና ትብብር ዋነኛው መሣሪያ ነው:: ሀገር በሁሉም ነገር አድጋና ዘምና፣ ዓለም የደረሰበትን የሥልጣኔ ማማ መቆናጠጥ የምትችለው በሁሉም ዜጎች ፍላጎትና ጥረት መሆኑ አያጠያይቅም:: ብዙኃኑ የሚያልሙትና የሚመኙትን እድገትና ብልፅግና ለማምጣት ብዙ እንቅፋቶችን አልፎ እና በመተባበር አንድ ላይ ቆሞ መገኘት ደግሞ ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም::
እንደ ሀገር የእድገትና ሥልጣኔ ማማውን ልንቆናጠጥ የምንችለው ጠንክሮ በመሥራትና የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች በትብብር ክንድ ነቅለን በመጣል ነው:: ለዚህም የሠለጠነ ማኅበረሰብና በኢኮኖሚ የበለፀገችን ሀገር እውን ለማድረግ ዛሬ ላይ የሚታዩትን ፈተናዎችን ብስለት በተሞላበትና በአንድነት መሻገር ዋናውና አስፈላጊው ጉዳይ ነው::
ለዚህም ትልቅ ማሳያ ሊሆነን የሚችለው የተጋረጡብንን ችግሮች አልፈን የነገ እድገትና ሥልጣኔ ተስፋችን የሆነው የዓባይ ግድብን እውን ማድረጋችን ነው:: ግድቡ በ2003 ዓ.ም በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ሥራው ብዙ ፈተናዎች ተሻግሮ የአስራ ሦስት ዓመት ልደቱን ሻማ ለኩሷል::
የዓባይ ውሃ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ እንዳለፉት ዘመናት ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› አይደለም:: የሚታይ የሚጨበጥ የመጪው ትውልድ ጭምር አንጡራ ሀብት ሆናል:: እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ግን ያለፈባቸው ፈተናዎች፣ የተሻገራቸው እንቅፋቶች ጥቂት አይደሉም:: ፈተናው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ገንብታ ዜጎቿን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት ስትወጥን ከሚያስፈልገው ገንዘብ ይጀምራል::
የወንዙን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የማይፈልጉና የኢትዮጵያ እድገትና ሥልጣኔ የሚያንገበግባቸው ሀገራትም ግንባታው ቀድሞ እንዳይጀመር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንጮችን ጠርንፎ በመያዝ እንዲዘገይ የሚችሉትን ብቻ ሳይሆን የማይችሉትንም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: እነዚህን ግዙፍ ፈተናዎች ግን ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በአንድነትና በተባበረ ክንድ ቆመው ባደረጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ግድቡን በማይታመን መልኩ ለማጠናቀቅ ተቃርበዋል::
የቀደመው ትውልድ የራሱን ጥረት ቢያደርግም በነበረው ትልቅ ሴራ ግድቡ እንኳን ሊሠራ ሊታሰብ የማይቻል ይመስል ነበር:: ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን ግን የገንዘቡም ምንጭ፣ የምሕንድስናውም ሊቆች ራሳቸው ሆነው ግንባታውን በማስጀመር ለፍፃሜ አድርሰውታል:: የገንዘቡ ምንጭ እራሱ የሀገሬው ዜጋ በመሆን እያንዳንዱ ሰው አቅሙ በፈቀደ መጠን በማዋጣት ግድቡ አሁን ከደረሰበት ከፍታ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል::
ኢትዮጵያውያን በመተባበር ዳግማዊ ዓድዋን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ተራሮች መሐል ለዘመናት ላይነቀል ሊተክሉ ችለዋል:: ይሄም እያስተማረን የሚገኘው ኢትዮጵያውያን በትብብርና በአንድነት ከቆሙ የበለፀገች ሀገርን መፍጠር እንደማይሳናቸው ነው::
የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ በብዙ ደረጃዎች ከፍ የሚያደርግና የኢትዮጵያውያን ሕይወት ለመሆን ቢቀርብም በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎ የምርቃት ባነሩን ለመቁረጥ እና የመላው ኢትዮጵያውያን የደስታ ምንጭ ሊሆን ጥቂት ነገሮች ቀርተውታል:: እስከ አሁን የተጓዘችባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችንም በትልቅ ድል በመወጣት ከአፍሪካ አልፎ በዓለም ደረጃ ታላቅ መሆናችንን የምናሳይበት ቀን እሩቅ አይሆንም::
ይህም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙና በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ ሃሳብን በማዋጣት የሀገራቸው ግንባታ ላይ ካተኮሩ ዓለም የደረሰበት የሥልጣኔና የኢኮኖሚ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ነው:: ይህ በዓባይ ግድብ ላይ የታየው አንድነትና መተባበር በሌሎች ዘርፎችም ሊደገም ከቻለ የበለፀገች እና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሀገርን መፍጠር እንደሚችሉ ማሳያ ነው::
የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የታየው ትብብርና ፈተናን የማሸነፍ ፅናት እንዲሁ ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም:: ከዚህ ትልቅ ትምህርት ሊወሰድ ይገባል:: ካለፈተና የሚመጣ ውጤት አይኖርም:: ችግር ትልቅ ትምህርትንና መፍትሔን የሚሰጥ የመማሪያ መድረክም ነው:: ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረግና ወደፊት ለሚገጥሙን ችግሮችና እንቅፋቶች እንደየሁኔታው በቂ መፍትሔን መስጠትና በአሸናፊነት መወጣትን የምንማርበት ድል ሊሆን ይገባል::
የሚገጥሙንን እንቅፋቶች እንደመልካም አጋጣሚ መመልከት ነገ የሚገጥሙንንን ፈተናዎች ሳንሸበርና ሳንደናገጥ ተባብረን ለመሻገር ትልቅ የመንፈስ ስንቅ ይሆነናል:: አሁን ለገጠሙን እና እየገጠሙን ለሚገኙት የሠላም እጦት ድህነት እና ሌሎች ሀገራዊ ችግሮቻችንን አልፈን የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከዓባይ ግድብ ስኬታችን በላይ ምሳሌና አስተማሪ የለም::
በመሆኑም ግድቡ ተሻግሮ የመጣቸውን ተቆጥሮ የማያልቁ ችግሮችን እንደ ትምህርት በመውሰድ እና ችግሮችን ወደ ድል በመቀየር የምንመኛትን የበለጸገች አገር ለመፍጠር በሁሉም ዘርፎች በጋራ መቆምና መተባበር ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም ሊለየን ይገባም:: አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት ተስፋ የተጣለባቸውን እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሉት ተቋማት የጀመሩትን ሥራ ከስኬት እንዲያደርሱ፣ የመተባበር አድማሳችንን በማጉላት ረገድ የሚጫወቱት ሚና የጎላ ነው::
እንደዚህ ዓይነት ተቋማትን በማብዛት የሃሳብ ልዕልና የሚያሸንፍበት ባሕል የምንገነባ ከሆነ የትብብር መንፈስን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንችላለን:: ሕዝብ ከተባበረ እና በአንድነት ከቆመ ሀገራችን በአጭር ጊዜ አድጋ ማየት እንችላለን::
በዓባይ ግድብ ዙሪያ የተጋረጠብንን ችግርና ፈተና የተጋፈጥንበትን የትብብር መንፈስ በመከተል እና በሌሎች ዘርፎች ድልን በመቀዳጀት ለመጪው ትውልድ የምትመች ሀገር ማስረከብ ትልቁ የቤት ሥራችንም ሊሆን ይገባል:: ሁላችንም እንደየእውቀታችንና ሙያችን በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የተቻለንን ጥረት ማድረግ ይገባል::
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን የሀገሬውን ብሂል በመከተል ችግሮችን የሚያሸንፍ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል:: እነዚህን ለውጦች ለማምጣት ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውም ጥያቄ አብሮ መነሳት ይኖርበታል::
ለመተባበሩና በአንድነት ለመቆሙ መጀመሪያ መቅደም የሚኖርበት የኔ ድርሻ ምንድ ነው? የሚለውን ነገር ለይተን ስናውቅ ነው:: ሁሉም ለትብብሩ የአቅሙን የሚያዋጣውም ከዚህ ተነስቶ ይሆናል:: ለዚህም በማደግ ላይ ከሚገኙትና ካደጉት ሀገራት ልምድ በመውሰድ ለሀገር እድገትና ብልፅግና የድርሻችንን ማዋጣት ይኖርብናል::
ኢትዮጵያ ሠላም እና ፍትሕ የሰፈነባት ሀገር፣ በቴክኖሎጂ የበለፀገች፣ ዜጎቿ ከድህነት አረንቋ ተላቀው የሚኖሩበት ሀገር እንድትሆን በዓባይ ግድብ የታየው ትብብር እንዲደገም በየዘርፉ ባለን ሙያ የበኩላችንን ሚና ልንጫወት ይገባል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም