ሕጋዊነትን በመምረጥ ራስንም፣ ቤተሰብንም ካላስፈላጊ መከራና ስቃይ መታደግ ይገባል!

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። በችግሩ ዙሪያ ዜጎች ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር ባለመቻላቸው አሁንም ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በመሆኑም ተገቢውን ግንዛቤ ማዳበር እስካልቻልን በቀጣይም የሀገር ፈተና ሆኖ መዝለቁ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

ምክንያቱም በግጭቶች፣ በኑሮ ውድነት፤ ለራስ እና ለቤተሰብ የተሻለ ሕይወትን ከመሻት በሚመነጭ ጉጉት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ተታለው ድንበር ተሻግረው የሚሰደዱ ዜጎቻችን ቁጥር ዕለት ዕለት እየጨመረ ነው።

ይህ የሀገርን ክብር፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ችግር ውስጥ እየከተተ ያለ ዓለም አቀፍ ችግር በእኛ ሀገር መስተዋል ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት ውስጥም በሕገወጥ ደላሎች ተወናብደው በረሀ የበላቸው፣ የባሕር ሲሳይ የሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም ።

በአደባባይ በጽንፈኞች ሰለባ የሆኑ፣ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ የገቡ፤ ባልተገባ መልኩ ለእስርና እንግልት እንዲሁም ለግዞት የሚዳረጉ ዜጎቻችንን ቁጥርም ቢሆን በየእለቱ እያሸቀበ እንጂ እየቀነሰ ያለበት ሁኔታ አይስተዋልም ።

በተለይም ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ ወዳሉ ሀገራት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚሰደዱ ዜጎቻችን፣ መንገዳቸው ሕጋዊነት የተላበሰ ካለመሆኑ በተጨማሪ፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ባለመሆን ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ተገድደዋል።

ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚደረግ የሰዎች ድንበር ዘለል እንቅስቃሴ /የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት/ የተለመደ እና ዓለም አቀፍ ባሕሪ የተላበሰ ነው። በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ዜጎች የተለመደ እና በመንግሥት ደረጃም የሚበረታታ ነው። ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትም ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።

ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በሀገራት መንግሥታት መካከል በሚደረግ ሕጋዊ ስምምነት የሚመራ፤ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ለሚፈልሱ ሰዎች መሻት ስኬት መተማመኛ እና ማስተማመኛ ያለው ነው። እነዚህን ሰዎች ካላስፈላጊ እንግልት ፣ መከራ እና ስቃይ የሚታደግ ጭምር ነው።

ከሕጋዊነት ባለፈም ሥራ ፈላጊዎች ስለሚሄዱበት አካባቢ የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው፤ በሚሄዱባቸው አካባቢ ካሉ ሕዝቦች ባሕል፣ ሃይማኖት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ጋር የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው ።

የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ድንበር የሚሻገሩ ሰዎች ለሚሄዱባቸው አካባቢዎች ባይተዋር ሳይሆን፤ ፈጥነው ራሳቸውን ከአካባቢው ጋር እንዲያላምዱ የሚያስችል፣ በተሻለ እውቀት እና ክህሎት ተደግፈው ከድንበር ባሻገር ያለውን ተስፋቸውን የሚጨብጡበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።

እነዚህ ሀገራት በዚህ መልኩ ለሥራ ከሚያሰማሯቸው ዜጎቻቸው ብዙ ቢሊዮን ዶላር እያገኙም ነው። አጋጣሚውን ለዜጎቻቸው የሕይወት ለውጥ እንደ አንድ ትልቅ እድል አድርገው በመውሰድ፣ ዕድሉን በአግባብ ለመጠቀም ተቀናጅተው በመሥራት ውጤታማ ሆነዋል።

በኛ ሀገር ያለው እውነታ ግን በዚህ ደረጃ የሚገለጽ አይደለም። ዜጎች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለያዩ ወቅቶች ፤ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፤ ጥረቶቹ በሚመለከታቸው አካላት ቅንጅት ማነስና እና በሕዝቡ ውስጥ ባለው የግንዛቤ እጥረት የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።

በተለይም በሀገራችን ዘርፉ በአብዛኛው በሕገወጥ ደላሎች የሚዘወር መሆኑ፤ ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየሰፋ ሄዷል ። በዚህም ዜጎቻችን ላልተገባ መከራ እና ስቃይ፤ ሞት እና የጤና ችግሮች እየተዳረጉ ነው። ችግሩ እንደ ሀገርም እየፈጠረ ያለው ስብራት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።

ዜጎቻችን የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚያደርጉት ፍልሰት በመንገድ ከሚደርስባቸው እንግልት ባለፈ፤ በደረሱባቸው ሀገራት በሕገወጥ መንገድ መገኘታቸው፤ እንዲሁም ለአካባቢ ሕዝቦች ባሕል፣ ሃይማኖት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ባይተዋር መሆናቸው ለተጨማሪ ችግሮች ዳርገዋቸዋል ።

ይህንን ሀገራዊ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት መንግሥት ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚደረግ የዜጎችን ፍልሰትን ሕጋዊ ወደ ሆነ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመለወጥ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው። በተለይም ጉዳዩን አስመልክቶ ከመካከለኛናው ምስራቅ ሀገራት ጋር እያደረገ ያለው ውይይትና ውይይቶቹን ተከትሎ እየተደረሰባቸው ያሉ ስምምቶች የሚበረታቱ ናቸው።

ስምምነቶቹ ሕገወጥ ደላሎችን ከዘርፉ በማስወጣት፣ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪቶች ሕጋዊ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር፤ ዜጎች የተስፋቸው ባለቤት እንዲሆኑ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከዚያም አልፈው ሀገራቸውን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን ዕድልም የሚፈጥር ነው ።

ይህንን አሁናዊ እውነታ በአግባቡ በመረዳት ዜጎች ለሕልማቸው ስኬት፤ ሕጋዊ የሆነውን መንገድ በመከተል ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ሕገወጥነት ሊያስከትል ከሚችለው መከራ እና ስቃይ እንዲሁም አላስፈላጊ እንግልት መታደግ ይጠበቅባቸዋል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You