
አዲስ አበባ፡– ስለኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት የሚሰጠው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ችግሮች ከመባባሳቸው በፊት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
በጤና ሚኒስትር የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑ ቆይቷል።
ለዚህም መንግሥት የተለያዩ በሀገር ውስጥ ባለ ድርሻ አካላትንና ኅብረተሰቡን እንዲሁም ተራድዖ ድርጅቶችን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በእነዚህ ተግባራት አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ በመቻሉ የስርጭቱን መጠን ከአንድ በመቶ በታች ለማድረስ ችሏል ብለዋል።
ነገር ግን በ2030 በታቀደው እቅድና ለዓለም መንግሥታትም በተገባው ቃል መሠረት የማኅበረሰብ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ የማድረሱን ሥራ፤ ማለትም የሞትና በአዲስ መያዝን ዝቅ እናደርጋለን የሚለውን ለማሳካት አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ይህን ለማሳካት በተሠሩ ሥራዎች ቫይረሱ በደማቸው ያሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሕመም ሲሰቃዩና ሲቸገሩ ወይንም በፍጥነት ሲሞቱ አይታይም ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ማግለልና አድልዎም በጥሩ ሁኔታ ሊስተካከል በመቻሉ እንደማንኛውም ዜጋ አምራች እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። የቫይረሱን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታም በበቂ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት መቻሉ ቫይረሱ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዳይፈራ አድርጎታል ብለዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ለውጦች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መዘናጋትን ፈጥረዋል ያሉት ኃላፊው፤ የሚዲያዎች ተሳትፎም ተቀዛቅዟል ሲሉ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ኤች አይ ቪ ቫይረስን በተመለከተ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ትኩረት የሚሹና በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። እነዚህም ሴተኛ አዳሪዎች፣ አደንዛዥ እፅ የሚጠቀሙ ሰዎች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ አፍላ ወጣቶች በተለይ (ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ)፣ የቀን ሠራተኞች፣ ከማኅበራዊ ችግሮች ጋር ተያይዞ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የስርጭት መጠኑ ከአንድ በመቶ በላይ ቢሆንም ከቦታ ቦታ በፆታ፣ በኅብረተሰብ ክፍል፣ በገጠርና በከተማ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በከተሞች ያለው ስርጭት በገጠር ካለው በሰባት እጥፍ እንደሚበልጥም ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ልዩነት መሠረት ያደረገ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመጠጥ፣ የጫት ቤቶችና በሺሻ ቤቶች መስፋፋትም ሌላ ተግዳሮቶች እየሆኑ መጥተዋል። አንዳንድ ወጣት ሴቶች ከቫይረሱ በላይ እርግዝናን ይፈራሉ። የወጣቶች አዲስ የመያዝ ምጣኔ ጨመረ ባይባልም እየቀነሰ አይደለም፤ ይህ በራሱ ችግር ለመኖሩ አመላካች ነው ብለዋል።
ይህም በተለይ በወጣቶች በኩል ሁሉን አቀፍ ሥራ ባለመሠራቱ ዋጋ ሊያስከፍሉን የሚችሉ አጋላጭ ባሕሪያት እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በመሆኑም የኤች አይ ቪ ቫይረስን በተመለከተ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሀገር ማከናወን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም