በአማራ ክልል ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው

– በመጪው የመኸር ወቅት 169 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፦ በአማራ ክልል ለመጪው የመኸር ወቅት ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ክልሉ በመኸር ወቅት ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙንም ተጠቁሟል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ቢሮው ለመጪው የመኸር ወቅት በግብዓትነት እንዲውል ግዢ ከፈጸመው ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው።

እስከ አሁን ከአንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ደርሷል።

ቢሮው የ2016/2017 የመኸር ምርት የሰብል ልማት ከአምናው የተሻሻሉ አሠራሮችን በመተግበር የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ነው ያሉት ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር)፤ ይህም የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና ለእርሻ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከወዲሁ በማቅረብ ነው ብለዋል።

በባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት በክልሉ 145 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ያሉት ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር)፤ ዘንድሮ ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው። ይህም የ24 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ያለው ሲሆን በሄክታር 63 ሺህ ነው ብለዋል።

ለዚህም የልማት ንቅናቄዎችን የማከናወን፣ ግብዓቶችን በፍጥነት የማቅረብ፣ የኩታ ገጠም አሠራርን የማጠናከር፣ ለባለሙያዎች ቴክኒካል ሥልጠና የመስጠት እና አርሶ አደሩ የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ተደርጓል ያሉት ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የአንደኛ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ የእርሻ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር የእርሻ ሥራ ሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት የታረሰ ሲሆን በሁለተኛ ዙር የእርሻ ሥራ አንድ ሚሊዮን 255 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሷል ያሉት ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር)፤ በሦስተኛ ዙር የእርሻ ሥራ 435 ሺህ 200 ሄክታር መሬት መታረሱን ነው የገለጹት።

እንደ ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር) ገለፃ፤ አምና ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የዋጋ፣ የእጥረትና መሰል ችግሮች ተከስተዋል። ዘንድሮ ከአምናው በመማር ከስምንት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ተገዝቷል። ይህም አምና ከተገዛው ጋር ሲነፃጸር ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጭማሪ አለው።

ይህም ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ይገኛል። እስከ አሁን ከአንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ያሉት ማንደፍሮ አስናቀ (ዶ/ር)፤ ለመኸር ወቅት ከ185 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You