የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ዛሬ ይጀምራሉ

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በአሜሪካዋ ዩጂን በኢትዮጵያዊቷ እንቁ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ደምቆ የተጠናቀቀው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የ2024 የውድድር ዘመኑን ዛሬ አንድ ብሎ ይጀምራል። በዚህም መሠረት በ2024 በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ የመም እና የሜዳ ተግባራት የአንድ ቀን ውድድሮች ዛሬ በቻይና ዚመን መካሄድ ይጀምራሉ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በሦስት የመድረኩ የተለያዩ ርቀቶች ለማሸነፍ ይሮጣሉ።

ውድድሩ ዛሬ በቻይናዋ ዚመን ከተማ መካሄድ የሚጀመር ሲሆን የዛሬ ሳምንት በሻንጋይ ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል። ኢትዮጵያውያኑ ከሚጠበቁባቸው ርቀቶች አንዱ የሆነው የወንዶች 5ሺ ሜትር፣ አምስት አትሌቶች ፉክክሩን በድል ለመጀመር ከኬንያውያን ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል።

ከነዚህም መካከል የለንደን እና የዶሃ የዓለም ሻምፒዮናዎች ባለድሉ አትሌት ሙክታር እድሪስ አንዱ ነው። አትሌቱ ርቀቱ 12፡54.3 በመሮጥ የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት መሆኑ ይታወሳል። ከእሱ የበለጣ ፈጣን ሰዓት ያላቸው የሀገሩ ልጅ ንብረት መላክ እና ኬንያዊው ኪፕኮር ኒኮላስ ብቻ ናቸው። ኬንያዊው አትሌት 12፡46.33 ፈጣን ሰዓት ያለው ሲሆን ንብረት ደግሞ 12፡54.22 በሆነ ሰዓት ይከተላል። ባላቸው ፈጣን የግል ሰዓት ምክንያት እነዚህ አትሌቶች ለአሸናፊነት ቅድሚያ ግምትን ይወስዳሉ። ይሁኔ አዲሱ፣ ለሜቻ ግርማ እና ግርማ ኩማ ሌሎች ጥሩ ሰዓት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

የ1500 ሺ ሜትር ሴቶች ሌላው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበትና ለአሸናፊነት የሚጠበቁበት ርቀት ሲሆን 9 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተፎካካሪ ይሆናሉ። ከነዚህም መካከል ስድስቱ አትሌቶች ርቀቱን ከ 4 ደቂቃ በታች ሮጠዋል። ድሪቤ ወልተጂ ርቀቱን 3፡53.93 በመሮጥ ቀዳሚ ስትሆን የ2023 ዩጂን ዳይመንድ ሊግ አሸናፊና የክብረወሰን ባለቤት ጉዳፍ ፀጋይ 3፡54.01 ሮጣለች። ብርቄ ኃየሎም፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ወርቅነሽ መሰለ እና አክሱማይት አምባዬ ርቀቱን በጥሩ የግል ሰዓት ማጠናቀቅ የቻሉ ናቸው።

ኬንያዊቷ የርቀቱ ፈርጥ ፌዬዝ ኪፕየጎን በውድድሩ አለመሳተፏ የፉክክሩን ደረጃ በጥቂቱም ቢሆን ይቀንሳል ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮጵያውያኑ ኮከቦች ከሌሎች የርቀቱ አትሌቶች ጋር የሚያደርጉት ፉክክር አጓጊ ነው። በዚህም የዓለም ሻምፒዮናዋ ጉዳፍ ፀጋይ፣ የማይል ውድድር ክብረወሰን ባለቤት ድርቤ ወልተጂ እና የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናዋ ፍሬወይኒ ኃይሉ የሚያደርጉት ፍልሚያ የዓለምን ቀልብ መሳብ ችሏል።

በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች በሚካሄደው ውድድር ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። በርቀቱ አትሌት ሲንቦ ዓለማሁ፣ ፍሬሕይወት ገሰሰ እና ሎሚ ሙለታ ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር ይፎካከራሉ።

ወጣቷ አትሌት ሲምቦ ዓለማሁ በ2022 የዓለም ከ18 ዓመት በታች ውድድር 9፡18.98 ሰዓትን በመሮጥ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን አሻሽላለች። በዚህም መድረክ ከሁለት ዓመት በፊት ሮጣ 9፡21.10 መግባት ችላለች። በአምናው ውድድር ተሳትፋም 9፡05.83 በመሮጥ የራሷን ምርጥ የግል ሰዓት አስመዝግባለች።

እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ዓመታት ሁሉ አትሌቶች በ14 ተከታታይ የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ ከተሞች ነጥብ ለመሰብሰብ የሚፎካከሩ ሲሆን በእያንዳንዱ ርቀት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት አትሌቶች በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ለዳይመንድ ሊግ የፍጻሜ ውድድር የሚፋለሙ ይሆናል። ቀጣዮቹ ውድድሮች በዶሃ፣ ራባት እና ዩጂን ከተደረጉ በኋላ፣ ተከታዮቹ ወደ ኦስሎ እና ስቶክሆልም በግንቦት መጨረሻ እና ሰኔ መጀመሪያ ላይ ተካሂደው ወደ አውሮፓ ትልልቅ ከተሞች ያቀናሉ።

በሐምሌ ወር በፓሪስ፣ ሞናኮ እና ለንደን የሚደረጉ ውድድሮች ለአትሌቶች ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ እንዲዘጋጁ እድል ይሰጣቸዋል። ከኦሊምፒክ በኋላ እአአ ከመስከረም 13 እስከ 14 ባለው ጊዜ ውስጥ የውድድር ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት በሉዛን፣ ሲሌሲያ፣ ሮም እና ዙሪች ነጥቦችን ለማግኘት አራት ተጨማሪ ውድድሮች ይካሄዳሉ። እ.ኤ.አ. ከ2019 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድር ወደ ቤልጂየም ብራስልስ ሲመለስ፣ ከመስከረም 13-14 ባለው ቀን ውስጥ 32ቱ የዳይመንድ ሊግ ቻምፒዮኖች በመጨረሻው ሳምንት ውድድር የሚለዩ ይሆናል።

በውድድሩ 8 አትሌቶች እንደየደረጃቸው ነጥብ በመሰብሰብ ለዓመቱ መጨረሻ የፍጻሜ ውድድር ለማለፍ የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል አስደናቂ እንደሚሆን ይጠበቃል። አትሌቶች በሴቶችና ወንዶች በ16 የአትሌቲክስ ውድድሮች በማሸነፍ ለውድድሩ የተዘጋጀውን የዳይመንድ ዋንጫ እና 30 ሺ የአሜሪካን ዶላር ሽልማትን የግላቸው ለማድረግ ይፋለማሉ።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You