የኮሪደር ልማቱንም በግዙፍ ፕሮጀክቶች የግንባታ ፍጥነት

ከተሞች የአንድ ሀገር የእድገት ደረጃ የት እንደደረሰ በአጭር ጊዜ ጉብኝት ብቻ መግለጽ የሚቻልባቸው፣ የሀገሮች የእድገታቸው፣ የብልጽግናቸው፣ የኢኮኖሚያቸው መሻሻል፣ የፖለቲካቸው እሳቤ እድገታቸውና የማህበራዊ ስልጣኔያቸው መገለጫ ተደርገውም እንደሚወሰዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው የኮሪደር ልማትም ኢትዮጵያን የምትገልጽ ከተማ መገንባትን ያለመ ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን እንደ ስሟ ውብና አዲስ ማድረግን፣ ከአፍሪካ ዋና ዋና ከተሞች ተርታ እንድትሰልፍ ማድረግን እንዲሁም ከተማዋ ባለፉት አመታት የገነባቻቸውን ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ማገናኘትም ያለመ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ሀገር የነበረው የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጥሩ አልነበረም፤ የግንባታ ፕሮጀክቶች በእጅጉ ሲጓተቱ ቆይተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የፕሮጀክቶች ሀብት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ሆኖ ቆይቷል።

በሀገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ግን እነዚህን ችግሮች ማስቀረት እየተቻለ ሲሆን፣ አሁን እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ፍጥነትም የዚሁ ለውጥ ሌላው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም አዲስና መልካም ባህል እየተገነባ ነውና። የዚህ ፕሮጀክት ግንባታም በፍጥነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ ከተማን ለኑሮ የተመቸች ማድረግን እንዲሁም አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሰራ ይገኛል። የከተማ አስተዳደሩም በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ለማገናኘት የሚያስችሉ አምስት የኮሪደር ልማቶችን በማስጠናት ወደ ኮሪደር ልማቱ ሥራ ገብቶ ልማቱን እያካሄደ ይገኛል። እነዚህ ስራዎች የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም እና የውሃና የፍሳሽ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ የሚከናወኑ ግንባታዎች ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የከተማዋን እንግዶችና ጎብኚዎችንም ለማስናገድ ብቃት እንዲኖራቸው ተደርገው እየተገነቡ ናቸው።

የኮሪደር ልማቱን አላማ፣ በልማቱ የተካተቱ አካባቢዎችን፣ በልማቱ የሚከናወኑ ተግባሮችን፣ ልማቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ የሚጠናቀቅ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ ተብራርቷል፡፡ ፕሮጀክቱ በከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት መሪነት እየተፈጸመ የሚገኝና በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚመራም ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ባለፈው ሳምንት የኮሪደር ልማቱን እንቅስቃሴ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳስረዱት፤ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ሥራ በአንድ ጀምበር የተጀመረ አይደለም፤ ከባለፈው 2015 ዓ.ም ግንቦት ወር አንስቶ በሀገር ውስጥ በሚገኙ አንጋፋ አጥኚዎች፣ አማካሪዎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት ዝርዝር እቅድ ወጥቶለት ሲጠና የቆየ ነው።

ይሄን መሰል ሰፊ ሥራ ሲካሄድ ኅብረተሰቡንና የሚመለከታቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ግለሰቦች የማወያየት ሥራ ተሰርቷል፤ ወደ ተለያዩ ጉዳዮች ገባ ብሎ በመመልከትም መረጃ ተወስዷል። ፕሮጀክቱ ሲጀመርም ምን ያህል ነዋሪዎችን እና መሰረተ ልማቶችን ሊነካ እንደሚችል፣ ምን ያህል ተጨማሪ ሀብት እና ጊዜ እንደሚፈልግ ጭምር በዝርዝር ተጠንቶ ያንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሞገስ አብራርተዋል።

የሚመለከታቸው ባለሙያዎች አስተያየት እንደሰጡበት፤ አመራሮች እና የተቋማት ኃላፊዎች እንደተሳተፉበት የገለጹት አቶ ሞገሰ፤ እነዚህ ጉዳዮች ሰብሰብ ብለው በከተማ አመራር ውይይት ተደርጎባቸው እና ህጋዊ አካሄድን ተከትሎ ወደ ሥራ እንደተገባም አስታውቀዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ጉዳይ በዚህ መልኩ ሂደቱን እየጨረሰ መምጣቱን አብራርተው፤ ማህበረሰቡም በሂደቱ ውስጥ ያለፈና ዓላማውን እየተረዳ የመጣ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ኅብረተሰቡ እስካሁን በከተማ አስተዳደሩ ተገንብተው ለአገልግሎት ከዋሉ ፕሮጀክቶች ግንዛቤ በመውሰድ የከተማ አስተዳደሩ ባቀረባቸው አዳዲስ የልማት ፍላጎቶች ላይ ተባባሪ መሆኑን እንዳረጋገጠም አስታውቀዋል።

የቅድመ ዝግጀት ሥራውም በአግባቡ የተሄደበት እና የኅብረተሰቡን መረዳት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እረፍት አልባ በሆነ ሂደት የተሠራ መሆኑን አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ መጨረስ ሌሎች ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮር ለመስራት ጊዜ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡ የልማቱ መፍጠን ድህነት ለማስወገድ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉም አቶ ሞገስ አመላክተዋል።

እንደ አቶ ሞገስ ማብራሪያ፤ የመዲናዋ ኮሪደር ልማት ሰፊ ሥራ የተካተተበት ከመሆኑ በስተቀር በከተማዋ ከለውጥ ጊዜ ጀምሮ በመስቀል አደባባይ፣ በአንድነት ፓርክ፣ በወዳጅነት ፓርክ፣ በእንጦጦ እንዲሁም በሌሎች ፕሮጀክቶች በርካታ ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። እነዚህ መሰረተ ልማቶች በለውጡ መንግሥት ቁርጠኛ አመራርነት የተሠሩ ናቸው። የለውጡ መንግሥት ቃል የገባውን የሚፈጽም ነው። የአሁኑ የኮሪደር ልማት ሰፋ ባለ መልኩ ማንቀሳቀስ ከመቻሉ ውጪ የመሰረተ ልማት ሥራው በከተማዋ ከለውጡ ወዲህ እረፍት በሌለው ሁኔታ ሲከናወን ቆይቷል።

መዲናዋን እንደ ስሟ የማስዋብ እና የማልማት ሥራው በተጠናከረ መልኩ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው፤ በካዛንቺስ፣ ቸርችል ጎዳና፣ ብሔራዊ በመንገዶች አስተዳደር አካባቢ፣ የተሰሩትን ሥራዎች በአብነት አንስተዋል፡፡ የአሁኑን የኮሪደር ልማት ሥራ ልዩ የሚያደርገው ሰፊ እና በርካታ አካባቢዎችን የሚዳስስ በመሆኑ ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኮሪደር ልማቱ በአምስት አካባቢዎች ላይ እየተካሄደ ነው። በፒያሳ እና ዙሪያው፣ ከፒያሳ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና፣ ከቀበና በኬንያ ኤምባሲ በጀርባ በኩል መገናኛ አደባባይ፣ ከቀበና በዋናው መንገድ ተከትሎ መገናኛ አደባባይ፣ ከቦሌ አደባባይ በመስቀል አደባባይ አልፎ እስከ አራት ኪሎ፣ ከቦሌ በኢምፔሪያል በኩል እስከ መገናኛ፣ ከመገናኛ ሲኤምሲ ባሉት አካባቢዎች የከተማ አስተዳደሩ በሰፊው የመሰረተ ልማት ግንባታውን እያካሄደ ይገኛል።

በሌሎች አካባቢዎች ላይ በቀጣይ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ሲኖሩ ለኅብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ ይሰራል ያሉት አቶ ሞገስ፣ የእናንተ ኮሪደር ሊለማ ነው፤ ከዚህ ውጡ፤ ይሄንን ሸጡ እያሉ የሚያደናግሩ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ሌሎች የልማት ሥራዎችን በተመሳሳይ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንደሚያከናውን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ህብረተሰቡንና የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት እንጂ በስማ በለው እና በአደናጋሪዎች እንደማይሠራ አመልክተዋል። ኅብረተሰቡ በየደረጃው የሚገኙ የከተማ አስተዳደሮችን ማናገር እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

ስራውን ለማከናወን የሚያስችሉ የገንዘብ እና የማቴሪያል አቅርቦቶችም አብረው ተቀናጅተው ሥራው እየተመራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል። በርከት ያሉ ኮንትራክተሮች እና ማሽነሪዎች በፕሮጀክቱ እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ የመንገዶች ባለሥልጣን ቡድን፣ በአንዳንዱ ላይ ደግሞ ሌሎች ኮንትራክተሮች መሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡

ሀገራችን ካለባት የድህነት ጫና በመነሳት እያንዳንዱ የመሰረተ ልማት ሥራ በፍጥነት እና በጥራት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲልም በዚህ ተግባቦት ላይ በመመስረት በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። ከዚህ በፊት 10 እና 15 ዓመት የሚወስዱ፣ አንዳንዶቹም ተጀምረው የማይከናወኑ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን የፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እየተፈጸመ የሚጠናቀቁበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህም ባጠረ ጊዜ የተጠናቀቁ፣ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ፣ የከተማዋን ገጽታ በትልቁ የቀየሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዳሉም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ አዲስ አበባ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ከ10 በላይ የተለያዩ ስትራክቸራል ፕላኖች በተለያየ ጊዜ ተዘጋጅተዋል። አብዛኛዎቹ ፕላኖች ግን ትውልዱን ታሳቢ ያደረጉ፣ ዘመኑን የዋጁ፣ የዓለምን የከተሞች እድገት እና ስልጣኔ መሰረት ያደረጉ አልነበሩም።

መዲናዋ ካላት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮና ኃላፊነት አኳያ ከስር ከስር እየተሰሩ እያደጉ ባለመምጣታቸው ዛሬ ላይ ላለው የከተማ አስተዳደር ውዝፍ የቤት ሥራ ጥለው አልፈዋል ሲሉም አመልክተዋል። ይህ በመሆኑም አዲስ አበባ የስም ብቻ በመሆን የማይታይ አበባ እና የማይታይ አዲስነት ይዛ ቆይታለች ያሉት አቶ ሞገስ፣ የደከሙ ቤቶችና መንገዶች፣ ያልተሟሉ መሰረተ ልማቶች፣ ለኅብረተሰቡ ምቹ ያልሆኑ መንደሮች የበዙባት፣ ነገር ግን በስም ተንቆጥቁጣ አዲስ አበባ ስንላት የቆየች ከተማ ናት ሲሉ አዲስ አበባን ገልጸዋታል።

ከአምስቱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መካከል አንዱ ከሜክሲኮ ሳር ቤት ወሎ ሰፈር ያለው የኮሪደር ልማት ነው። የዚህን ኮሪደር ልማት ሥራ የሚከታተሉት አቶ ሞገስ እንዳብራሩት፤ ከሜክሲኮ ሳር ቤት ወሎ ሰፈር ያለው የኮሪደር ልማት ከሜክሲኮ ሳር ቤት፣ ከሳር ቤት ጎተራ እና ከጎተራ ወሎ ሰፈር በሶስት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተሰራ ነው።

በዚህም የመጀመሪያው ምዕራፍ ከሜክሲኮ ሳር ቤት ያለው የኮሪደር ልማት 70 በመቶ በላይ የሚሆነው ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን በወቅቱ ገልጸዋል። በመንገድ አካፋዩ ላይ የነበሩ ዛፎችና መሰረተ ልማቶችን በማንሳት በዲዛይኑ መሰረት የሳር ልባስ ተደርጎለት የዛፍ ተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ ይገኛል ያሉት አቶ ሞገስ፤ በግንባታው ምክንያት የተቆፈረው የአስፋልቱ መንገድ ተመልሶ የአስፋልት ሥራው ተጠናቋል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ የዚህ ምዕራፍ አብዛኛዎቹ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው። በ60 ቀናት ውስጥ ሥራውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው። ሥራው ለ24 ሰዓት እየተከናወነ በመሆኑ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። የጎንና ጎን የአፈር ሥራውና በውስጥ የሚገነቡት የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተጠናቀው የእግረኛ ንጣፍ እየተሰራ ነው። ከዚህም ባለፈ የሳይክል መንገድ እየተሰራ ይገኛል።

ከሳር ቤት ጎተራ ያለው መንገድ ከተመረቀ ቅርብ ጊዜው ቢሆንም፣ በአረንጓዴ ቦታዎቹ እና በእግረኛ መንገዶቹ ላይ የዲዛይን ማሻሻያ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከቀድሞ ኮንትራክተር ጋር ውይይት ተደርጓል ያሉት አቶ ሞገስ፤ የዚህም የወሰን ማስከበር ሥራው የተጠናቀቀ በመሆኑ በቀሪዎቹ ጊዜያት የማሻሻያ ሥራው ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ከጎተራ ወሎ ሰፈር ያለው የኮሪደር ልማት ትልልቅ ሕንፃዎች፣ ከፍተኛ ኃይል የሚያስተላልፉ የኤሌክትሪክ መስመሮች እንዲሁም የቴሌኮም ፋይበር መስመሮች እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ከታችና ከላይ ያሉበት በመሆኑ የልማት ሥራው በሚጠበቀው ፍጥነት ሊሄድ አልተቻለም። እነዚህን ጉዳዮች በጥንቃቄ በመመልከትም ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፤ አሁን በመሬቱ ስር የሚያልፉ መስመሮችን የማስተካከል ሥራ፤ የእግረኛና የሳይክል መንገድ ንጣፍ እየተከናወነ ነው። ይህኛው ምዕራፍም ከሜክሲኮ ሳር ቤት ቀጥሎ ይጠናቀቃል ።

መንግሥት በኮሪደር ልማቱ የሚሰራቸው ሥራዎች ድህነት፣ ኋላቀርነት እና ውስብስብ የሆኑ ማህበራዊ ጫናዎችን የሚያቃልሉ ናቸው። የልማት ሥራዎቹም በፍጥነትና በጥራት ይከናወናሉ።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You