“ከተማዋ ባልተገራ የልማት ሥርዓት ውስጥ በማለፏ ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርጋለች” – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጊዜያት ባልተገራ የከተማ ልማት ሥርዓት ውስጥ በማለፏ ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርጋለች ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በከተማው ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሚቆይ የአካባቢ ብክለት የመከላከል ንቅናቄ ትናንት ተጀምሯል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዕለቱ እንደገለጹት፤ ከተማዋ ባለፉት ጊዜያት ባልተገራ የከተማ ልማት እድገት ሥርዓት ውስጥ በማለፏ ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርጋለች፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ለመመሥረቷና ለስያሜዋ ምክንያት የሆኑ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሯትም፤ በአግባቡ ባለመያዛቸው የተፈጥሮ ሀብቷን ጠብቆ ማቆየትም ሆነ ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አክለውም፤ ከተማዋ ለከፍተኛ ብክለት በመዳረጓ በከተማዋና በዙሪያዋ በወንዞች አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎቿ ላይ የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማጎሳቀል በተጨማሪ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች ገለጻ፤ ከተማዋ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው 76 ወንዞች፣ በርካታ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች፣ ጥብቅ ደን እንዲሁም ሌሎች ሀብቶች ቢኖራትም በነበረው ያልተገራ የከተማ ልማት ሥርዓት በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ችግሩን ለመቅረፍና የከተማዋን ሥነ-ምሕዳር ለማሻሻል የሚረዱ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ርብርብ በልዩ ትኩረት ሲተገበሩ ቆይተዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ አሁን ላይ በከተማው የተጀመረው የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ወንዞችን ከመጥፋት እየታደገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ የነበረውን የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን የታደገውና ከነበረበት ሁለት ነጥብ ስምንት ወደ 15 በመቶ ያሳደገው የአረንጓዴ አሻራ፤ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ በኤሌክትሪክ መኪና መተካት የሚያስችለው ፖሊሲ መዘጋጀት እና የኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቮች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየራቸው በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን አብራርተዋል፡፡

በከተማው እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ የፕላስቲክ አጠቃቀም ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ አካባቢን በማይበክሉ ተለዋጭ ምርቶች መተካት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ከንቲባ አዳነች ያስረዱት፡፡

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዚያ 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም የሚቆይ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ እንደሚያካሄድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You