የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ውጤታማ የሆነው ማህበር

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክተው የቡና ልማት የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናኑ ይገኛሉ። የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የኤክስፖርት ንግዱን ማሻሻል ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ውጤት እንድታገኝ ያስችላታል። በመሆኑም ከታች ከልማቱ ጀምሮ በቡና አዘገጃጀትና በኤክስፖርት ንግድ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ። ይህ የቡና ልማትና ግብይት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል አርሶአደር ላይ መሥራት የግድ እንደሆነ ይታመናል።

የቡና ምርትና ምርታማነት ሲያድግ የኤክስፖርት መጠንም በዚያው ልክ ከፍ እንዲል መስራት ይገባል። ለዚህም የሀገሪቱን ቡና በዓለም ገበያ ለማስተዋወቅና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን የበለጠ ለማሳደግ ብዙ መሥራት ይጠበቃል። የቡና ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ቡናውን በጥራት አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ የተለያዩ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እንዲሁም ማበረታቻዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ። ለዚህም ነው መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በጥራት እንዲመረትና እንዲዘጋጅ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርጉት።

የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅና የተሻለ ገበያ እንዲያገኝ ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል ‹‹ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱን መስፈርት አሟልተው ሰርተፊኬት ያገኙ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና የግል ቡና አምራቾች በየዓመቱ የቡና ቅምሻ ውድድር እንዲያደርጉ በመስራት ምርጥ አሰራሮችን በመለየት ቡናቸውንና እነሱን በዓለም ገበያ ያስተዋውቃል። ይህም የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ገበያውን ሰብሮ እንዲገባና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ያደርጋል።

የዕለቱ የስኬት ዝግጅታችንም ‹‹ከኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› ዓለም አቀፍ ድርጅት ዕውቅና ካገኙ ህብረት ሥራ ማህበራት መካከል አንዱ በሆነው በሲዳማ ቡና አምራች የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ላይ ትኩረት አድርጓል። ማህበሩ ቡናቸው ተወዳድሮ ‹‹የኦርጋኒክ ፌር ትሬድ ››የዕውቅና ሰርተፊኬት ካገኙ ቡና አምራች ህብረት ሥራ ማህበራት መካከል አንዱ ነው። ኦርጋኒክ የሆነ ጥራት ያለው ቡና አምራች የሆነው ማህበሩ፣ በዘንድሮው ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› ዓለም አቀፍ የቡና ቅምሻ ውድድር ተሳትፎ የአምስተኛነት ደረጃን ይዟል።

የሲዳማ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ፕሮጀክትና ሰርተፊኬሽን አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ ደስታ እንዳሉት፤ ማህበሩ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ የሲዳማ አካባቢ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ እጅግ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ቡናው ከምርት ጀምሮ በጥራት የሚዘጋጅና ተፈጥሯዊ ጣዕሙን እንደጠበቀ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ በመሆኑም የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ በማውጣት ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል።

አቶ ኤርሚያስ እንዳብራሩት፤ የሲዳማ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር በ1993 ዓ.ም በ12 አባላትና በ36 ሚሊዮን መነሻ ካፒታል ነው የተመሰረተው። ማህበሩ አሁን ላይ 67 ማህበራትና ከአንድ መቶ ሺ በላይ አባላትን ማፍራት ችሏል።

ማህበሩ በሁለት የተከፈለ ነው፤ በአሁኑ ወቅት 41ዱ ማህበራት ‹‹በፌር ትሬድና ኦርጋኒክ›› ሰርተፊኬት አግኝተዋል፤ ቀሪዎቹ 26 ማህበራት ደግሞ ‹‹የፌር ትሬድ ኦርጋኒክ›› ምስክር ወረቅትን ለማግኘት እየሠሩ ይገኛሉ። ቡናን በጥራት በማምረት ‹‹የፌር ትሬድ ሰርተፊኬት›› ያገኙት 41 ማህበራትም ከ72 ሺ በላይ አባላት አሏቸው።

የማህበሩ አባላት በቡና ጥራት ላይ እየሠሩ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፤ ከጥራት ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም እንዲሁ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ሲሉ ይገልጻሉ። በተለይም በአለም አቀፉ ‹‹ኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› ዕውቅናን ያገኙ ማህበራት ከድርጅቱ የሚያገኙት ማበረታቻ በመኖሩ ተነሳሽነታቸውን ጨምሯል ነው ያሉት። የሲዳማ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የምርት መጠንና ጥራት እየጨመረ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ማህበሩ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እንደመሆኑ ሥራው ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል። ገዢ አገራት ውል የሚገቡት ቡናው እንዴት እንደሚመረት፣እንዴት እንደሚዘጋጅና ቀጣይነት ያለው የእሴት ሰንሰለት መኖሩን እያረጋገጡ ነው። ለእዚህም ምርታማነትና ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የግድ ይሆናል። አንድ ዓመት ልኮ ቀጣይ ዓመት ላይ አለመላክ አይቻልም። ከደንበኞች ጋር በሚኖር የውል ስምምነት መሰረት በየዓመቱ የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡና ለደንበኞቹ ይቀርባል።

ማህበሩ ስፔሻሊቲ ቡናን ለረጅም ጊዜ ደንበኞቹ ማቅረብ በመቻሉ ቡናውን ተደራድሮና ከዓለም አቀፍ ዋጋ በበለጠ ከፍ አድርጎ የመሸጥ ዕድል አለው። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ከኦርጋኒክ ፌር ትሬድ›› የዕውቅና ሰርተፊኬት ያገኘ በመሆኑና በዚህም ቡናውን በዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ ከፍ አድርጎ ከመሸጥ ባለፈ በኪሎ ከ20 እስከ 40 ሳንቲም ጭማሪ ያገኛል። አብዛኞቹ ገዢ አገራት የሚፈልጉት ቡና የፌር ትሬድ የዕውቅና ሰርተፊኬት ያገኘና ኦርጋኒክ ቡና በመሆኑ ማህበሩ ትልቅ የገበያ ዕድል ተፈጥሮለታል።

እሳቸው እንዳሉት፡- በአሁኑ ወቅት የሲዳማ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን የተሻለ ዋጋ እያገኘ ነው። የምርትም፣ ኤክስፖርት መጠኑም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል፤ ለዚህም የኦርጋኒክ ፌር ትሬድ ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል መሆኑና የዕውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶለታል። ማህበሩ ከአባላቱ የሚሰበስበውን ቡና በየዓመቱ ለውጭ ገበያ እያቀረበ ሲሆን፤ አዳዲስ ገዢ ሀገራትም የሲዳማ ቡናን ምርጫ እያደረጉ ነው።

ማህበሩ ከአባላቱ የሰበሰበውን ቡና በራሱ ማበጠሪያና መፈልፈያ ማሽን አዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ ኤክስፖርት ያደርጋል። በአብዛኛው ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያዎች ቡናውን ያቀርባል።

አመታዊ የኤክስፖርት አቅሙም ከአራት ሺ እስከ አምስት ሺ ቶን እንደሆነ አቶ ኤርሚያስ አስታውቀዋል። በውጭ ምንዛሪ ግኝቱም ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ጠቅሰው፤ ከዚህ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ቡናን በጥራት አምርቶና አዘጋጅቶ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚገባው አስታውቀዋል፤ ለዚህም አርሶ አደሩ ላይ በመሥራት ተነሳሽነቱን ከፍ ማድረግ አለበት ባይ ናቸው።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በ2016 በጀት ዓመት ማህበሩ አራት ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ሲሆን፤ ከዚህም ከ22 እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ይችላል። የውጭ ምንዛሪ ገቢ ግኝቱን ተደራድሮ የሚሸጥበትን ዋጋም ማህበሩ ይወስናል፤ ዘንድሮ የተመረተው ቡና በተወሰነ መጠን ቅናሽ ማሳየቱን አቶ ኤርሚያስ ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ ግን ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል ሲሉ አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ ያመረተውን ቡና በማህበራቱ አማካኝነት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መሸጥ መቻሉ ትልቅ ጥቅም እያስገኘለት ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ ማህበሩ የሚያገኘውን ትርፍም እንዲሁ ለአባላቱ በማከፋፈል የአባላቱን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው ብለዋል። ለአብነትም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ የትርፍ ትርፍ ክፍያ በማድረግ ለአባላቱ ማከፋፈል መቻሉን አስታውሰዋል። ይህም ቡናው በዓለም አቀፍ ገበያ ተዋውቆ በተሻለ ዋጋ መሸጥ በመቻሉ የተገኘ ውጤት መሆኑን አስታውቀው፣ ማህበሩ በአካባቢው በሚሰራቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎቹ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

እንደ አቶ ኤርሚያስ ማብራሪያ፤ አብዛኛው የሲዳማ ክልል አርሶ አደር ቡና አምራች እየሆነ መጥቷል ።በቀድሞው ሲዳማ ዞን በአሁኑ ሲዳማ ክልል የሚገኙ ወይናደጋማ አካባቢዎች ጭምር አሁን ላይ ቡና በስፋት ይመረትባቸዋል። ዳራ፣ ዳሌ፣ ጩኮ፣ በንሳ፣ ጭሬና ሌሎች የክልሉ ወረዳዎች ቡና እንደሚመረትባቸው አቶ ኤርሚያስ ጠቁመዋል። የሲዳማ ቡና አምራች ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር የተመሰረተውም በእነዚሁ ቡና አብቃይ አካባቢዎች በሚገኙ አባል አርሶ አደሮች መሆኑን ተናግረዋል።

በየወረዳው የሚገኙ አባል አርሶ አደሮች የሚያለሙትን ቡና ለማህበራት በመሸጥ ማህበሩም ከአርሶ አደሩ የሰበሰበውን ቡና አጥቦና አድርቆ በማዘጋጀት ለዩኒየኑ እንደሚያስረክብ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፤ ዩኒየኑም ገበያ አፈላልጎ ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ እንደሚልክ አጫውተውናል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ህብረት ሥራ ማህበሩ ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ቡናን በጥራት ማምረት እንዲችል ድጋፍና ክትትል ያደርጋል። አርሶ አደሩም ስልጠናውን ተግባራዊ በማድረግ ከዓመት ዓመት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በመሆኑም በ36 ሚሊዮን ብር የተመሰረተው የሲዳማ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር በአሁኑ ወቅት የካፒታል መጠኑ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ደርሷል። ካፈራቸው ሃብቶች መካከልም ሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ የገነባውና ወደ ስራ ያስገባው ትልቅ ህንጻ አንዱ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁለት የኤክስፖርት ቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎችንም ገንብቷል። በእነዚህ ጣቢያዎች እና አጠቃላይ በኤክስፖርት ግብይት ዙሪያ ተሳታፊ ለሆኑ 36 ሠራተኞችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

የሲዳማ ቡና አምራች ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር አርሶ አደሩ ቡናውን በተሻለ ዋጋ መሸጥና ከቡናው የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ድጋፎችን እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፤ ቡናውን ለሚገዙ ማህበራት የፋይናንስ አቅርቦቱን በማስፋት ማህበራቱ ከማህበሩ ብድር ወስደው ቡናውን ከአምራቹ መግዛት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት። በዚህ የተነሳም ማህበራቱ ብድር ፍለጋ ወደ ባንክ አይሄዱም ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ማህበሩ ራሱ ባንክ ሆኖ በማገልገል ከወለደ ነጻ ብድር ያቀርብላቸዋል ብለዋል።

ማህበራቱ ቡናውን ከአርሶ አደሮቹ ሲገዙ አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ባረጋጋጠ መንገድ መሆኑንም በመግለጽ፤ አንድ ኪሎ ቀይ ቡና ለሚያቀርብ አንድ አርሶ አደር ከመደበኛ ዋጋው በተጨማሪ ማህበራቱ ከአምስት እስከ አስር ብር ተጨማሪ ክፍያ ይከፍላል ብለዋል። ይህም የሚፈጸመው አርሶ አደሩን ለማበረታታትና ተነሳሽነቱን ለመጨመር እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ ማህበሩም ከማህበራቱ የሰበሰበውን ቡና በጥራት አዘጋጅቶ ገበያ በማፈላለግ ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ የሚያገኘው ትርፍ በመኖሩ ነው ብለዋል። ከሚያገኘው ትርፍ እያንዳንዱ አባል አርሶ አደርም እንዲሁ ተከፋይ መሆኑን አስረድተው፤ ይህም ማህበሩ የቡና ባለቤት የሆነውን አርሶ አደር ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበራቱ በሚያገኙት የትርፍ ክፍያም ከማህበሩ ጋር በአካባቢው የልማት ሥራዎችን የሚሠሩ ሲሆን፤ ከሚሠሯቸው የልማት ሥራዎች መካከልም ትምህርት ቤቶች፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ የጤና ተቋማት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃና የመብራት ዝርጋታ ይገኙበታል። እነዚህን የልማት ሥራዎች ለአካባቢው በመሥራት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ማህበሩ ከእነዚህ ስራዎች በተጨማሪ ማህበሩን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ስራዎች ላይ ‹‹ከፌር ትሬድ አፍሪካ ››ጋር በመተባበር እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማቅረብ የአርሶ አደሩን የኑሮ ጫና እያቀለለ የሚገኝ ትልቅ ፕሮጀክት ዕውን ተደርጓል።

የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት በመጠበቁ በአካባቢው የቡና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ አርሶ አደሩ የቡና ልማቱን እያስፋፋ ጥራትም ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የምርት መጠኑ እያደገና ተነሳሽነቱም እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። በቀጣይም አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግና ጥራት ያለው ቡና እንዲያመርት ከማድረግ ባለፈ ቡናን በጥሬው ለዓለም ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ እሴት ጨምሮ በማዘጋጀትና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ጠቁመዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You