መንግሥት ሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገት ለማምጣት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፣ በዚህም እየተመዘገበ ያለው ስኬት እንደ ሀገር ካለንበት ፈተና አንጻር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው። ይህንንም በየወቅቱ የሚወጡ ዓለም አቀፍ መረጃዎች በተጨባጭ የሚያመላክቱት ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት ጦርነት እና ግጭቶች፣ አለመረጋጋት እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች በበዙበት ሀገራዊ ዓውድ ውስጥ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል፣ በዚህም እየፈተኑን ያሉ ችግሮች የበለጠ አቅም ገዝተው የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳይከቱን መከላከል ችለናል።
ለዚህም ሲባል ወቅቱን የሚዋጁ የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን ከመጠቀም ጀምሮ፣ የምንመኘውን ለውጥ በምንፈልገው ፍጥነት ማሳካት የሚያስችሉ የቀደሙ ሕጎችና መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራዎች በስፋት ተሠርተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጭ ናቸው ።
በለውጡ ማግስት ተግባራዊ የሆነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ለዚህ በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው። ይህንን ተከትሎም በተለይም ንግድና ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል።
ከዚህ ውስጥ ሰሞኑን በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ክፍት ያደረገው የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ደንብ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኢንቨስትመንት ደምብ 474/2012 ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ የንግድ ሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል።
እንደሚታወቀው፣ መንግሥት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማበረታታት ለረጅም ጊዜያት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ዘርፎችን ከውጭ ኢንቨስትመንት ውድድር ተከልለው እንዲቆዩ የሚያስችለው ፖሊሲ ባለበት እንዲቆይ አድርጓል፡፡ ባለሀብቶች ፖሊሲው በሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ ሰፊ ርቀት ተጉዟል ።
በርግጥ፣ ፖሊሲው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት፤ ከዓለም-አቀፉ የንግድ ትስስር ሥርዓት ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ ለማስቻል፤ በሂደትም እሴትን ወደሚጨምሩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሸጋገሩ በማድረግ በሀገር ውስጥ አቅሞች ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ነበር ።
እንደ ሀገር በፖሊሲው አፈጻጸም የታየው ውጤት ግን፣ የሚጠበቀውን ዓላማ በሚፈለገው መጠን ማሳካት ያስቻለ አይደለም ፤ ከዚህ ይልቅ ከለላ የተሰጣቸው የንግድ ዘርፎች ሰፊ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ የጥራት እና የብቃት ችግሮች የሚታይባቸው ፣ ለሕገ-ወጥ ድርጊት የተጋለጡበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል ።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት የፖሊሲ እሳቤውን ማሻሻል አስፈልጓል። ዘርፎቹ ፍላጎትና አቅሙ ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች ደረጃ በደረጃ እንዲከፈቱ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አራቱ የንግድ ሥራ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል ።
የንግድ ሥራ ዘርፎች የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ በፀደቀው አዲስ የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟሉ ድረስ የውጭ ባለሀብቶች በጥሬ ቡና፣ በቅባት እህሎች፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች፣ ዶሮና የቁም እንስሳት መላክ የወጪ ንግድ ላይ መሳተፍ እንደሚችሉም ተመልክቷል ።
በገቢ ንግድ ከማዳበሪያና ነዳጅ ንግድ በስተቀር የውጭ ባለሀብቶች በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት፣ በጅምላ ንግድ ከማዳበሪያ ጅምላ ንግድ በስተቀር መሳተፍ እንደሚችሉ ተወስኗል። በችርቻሮ ንግድ የውጭ ባለሀብቶች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተከልለው በቆዩት በሁሉም የችርቻሮ ንግድ መሠማራት እንደሚችሉም ተገልጿል ።
ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መሆናቸው፤ ዘርፉን በውድድር እንዲመራ በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን በተሻለ መልኩ ማሳደግ የሚያስችል ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያሉ እውቀቶችን፤ ክህሎቶችን እና ሥርዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንደ መልካም አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ሀገር ውስጥ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀም ከማስቻል ባለፈ፤ የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን መልካም አጋጣሚ በመፍጠር ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል። ለጀመርነው ልማት ስኬትም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም