የአራዶቹ ሰፈር ከስማቸው በላይ ገዝፎ ሊታይ ነው

ከተመሠረተች ከ135 ዓመታት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ፤ የሀገሪቱ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት፤ ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን መገኛ በመሆን ሦስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ ነች። ከተማ እንደ ስሟ አዲስ ልትሆን ሀያ አራት ሰዓት እየተሠራ መሆኑን ስመለከት አንዳች የደስታ ስሜት ልቤን ይሞላዋል።

በከተማዋ መሐል ከተገነቡ ዘመናትን የተሻገሩት ቤቶች የሚያድሳቸው ጠፍቶ በእርጅና ምክንያት ጎብጠው፤ ግድግዳዎቻቸው ፈራርሶ፤ የጣራዎቻቸው ቀለም ወይቦ የከተማዋን ውበት አደብዝዘው ቆይተዋል፤ የነዋሪዎቿንም ሕይወት የማይመች አድርገውታል።

በእነዚህ የአረጁ ቤቶች ውስጥ በበጋም ሆነ በክረምት መኖር ስቃይ ነው። ቤቶቹ ከተማዋ ስትቆረቆር ጀምሮ የነበሩ በመሆናቸው የሚያፈርሳቸው ወይም የሚያድሳቸው አካል ቢያጡ አገልግሎት በቃኝ ያሉ ይመስል በራሳቸው እየፈረሱ እባካችሁ አንሱኝ ማለት ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል።

ባለ አንድ ክፍል የሆኑት አብዛኞቹ ቤቶች ሳሎንም መኝታም ምግብ ማብሰያም ሆነው ኖረዋል። ባስ ሲልም በአንድ ክፍል ውስጥ ደባል በመሆን ሁለት አባ ወራ የሚያስተናገዱ ቤቶችም አልታጡም። እናትና አባትን ልጆችም ሆኑ ሌሎች ተጨማሪ እንግዶች ይህችኑ አንድ ክፍል ይጋራሉ። ተጠጋግቶ መኖር ፍቅርን ያጠነክራል የሚል አባባል ቢኖርም አኗኗሩ አስተዳደግ ላይ የሚኖረው አሉታዊ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የቀደሙት ሰፈሮች ቤት በቤት ላይ ተደጋግፈው ችምም ብለው የተሠሩ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመኑ፤ ከ135 ዓመታት በፊት ከነበሩበት ዲዛይናቸው ተቀይሮ ቤት ሲጠብ ሌላ ቤት ተቀጥሎበት፤ መፀዳጃ ቤትን ለሠላሳና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚጠቀሙባት ሻወር መውሰድ ቅንጦት የሆነበት፤ የቆረቆዘች የድህነት መገለጫ የሆኑ ሕዝቦች ከተማ መሆኗ ቀርቶ በውበቷ የምታማልል ሽቅርቅሪቱን አዲስ የምናየበት ቀን እሩቅ አይሆንም።

ቤቶቹ የአዲስ አበባን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩ፤ ከተማዋ ተመልካች አልባ ሆኗ ስለመኖሯ አመላካቾች፤ ጎዳና ተዳዳሪነት፤ ሴተኛ አዳሪነት፤ ማጅራት መቺነትና የመሳሰሉት ወንጀልና ወንጀል ነክ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው፤ የቁማር፤ የጫት፤ የሺሻ እና የአረቄ ቤቶች መገኛ፤ ወጣቶች በገዛ ፈቃዳቸው ለሱሰ ተገዥ የሆኑባት ከተማ፤ ቤቷን አድሷ ጓዳ ጎድጓዳዋን ሰታፀዳ የፀዳ ከተማ ከፀዳ አዕምሮ ጋር አይኖራትም ትላላችሁ?

እነ ዶሮ ማነቂያ፤ እሪ በከንቱና ውቤ በረሃን ያየ ከገናና ስማቸው ጀርባ የዋልጌዎች መናኸሪያ መሆናቸውን መረዳት አይከብድም። ፒያሳም ብትሆን ስሟ የደመቀ ያሸበረቀ ቢሆንም፤ የስሟን ያህል የፀዳች ሥርዓት ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ ልትሆን ያልቻለችበት ምክንያት ያው አሮጌ በመሆና የተነሳ ነው።

በእውነት የልጅነትና የወጣትነት ትዝታን በውስጣቸው የያዙ የካፌዎች፤ ኬክ ቤቶች፤ ሲኒማ ቤቶች መገኛም ቢሆንም ከዘመኑ ጋር የዘመኑ መሆን ግድ ይላልና እድሳቱ አይቀሬ ነው። አሮጌው በሙሉ በአይቀሬው እድሳት አዲስ ሆኖ በአዲስ ሊተካ ሥራው ተጧጡፏል።

ስማቸው ከገናኖች በላይ የገነኑት እነዚህ ሰፈሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአንዲት ክፍል ውስጥ ቆጥና ምድር ሠርተው ፤ መፀዳጃ ቤት ተጋርተው፤ በአንዲት ክፍል አስር፤ አስራ አምስት ሆነው ተደራርበውና ተነባብረው የሚኖሩባቸው የድህነት ጥግ የሚታይባቸው ቦታዎች መሆናቸውንስ ማን ያምናል?

አካባቢዎቹ መሠረተ ልማት አርጅቶ አፍጅቶ አገልግሎት መስጠት ላቁም አላቁም ብሎ የሚወዛገብባቸው ናቸው። የአሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው እጅግ ኋላ ቀር ከመሆኑ በላይ እጅግ የተወሳሰበና ለአደጋም የተጋለጠ ሲሆን ዝናብና የንፋስ ሽውታ ሲያገኘው በቀላሉ የሚበጠስ፤ በሰበብ አስባቡ ከአገልግሎት ውጪ የሚሆንበት ሰፈር ነው።

ቆሻሻ ልዩ ምልክቷ እስኪመስል ድረስ በየቦታው አፍንጫን የሚወጋ ሽታ ባለቤት የሆነችው ይች ከተማ ይህ ችግር እስከ ወዲያኛው ሊቀረፍላት ሽር ጉዱ ቀጥሏል። የውሃ ማስተለለፊያ መስመሮችና የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩበት ሁኔታ የጤና ችግርም የሚያስከትል ከመሆኑም ባሻገር አብዛኞቹ ውሃ መስመሮች ከቱቦዎች ውስጥ ወይም አጠገብ የተቀበሩ በመሆናቸው ከመፀዳጃ ቤት የሚወጣው ፍሳሽ ከሚጠጣው ውሃ ጋር እየተደባለቀ ለከፋ የጤና ችግር ሲዳርግ ቆይቷል።

ይህን ችግር ታሪክ ለማድረግም እየተሠራ ነው። በአንድ ጎን ፍሳሽ ማስወገጃው፤ በሌላ ገጽ የጎርፍ መውረጃው፤ የውሃና መብራት መሰመሮች ሁሉም ውቢቱን አዲስ በሚመጥን ልክ እየተሠራ ነው። አዲስ እንደ ስሟ ልትታደስ አሮጌዎቹ የከተማዋ ሰፈሮች ስማቸውን የሚመጥን ዘመናዊነት ሊላበሱ ርብርብ እየተደረገ ነው። የአራዶቹ ሰፈር ከስማቸው በላይ ገዝፈው ሊታዩ ፤ ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ወይ ! ሊያስብሉ ቀናትን በፍጥነት እየተጓዙ ነው።

ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮችን የሚመለከተው ይህ የኮሪደር ልማት፤ እርጅና ያጎበጣት ከተማ ዝቅ ማለቷ ቀርቶ ቀና ብላ እንግዶቿን የምትቀበለው፤ በውበት አሸብርቃ የምትታየው ዕድል ፈጣሪ ነው ።

ማንም ሰው ከለመደው የመለየት ነገር እንደ ሞት ቢከብደውም ልማቱ ነገን የተሻለ ለማድረግ ነውና ኅብረተሰቡም ይህን ተረድቶ ተባባሪነቱን ቢያሳይ፤ የልማት ተነሽዎችን ጉዳይ የያዛችሁ የመንግሥት አካላትም ሁሉን ባማከለና ባገናዘበ መልኩ አገልግሎቱን በቅንነትና በፍጥነት በመስጠት ከተማይቱ ተውባ የምትታይበትን ቀን እናሳጥር እላለሁ። አዱ ገነትን ቤት ለአንቦሳ የምንልበት ቀን እንዲቀርብ እመኛለሁ። ቸር ይግጠመን።

ለብሥራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You