የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት ከሦስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል

 እድሳቱን ለማጠናቀቅ 85 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡– የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ ገለጹ፡፡ እድሳቱን ለማጠናቀቅ 85 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ተነግሯል፡፡

የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የካቴድራሉ ሕንፃ እድሳት ከሦስት ወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ካቴድራሉ ከ90 ዓመት በላይ የአገልግሎት ዕድሜ ያለውና የሀገር ቅርስ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ እድሳቱን ከፍጻሜ ለማድረስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ካቴድራሉ ሕንፃውን ከሚያድሰው ቫርኔሮ ከተባለ ድርጅት ጋር ውል ገብቶ እድሳቱ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ሕንፃውን ለማደስ 172 ሚሊዮን ብር የሥራ ውል ስምምነት መፈጸሙንም ገልጸዋል።

እስካሁን ለእድሳቱ 90 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል ያሉት አስተዳዳሪው፤ ቀሪ የእድሳቱን ሥራዎች ለማጠናቀቅ 85 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የእድሳትና ጥገና ሥራው የመዋቅር፣ የኪነ ሕንፃ፣ የሥዕል፣ የፍሳሽ፣ ኤሌክትሪክ ዝርጋታ እድሳትን ጨምሮ ለዕድሳት ሥራው የሚውሉ የመዋዕለ ነዋያት ማሰባሰብ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ የካቴድራሉ እድሳት ሙሉ ለሙሉ ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡

ለኮንትራክተሩ ክፍያ የሚፈጸመው ከምዕመናን ከሚሰበሰብ ገንዘብ መሆኑን በመግለጽ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ለክፍያ የሚሆን በቂ ገንዘብ ማግኘት አዳጋች ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ቀናት የቀጥታ ሥርጭትን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች የገንዘብ ማሰባሰብ መርሀ ግብር መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ የካቴድራሉን እድሳት ለመጨረስ በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ካቴድራሉ የከተማዋ ቅርስ በመሆኑ እድሳቱን ከፍጻሜ ለማድረስ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ካቴድራሉ በውስጡ በያዛቸው ታሪኮች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም መስክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ የፓትርያሪክና የሊቃነ ጳጳሳት በዓለ ሲመት፣ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችና መሪዎች መካነ መቃብር የሚገኝበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You