ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቅ ምክር ቤቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሚያከናውናቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቅ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት የ 9 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ገምግሟል።

የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ የሱፍ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴሩ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅና የአፈጻጸም ክፍተት አለበት፡፡

እንዲሁም በክልሎች መካከል የአፈፃፀም ልዩነቶች፤ የጥናትና ዲዛይን ሥራ ዝቅተኛ መሆን፤ ግንባታ ጥራት ማነስ የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ለጊዜ እና ለሀብት ብክነት የሚዳርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶች መዘግየት ብድርን ከመመለስ አንጻር ክፍተት የሚፈጥር እና የሕዝብ የልማት ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ችግር የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በጥናትና ዲዛይን የያዛቸው ከሦስት ዓመት እስከ 11 ዓመት ያስቆጠሩ 27 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ከ27ቱ ፕሮጀክቶች 10 የሚሆኑት ላይ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተከናወነ ሥራ አለመኖሩን ተናግረው፤ በተጨማሪም አንድ ፕሮጀክት የተቋረጠ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

መሠረተ ልማት ግንባታን በተመለከተም ካሉት 28 የመስኖ መሠረተ ልማቶች 19 የሚሆኑት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ምንም ሥራ ያልተከናወነባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የአርብቶ አደር ማህበረሰቡን ከድርቅና ከጎርፍ የመሳሰሉት አደጋዎች ለመከላከልና ሕይወት ከማሻሻል አንጻር በቅንጅት ከተቋማት ጋር የመሥራት ክፍተት፣ እቅድና ሪፖርት ከመሬት ጋር ካለው ሥራ ያለመናበብ፣ ችግር አፈታት ክፍተት የሚስተዋል ሲሆን በልዩ ሁኔታ ታይቶ መፈታት አለበት ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፤ ለፕሮጀክቶች መዘግየት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የዲዛይን ችግር ነው። ይህም በበርካታ ፕሮጀክቶች ከ75 በመቶ የሚሆነውን የጊዜ መጓተት እና የገንዘብ መጨመር ድርሻ ይወስዳል፡፡

በክትትል ያልተሠራ ዲዛይንና አዋጭነቱ በትክክል ያልታወቀ ፕሮጀክት እንዲሁም በአካባቢው ላይ የሚኖረው ተጽእኖ በአግባቡ ባለመሠራቱ ምክንያት ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ አዳጋች ያደርገዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም የአዋጭነት ጥናት በትክክል አለመጠናት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር፣ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጉዳዮች፣ የሥራ ተቋራጭ አቅም ውስንነት እና በዘርፉ የአሠራር ስታንዳርድ አለመኖር እንዲሁም የግንባታ ግብዓቶች እጥረትንና የዋጋ መናር ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በክልሎች መካከል የሚስተዋለውን የአቅም ልዩነትን ለማጥበብ ለክልሎቹ የአፈጻጸም አቅምን ለማሳገድ የተለያዩ ሥልጠና እና ልምድ ልውውጥ የሚያካሂድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያሉበትን ችግሮች በመፍታት ሀገሪቱ ያላትን የመስኖ አለኝታዎች እና የቆላማ አካባቢ ሀብቶችን በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።

ማኅሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You