በንቅናቄው ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- አካባቢን ከብክለት በመከላከል ንቅናቄ ለሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዕቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም የሚቆይ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ዲሪባ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በንቅናቄው ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል፡፡

ንቅናቄው በአካባቢ ብክለት ዙሪያ የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡

የመርሀ- ግብሩን ተፈጻሚነት ለማሳደግ የሚያግዙ የተለያዩ ዶክመንቶች በማዘጋጀት ፕሮግራም ወጥቷል ያሉት አቶ ድዳ፤ በከተማው የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን አመላክተዋል፡፡

የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄው በከተማ አስተዳደሩ እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ድረስ በመውረድ የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ድዳ ገለጻ፤ የንቅናቄው ዓላማ እየተባባሰ የመጣውን የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ ከብክለት የጸዳ ሀገር የማስረከብ እሳቤ በመያዝ ነው፡፡

ንቅናቄው በተለያዩ ዙሮች የሚከናወን ሲሆን፤ የፕላስቲክ ብክለት፣ የአየር ብክለት፣ የውሃ ብክለት፣ የአፈር ብክለት እና የድምጽ ብክለት በሚል እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻው ዙርም ንቅናቄው የሄደበት ሂደት እንደሚገመገም አቶ ድዳ ተናግረዋል፡፡

ከግንዛቤ ማስጨበጡ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ ሕጎች የሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት አቶ ድዳ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ይህ የንቅናቄ መርሀ- ግብር በአዲስ አበባ ከወዲሁ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።

አቶ ድዳ፤ በንቅናቄው በከተማው የሚገኙ የማህበረሰብ አካላት በሙሉ የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ በነቂስ የሚሳተፉበት ነው ያሉ ሲሆን፤ ከተማዋ በተለይ የዲፕሎማቲክ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ጽዱና ውብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በከተማው የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ሥራዎች ባለመሠራታቸው የጤና ችግር እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መኖሩን አቶ ድዳ አመላክተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You