በሰው ተኮር ልማት የደመቀው የአዲስ አበባ ውበት

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን ትላልቅ ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ግድቦች፣ ኢንደስትሪ ፓርኮች፤ መንገዶች፤ የቴሌና የመብራት መሠረተ ልማቶች፤ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ተጠቃሽ ናቸው። ለእነዚህም በርካታ መዋዕለ ነዋይ ወጥቷል። ነገር ግን እስከ ለውጡ ድረስ በሰብዓዊ ልማት ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት በእጅጉ ውስን ሆኖ ቆይቷል።

ይህ ደግሞ ሀገሪቱ የተሟላ ልማት እንዳይኖራትና ዕድገቷም ሁለንተናዊ እንዳይሆን አድርጓል። ከለውጡ ወዲህ ያሉት ዓመታት ግን ይህንን አስተሳሰብ በመሻር ከቁሳዊ ልማቱ ባሻገር፣ ለሰብዓዊ ልማት በቂ ትኩረት የተሰጠበት ጊዜ ነው። ለዚህ በርከት ያሉ ማሳያዎችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ ያለውን ሁነት እንደ ማሳያ ማንሳቱ በራሱ በዚህም፣ ገላጭም ይሆናል።

ምክንያቱም፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ስሟ ሆና እንድትገለጥ ዘርፈ ብዙም፣ መልከ ብዙም የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ነው። ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚቀይሯት የተለያዩ መሠረተ ልማቶች፣ የመዝናኛ እና የቱሪዝም ሥፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ።

በዚህ መልኩ የአዲስ አበባን ገጽታ የሚቀይሩና እና የቱሪስት ፍሰት የሚያሳድጉ ሥራዎችንም በመሥራት፤ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን ከተማ በጎብኚዎች ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የተሠራው ሥራም የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ነው። ለምሳሌ፣ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የአንድነት፤ የወንድማማችነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከአዲስ አበባ አልፈው የሀገር ኩራት ለመሆን በቅተዋል።

እነዚህ በአዲስ አበባ የተሠሩት አመርቂ ሥራዎችም ኮይሻን፤ ጎርጎራንና ወንጪን ለመሳሰሉ ግዙፍ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መነሻ ለመሆን በቅተዋል። ይሄም ከተማዋ እንደ ስሟ ውብና አዲስ ሆና እንድትታይ፤ ለነዋሪዎቿም፣ ለእንግዶቿም ምቹና ሳቢ በመሆን የስማርት ሲቲ ገጽታን እንድትላበስ የሚያደርጋትም ነው።

ከእነዚህ ዓይነ ግቡ ሥራዎች ጎን ለጎን ደግሞ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት የሚያሻሽሉ ሰው ተኮር ተግባራትም እየተከናወኑ ነው። በተለይም ለውጡ እውን ከሆነበት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ አስተዳዳር መለያ ከሆኑ ተግባራት ውስጥ በዝቅትኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል የሚደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው።

በዚህ ፕሮግራም ውስጥ በተለይም አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርገዋል። እጅ ያጠራቸውን ዜጎች ከማገዝ አኳያም ሊፈርሱ የደረሱ ደሳሳ ጐጆዎቻቸው ቀና እንዲሉ ተደርገዋል። በዚህም የበርካታ አቅመ ደካሞች እንባ ታብሷል፤ የበርካቶችንም ተስፋ ማለምለም ተችሏል።

መንግሥት በሚከተለው ሰው ተኮር ፖሊስ ምክንያት፣ ዜጎች የተሻለ መጠለያ እንዲያገኙ በተያዘው ዕቅድ በየዓመቱ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የአቅመ ደካማ ቤቶች እየታደሱ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ዜጎች በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ ከማስቻሉም በላይ የከተማዋን ገጽታ ከስር መሠረቱ እየቀየረው ይገኛል።

አሁን አሁን ደግሞ በክረምት ብቻ የነበረው ቤት ማደስ ክረምትን ተሻግሮ በበጋም መተግበር ጀምሯል። በዚህም ምክንያት የበጎ ፈቃድ ሥራው ዓመቱን ሙሉ እየተከናወነ ይገኛል። በዚህ በጎ ተግባር ውስጥም መንግሥት የራሱን ሀብት ፈሰስ ከማድረጉም ባሻገር፤ ባለሀብቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል።

ሌላው የከተማ አስተዳደሩ እየሠራቸው ካሉ በጎ ተግባራት ውስጥ አንዱ የሆነው እና በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደ ባህል እየተወሰደ ያለው፣ ማዕድ ማጋራት ነው። ማዕድ ማጋራት በአቅም እጦት የተነሳ በአግባቡ ምግብ ማግኘት የማይችሉ ወገኖችን የሚደግፍ በጎ ሥራ ነው። ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም እሴት ነው። በተለይም ይህ ተግባር በበዓላት ወቅት በብዛት የሚዘወተርና ዜጎች አውደ ዓመቶችን (በዓላትን) እንደሌላው ዜጋ ተደስተው እንዲያሳልፉ የሚያስችል ነው።

ለወትሮ በማጣት ምክንያት በበዓላት ወቅት ቤታቸውን ከርችመው የሚውሉ ዜጎች፣ ዛሬ በማዕድ ማጋራት መልካም ተግባር ምክንያት በዓላትን በደስታ ማሳለፍ ችለዋል። በበዓላት የሀዘን ድባብ የሚያጠቃቸው ቤቶች ዛሬ በደስታ ተለውጠዋል። በእነዚህ ዜጎች ዘንድ በዓላት የፈገግታ ምንጭ ሆነዋል። እናም ማዕድ ማጋራት ተሳስቦ የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴትን ያጠናከረ እና የእኛነታችን አንዱ መገለጫ እየሆነ ያለ ተግባር ነው።

ማዕድ ማጋራት የብዙዎችንም ሕይወት የታደገ በጎ ተግባር ነው። በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ስጋት ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ በተገደበበትና አቅመ ደካሞችም አስታዋሽ ባጡበት ወቅት ሕይወታቸውን የታደገው የማዕድ ማጋራት ተግባር ነው። በተለይም የእለት ጉርሳቸውን በአነስተኛ ሥራ እና በልመና የሚያሟሉ ዜጎች ማዕድ ማጋራት ባይደርስላቸው ችግሩ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

በማዕድ ማጋራት ከሀገር ውስጥ አቅመ ደካሞች ባሻገርም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ሀገራቸውን ትተው የተሰደዱ ስደተኞችም ጭምር እንዲታወሱ በማድረግ፤ ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነቷንና የሰው ልጀችን ሁሉ በእኩል ዓይን የምታይ ሀገር መሆኗን አስመስክራለች። የቅርቡን እንኳን ብንመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቤተመንግሥታቸው ከሶርያ፤ ከየመን፤ ከሶማሊና ከሌሎችም ሀገራት የመጡ ስደተኞችን ጠርተው በኢፍጣር ማዕድ አጋርተዋል።

አቅመ ደካሞችን ከመመገብ ጋር በተያያዘ ሌላው ሳይነሳ የማይታለፈው የምገባ ማዕከላት ጉዳይ ነው። አቅመ ደካሞች ለሆኑና በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ላቃታቸው በራቸውን ክፍት አድርገው የሚጠብቁ 20 የምገባ ማዕከላት ተከፍተው በቀን ከ35 ሺህ በላይ አቅም ደካሞችን እያገለገሉ ነው።

የምገባ ማዕከላቱ ዜጎች በአቅም ማነስ ምክንያት ሳይበሉ እንዳይውሉና በተለይም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች እንዳይራቡ እነዚህ የምገባ ማዕከላት አበርክቷቸው የጎላ ነው። የአዲስ አበባ አስተዳደር ይፋ እንዳደረገውም በአዲስ አበባ ከተማ 102 ሺህ ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ራሳቸውን መመገብ አይችሉም።

በቀን አንድ ጊዜ እራሳቸውን መመገብ ከማይችሉት 102 ሺህ ዜጎች መካከል፣ መንቀሳቀስና ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የማይችሉና ሥራ የመሥራት አቅም እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት ያልቻሉ ይገኙበታል። ስለዚህም አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መልኩ አስተዳደሩ የምግባ ማዕከላትን እያስፋፋ መምጣቱ ተገቢነት ያለው ተግባር መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያብራራው፤ በሀገራችን ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱት መካከል ከ26ነጥብ8 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ልጆች ከ40 ሺህ በላይ በሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። እድሜያቸው ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የደረሱ ሁሉንም ልጆች ተደራሽ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶችም አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ልጆች ዛሬም ድረስ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሆኖም በትምህርት ተሳትፎ እና ውስጣዊ ብቃት ችግር ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የምግብና ሥርአተ ምግብ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። ልጆች ለምግብ እጥረት በመጋለጣቸው የተነሳ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ከሚመጣው አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ውስንነት ተጋላጭ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ እስከ ዘለቄታው ከትምህርት ጋር ተቆራርጠው የሚቀሩበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ለአብነትም፣ በኢትዮጵያ 16 በመቶ የሚሆነው የተማሪዎች መጠነ መድገም የሚከሰተው ከተመጣጠነ ምግብ ችግር ጋር በተያያዘ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ለገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብቻ የተተው አይደለም። ይልቁንም የአፍሪካ መዲና እና የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባም የዚህ ችግር ሰለባ ነች። አዲስ አበባ በየዓመቱ ከምግብ ችግር ጋር በተያያዘ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ላልተገባ ሕይወት ይዳረጋሉ። ይህንን የተረዳው አዲስ አበባ አስተዳደር በ2011 በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባን በማስጀመር ለተማሪዎች ብርታት ለወላጆች እፎይታ ለመሆን በቅቷል።

አስተዳደሩ ባደረገው ጥረትም 700 ሺህ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብ ትምህርታቸውን ያለሃሳብ በመማር ላይ ይገኛሉ። በዚህም ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና እንዳያቋርጡ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። መጠነ ማቋረጥና ማርፈድም ወደ ዜሮ ወርዷል።

የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የረሃብ ተጋላጭነትን በማስቀረት የተሟላ ሥነ-ምግብና፤ ጤና እንዲሁም ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አቀባበልና ውጤት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ያደጉ ሕፃናት ከሌሎች ሕፃናት ጋር ሲወዳደሩ ጤናማ፣ በትምህርታቸው ውጤታማ በተለይም በሂሳብና በሳይንስ ትምህርቶች የላቀ ችሎታ ያላቸው፣ አዳዲስ ጠቃሚ ሃሳቦችን ማፍለቅ የሚችሉ፣ ሲያድጉም ሥራ ፈጣሪ መሆን የሚችሉ ናቸው።

ከእነዚህ ሰው ተኮር ተግባራት ጋር አብሮ ሊጠቀስ የሚችለው ሌላው ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሴቶችን ማዕከል አድርጎ የሚያከናውናቸው ተግባራት ናቸው። ጎዳና ላይ የወደቁ ሴቶችን ከጎዳና አንስቶ አሰልጥኖ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከማድረግም ባሻገር ለዘመናት የተረሱ እና እንጨት ለቅመው የሚተዳደሩ ሴቶችን በማሰባሰብ በጉለሌ አካባቢ ሰፊ ሥራ እድል ፈጥሮላቸዋል።

እነዚህ ሴቶች ለዘመናት በእንጨት ለቀማ ሲተዳደሩ የነበሩና በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን የተጋፈጡ ሴቶች መሆናቸው ቢታወቅም፤ እስከዛሬ ግን ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ ተግባር የፈጸመላቸው አካል አልነበረም። አስተዳደሩ ሰሞኑን ያስመረቀው የጉለሌ የተቀናጀ የሴቶች ማዕከል በርካታ ሴቶችን በባልትና ፤ በእንጀራ እና በከተማ ግብርና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ከዚሁ ባሻገርም ባለሀብቶችን በማስተባበር ጭምር ለእነዚሁ አቅመ ደካማ ሴቶች ተገጣጣሚ ቤቶችን ሰርቶ አስረክቧል።

በቃሊቲ አካባቢ የተገነባው ‹‹የነገዋ የሴቶች ማዕከልም›› በሴተኛ አዳሪነትና በጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ሴቶችን ከጎዳና ላይ በማንሳት በተለያዩ ዘርፎች ሴቶችን በማሰልጠን የሙያ ባለቤት የሚያደርግ ዘመናዊ ማዕከል ነው። ይህ ማዕከል ከዘመናዊነቱም ባሻገር በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶችን በማሰልጠን እራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል።

ዛሬም አዲስ አበባ የመልሶ ማልማትና የኮሪደር ልማት እየተከናወነባት ያለች ከተማ ነች። ሆኖም ይህቺ ከተማ እንደቀድሞ ለልማት ስትል ነዋሪዎቿን የምትገፋ ከተማ አይደለችም። ይልቁንም ቅድሚያ ለሰው በሚል መርህ ዜጎች ከአካባቢያቸው ሲነሱ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።

የኮሪደር ልማቱ ሲከናወንም ከተለያዩ ቦታዎች ለሚነሱ ግለሰቦች ምትክ ቦታ እንደሚሰጥ አስተዳደሩ አስታውቋል። ቀደም ሲል በቀበሌ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ከቦታው በመነሳታቸው ምክንያት ለችግር እንዳይጋለጡ ምትክ የቀበሌ ቤት ወይም ኮንዶሚኒየም እንደ ምርጫቸው እንደሚሰጣቸው አስተዳደሩ አስታውቋል። ይሄውም እየተደረገ ይገኛል። በተመሳሳይም የግል ይዞታ የነበራቸው ነዋሪዎች ምትክ ቦታና ካሳ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል። ይህም ተግባራዊ እየሆነ ነው።

በአጠቃላይ አዲስ አበባ በለውጥ ውስጥ ትገኛለች። ለውጡ ደግሞ ቁሳዊ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሰብዓዊ ባህርያትን የያዘ ሰው ተኮር ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የሚገነቡት መንገዶች ተንከባካቢ አግኝተው እድሜ እንዲኖራቸው፤ የሚተከሉ ችግኞች እና አረንጓዴ ቦታዎች እንዲጠበቁና ውበት እንዲጎናጸፉ በር ይከፍታል።

ሰውን ባገለለ መልኩ የሚሠሩ ሥራዎች ግን ውጤታቸው መበላሸት ብሎም መፍረስ መሆኑን አይተናል። በመልሶ ማልማት ስም ሲፈጸሙ የነበሩ ግፎች መንግሥትና ሕዝብን ምን ያህል እንዳቃቃሩ ኖረን ተመልክተናል። ዛሬ ግን የከተማ አስተዳደሩ ቁሳዊና ሰብዓዊ ልማቶችን አሰናስኖ እየሄደ ነው። ትላንት ስጋት አድሮባቸው የነበሩ ወገኖች፣ ዛሬ ላይ ሥራዎች ሰውን ማዕከል አድርገው እንደሚከናወኑ በመረዳታቸው ምስጋና ሲያሰሙ እያዳመጥናቸው ነው። ይሄን ተግባር እኛም አመሰገንን።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You