ድርጅቱ ክፍተቶቹን በማረም የሀገርን ኢኮኖሚ በአግባቡ እንዲደግፍ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በገቢ አሰባሰብና በአገልግሎት አሰጣጥ የታዩበትን ክፍተቶች በማረም የሀገርን ኢኮኖሚ ባግባቡ ሊደግፍ እንደሚገባ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትና የየብስ ወደቦች አገልግሎት አሰጣጥ ኢኮኖሚያዊ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ የ2014/15 ዓ.ም አገልግሎት አሰጣጥ የዋና ኦዲተርን የክዋኔ ኦዲት መነሻ በማድረግ ውይይት አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ካለው ሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩበትን ክፍተቶች በአፋጣኝ ማስተካከል አለበት። የማህበረሰቡን ችግር መፍታት ገቢ በማመንጨትም የሀገርን ኢኮኖሚ ባግባቡ የመደገፍ ተግባሩን መወጣት ይኖርበታል።

ያልተሰበሰቡ ቀሪ ገንዘቦች ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲሰበሰብ፣ ድርጅታዊ መዋቅሩ ተገቢ የሰው ኃይልን ማሟላት እንደሚገባው፤ አገልግሎቱን የሚመጥን እና ክፍተቶችን የሚደፍን ተግባር ማከናወን እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ከስምንት ዓመታት እስከ 11 ዓመታት ድረስ ተከማችተው የሚገኙ ባለቤቶቻቸው የማይታወቁ፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ ኬሚካል እና ምግቦችን በመስክ ምልከታ መታዘባቸውን በማንሳትም፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በፍጥነት ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመረጃ አያያዝ ሥራውን ለማዘመን ትኩረት መስጠት አለበትም ነው ያሉት።

ድርጅቱ የዋና ኦዲተር ግኝትን የእቅዱ አካል አድርጎ ሊሠራበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ ድርጅቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥልቀት እንደታየ አንስተዋል።

የማስፈጸም አቅም ውስንነት ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርገውን አሰራር ያለመዘርጋቱን በውስንነት አንስተዋል።

በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ከውጪ ሀገር በጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻ ላጓጓዛቸው ጭነቶችና የተሽከርካሪ አገልግሎቶች ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግለሰቦች እና ከተለያዩ ድርጅቶች ደንበኞቹ ያልሰበሰባቸው ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም አምስት ሚሊዮን ዶላር ውዝፍ ክፍያዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

ድርጅቱ በወደቦችና ተርሚናሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያከናውናቸው ግዥዎች፤ የግዥ ሥርዓትና መመሪያን ያልተከተሉ መሆናቸው በክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ተጠቁሟል።

ባለቤታቸው ያልታወቀና ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችና የታሸጉ ምግቦች በማስወገድ በኩል ክፍተት እንዳለበትም ተጠቅሷል።

ድርጅቱ የዘርፉን ሥራ ሊያሠራ የሚያስችል ድርጅታዊ መዋቅር የሌለው፤ የተቀመጠውን በቂ የሰው ኃይል ያላሟላ መሆኑንም በኦዲቱ መለየቱም ተነስቷል።

ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚጓጓዙ የኮንቴይነር ጭነቶችና ተሽከርካሪዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ወደ መዳረሻ ቦታዎች የሚያደርስበት አሠራር ሥርዓት ላይ ክፍተት መኖሩም ተጠቁሟል።

ዕቃዎችንና ተሽከርካሪዎችን አጓጉዘው ጥቅም ላይ የዋሉ ባዶ ኮንቴነሮችን ወደ ጅቡቲ ወደብ በጊዜ ባለመመለሳቸው የኮንቴይነር ክምችት መኖሩም በክፍተት የተለየ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፤ ድርጅቱ ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ከየብስ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከክዋኔ ኦዲት ግኝቱ በኋላ የነበሩትን በርካታ ችግሮች ለማስተካከል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አብዛውን የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ መሰብሰብ መቻሉንም አመልክተዋል። አብዛኛውን የቀረውንም እንዲከፈል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

ባዶ ኮንቴይነሮች በጊዜ እንዲመለሱ እየተሠራ ነው፣ አሠራሩን ዘመናዊ የማድረግ ሥራ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ድርጅቱ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴውና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር እንዲያቀርብም ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You