ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል። ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረጉም በኩል የተወጣው ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ከትምህርት ከጤና፤ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት እንደ ዘርፎቹ ቢለያይም መረጃውን ተደራሽ በማድረግና አገልግሎቱን ሰፊና ቀልጣፋ እንዲሆን በማስቻሉ በኩል ቴክኖሎጂ ተኪ የለሽ ሚና ያለው ነው።
እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ ቴክኖሎጂ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር፣ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ ለትምህርት ለግብርና ለጤና ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ የማይታሰብ ከሆነ ሰነባብቷል።
እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ በመንግሥት ይገለፃል። የዚሁ አካል የሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን ለሦስት ሳምንት በሚዘልቀው ዓውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፎች የተሠማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ‹‹ስታርት አፖች›› ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
ወጣት አብርሃም አሰፋ በዚህ ዓውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች አንዱ ነው። የሀዱ ዌብ ቴክኖሎጂ ኩባንያው መሥራችና ባለቤት የሆነው ወጣት አብርሃም፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት በሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ሥራ ተሠማርቶ እንደቆየ፤ በቅርቡ ደግሞ ቅድሚያ ጤና (Tena first) የተሰኘ ዲጂታል የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የፈጠራ ሀሳብ ይዞ ብቅ እንዳለ ያስረዳል።
ስለ ቴክኖሎጂው ምንነት ወጣት አብርሃም ሲያስረዳ፤ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የጊዜ ውስንነት ሳይገድባቸው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ አማራጭ እንደሆነ ይናገራል። ለዚህ ሥራዬ ምክንያት የሆነኝ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የተከሰተው ሁኔታ ነበር “በኮቪድ ወቅት የማኅበራዊ ግንኙነት የተገደበ በመሆኑ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙት በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ነበር” የሚለው አብርሃም በዚህ ወቅት የዚህ ቴክኖሎጂ ፋይዳ በጉልህ የታየ ስለነበር ብዙዎች እንደገቡበት ተናግሮ የእርሱም ምክንያትም ይሄው እንደነበር ይናገራል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስምንት በመቶ በታች የነበረው ወደ (Tele medicine) ቴክኖሎጂ የመግባት እንቅስቃሴ ከኮቪድ በኋላ ወደ 68 በመቶ እንዳደገ የሚናገረው አብርሃም፤ እንደዚህ አይነት የቴሌ ሕክምናዎች ማንኛውም ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ የትኛውንም የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አማራጭ በመሆኑ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ጥረት ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ ወደዚህ ሥራ የገባነው ይላል።
አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አንድን ሐኪም ለማግኘት በትንሹ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ይፈጃል፤ ታካሚ ከዶክተሩ ጋር የሚኖረው ጊዜ ግን ቢበዛ ከአስራ አምስት ደቂቃ የማይበልጥ ነው። በዚህ ምክንያት የሚባክነው ጊዜ ከፍተኛ ነው የሚለው ወጣት አብርሃም፤ በዚህ ቴክኖሎጂ ግን ሕክምና የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የሚያስፈልገውን የሕክምና ባለሙያ ማግኘት እንደሚችል ይናገራል።
ድርጅቱ ይህንን ቴክኖሎጂ በተለያዩ አራት አማራጮች ይዞ መጥቷል የሚለው አብርሃም፤ የመጀመሪያ ድምፅን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን ሰዎች የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም በርቀት ካለ የሕክምና ባለሙያ ጋር በመነጋገር የመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ይላል።
ሁለተኛው በቪዲዮ የተደገፈ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን በተለይ ይህ አማራጭ ለቆዳ ሕክምና ፈላጊዎች ከፍተኛ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ይናገራል። ታካሚው ባለበት ቦታ ሆኖ የተጎዳውን የቆዳ አካል ፎቶግራፍ አንስቶ ወይም ቪዲዮ ቀርፆ ለሐኪሙ ይልክለታል የሕክምና ባለሙያው በየትኛውም ቦታ ሆኖ የተላከለትን ፎቶግራፍ ወይም ቪዲዮ አይቶ መድኃኒት ማዘዝ የሚያስችል እንደሆነ ይገልጻል።
ሦስተኛው መንገድ (on clinic) የሚሰኝ አማራጭ ነው የሚለው ወጣቱ “ይህ ማለት አሁን ያለውን የሰዎች በአካል ተገኝቶ ሕክምና የመከታተል ሂደትን የሚከተል ሲሆን ነገር ግን ቴክኖሎጂው አካሄዱን በማዘመን የመጣ ነው” ይላል። “ሰዎች የት ጋር ሄደው የሚፈልጉትን ዶክተር ማግኘት እንደሚችሉ አያውቁም በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ግን የሚፈልጉትን ሐኪም ካገኙ በኋላ ቀጠሮ በመያዝ ሐኪሙ ወዳለበት የጤና ተቋም ሄደው ሕክምና ማግኘት እንዲችል ያስችላል” ይላል።
አራተኛው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ቤት ለቤት የሚሰጥ የጤና አገልግሎት እንደሆነ ወጣት አብርሃም ይናገራል፤ በዘርፉ የበቁ እውቀት ያላቸው ነርሶች በመጠቀም የቤት ውስጥ ሕክምና ለሚፈልግ ሰው አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ አንዱ የድርጅቱ ሥራ ነው። በዚህ ሂደት አገልግሎት ፈላጊው በቤቱ ሆኖ ሕክምና ማግኘት እንዲችል መንገዱን ቀላል ማድረግ እንደተቻለ ይናገራል።
እንደ ወጣት አብርሃም ገለፃ፤ ኩባንያው ይዞት የመጣው ትልቁ ነገር ሀገሪቱ ብዙ ኢንቨስት አድርጋ ያስተማረቻቸው የሕክምና ዶክተሮች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ባለሙያዎች በተፈለገው ልክ ሥራ እያገኙ አይደለም። አሁን ግን አንድ ዶክተር ሥራ ለመሥራት የግድ ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል መገንባት ሳይጠበቅበት በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የራሱን አቅም በማስተዋወቅ ሥራ መሥራት እንዲችል በር መክፈት ተችሏል። ከዚህ ባለፈ ባለሙያው በሚኖርበት አካባቢ ለሚገኝ የሕክምና ፈላጊ አገልግሎት በመስጠት የሥራ ዕድል በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያደርግ ስለመሆኑ ይናገራል።
የጤና ባለሙያ በዚህ የቴክኖሎጂ መስመር እራሱን ስላስመዘገበ ብቻ ሥራ መሥራት አይችልም፤ እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ትክክለኝነት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዲረጋገጡ ይደረጋል፤ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ሥራ የሚገቡት ይህም ተገልጋይ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሚኖረው ትርጉም ከፍተኛ እንደሆነ ወጣት አብርሃም ይናገራል።
ይህ ቴክኖሎጂ ሕክምናን ተደራሽ በማድረግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው የሚለው አብርሃም፤ ማንኛውም የሕክምና አገልግሎት ፈላጊ ግለሰብ ወደ 6037 የጥሪ ማዕከል በመደወል የሚፈልገውን አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ተስቦ የተሠራ በመሆኑ በዚህ ረገድ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ይናገራል።
የዚህ ቴክኖሎጂ ሌላው ፋይዳ ሰዎች አቅማቸውን ባገናዘበ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው የሚለው አብርሃም፤ የካርድና መሰል ወጭዎች ሳይኖሩባቸው በመቶ ሃምሳ ብር አንድ ሰው የጤና ሁኔታውን ማወቅ ከአንድ ዶክተር ጋር ስለጤናነው የምክር አገልግሎት ማግኘት ይችላል፤ ስለዚህ በትንሽ ወጭ ጤናውን እንዲጠብቅ የሚያስችል አሠራር እንደሆነ ይናገራል።
“አሁን ባለው የሕይወት ልምምድ ሰዎች ሩጫ ላይ ናቸው” የሚለው አብርሃም፤ ብዙ ሕመምና የጤና እክል እያለባቸው ከዛሬ ነገ ወደ ሕክምና ቦታ እሄዳለሁ እያሉ ጊዜ ይወስዳሉ በዚ ሂደት ድንገት ሕይወታቸው ያልፋል፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን የ24 ሰዓት አገልግሎት ስለሚሰጥ ይህንኑ በመጠቀም እራስን ከከፋ ጉዳት መታደግ እንደሚቻል ይናገራል።
ሰዎች የሕመም ስሜት ሲሰማቸው በቶሎ መታከም ቻሉ ማለት በብዙ መልኩ ወጪን መቀነስና በትንሽ ወጪ ከሕመማቸው መዳን ቻሉ ማለት ነው የሚለው አብርሃም፤ ውስብስብ የሕክምና ሂደት ውስጥ ከገቡ የሚያስወጣቸው ወጪ ከፍተኛ ነው። በዚህም ቢሆን ሕመሙ ስር ሰዶ ከረፈደ ከደረሱ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተውም ቢሆን መዳን አይችሉም፤ ስለዚህ እንደዚህ አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰዎች ስለጤናቸው ተከታታይ ክትትል እያደረጉ ችግር ሲያጋጥማቸው አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ጤናቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ ናቸው ይላል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ ነው የሚለው አብረሃም፤ የላብራቶሪ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር በጋራ ስለሚሠራ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛነታቸው ወደተረጋገጡ የላብራቶሪ ተቋማት አንድ ታካሚ ዲጂታል በሆነ መንገድ ከዶክተር የተላከለትን ትዕዛዝ ይዞ በመሄድ የላብራቶሪ አገልግሎት ማግኘት ይችላል። በተመሳሳይ ከፋርማሲ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠራ በመሆኑ አንድ ታካሚ ዶክተሩ ያዘዛለትን መድኃኒት በ QR code በመረጋገጥ ማግኘት እንደሚችል ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት በዚህ ቴክኖሎጂ ስር ከ800 መቶ በላይ የሕክምና ባለሙያዎች ተመዝግበው እንደሚገኙ የሚናገረው አብርሃም፤ ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያውያን ሕክምናን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ አቅምና ችሎታ ያላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለብዙዎች እፎይታ የሚሰጥ ነው ይላል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው አብርሃም፤ ይህ ዓውደ ርዕይም በጅምር ያለ የፈጠራ ሥራ ያላቸውን ወጣቶች የተገኙበት እንደመሆኑ በጅምር ያለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ የተለያዩ ኢንቨስተሮች አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ሥራዎችን ማሳየት የሚቻልበት አጋጣሚ መፈጠሩ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ይናገራል።
ወጣት አብርሃም እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቴክኖሎጂ በትምህርት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ማስተማር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነ ሕዝብ ሕክምና ተደራሽ ማድረግ አይቻልም። በግብርናውም በቴክኖሎጂ ተጠቅመን ካልሠራን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መመገብ አይታሰብም። ትልቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ ነው ያለውና ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የውዴታ ግዴታ ነው ይላል።
አብርሃም እንደሚለው፤ ቴክኖሎጂ በባሕሪው የሚታይ ውጤት ለማምጣት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፣ ስለዚህም ገና በጅምር እያለ ከተኮረኮመ ማደግ እንደማይችል እና አዲስ የተገኘን የቴክኖሎጂ ውጤት የማያዋጣና መጥፎ አድርጎ በመውሰድ ከመግፋት ይልቅ ተስፋ ሰንቆ በመበረታታት ብዙ ነገር ማትረፍ እንደሚቻል ያስረዳል።
አሁን ያለንበት ዘመን ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጃችን ማግኘት የምንችልበት የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ አንድን ነገር ለመከወን በሙሉ ልብ ከተነሱ የማይቻል ነገር የለም ገንዘብ የለኝም የሚያግዘኝ ሰው የለም በማለት የተቀመጡ ወጣቶች አሉ ይህ መሆን የለበትም የተወሰነ ዕውቀት ከለ ያንን በማዳበር ባላቸው ግብዓት ብቻ ከቀላል ነገር በመጀመር ለመሥራት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ወጣት አብርሃም ይናገራል።
ቴክኖሎጂ በጥቂት የሰው ኃይልና ቦታ ትላልቅ ሥራዎች ለመሥራት ምቹ መሆኑ ዘርፉን በብዙ ተመራጭ እንደሚያደርገው የሚናገረው ወጣት አብርሃም፤ በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ቴክኖሎጂን ከግምት በማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ብሎም በቴክኖሎጂ ላይ ለተሠማሩ ተቋማትና ግለሰቦች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መሥራት እንዳለበት ያስገነዝባል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም