ችግሮችን በጠብመንጃ አፈሙዝ ፣ በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ የጥፋት ጉዞዎች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። እንደ ሀገር ከመጣንበት የግጭት አዙሪት ወጥተን ፣ በተሻለ ሰላም እና መረጋጋት ነገዎቻችንን ብሩህ አድርገን መሥራት እንዳንችልም ዋነኛ ተግዳሮት ሆነውብናል ።
ከዚህ ዘመን ካለፈበት የተሳሳተ አስተሳሰብ ችግር መማር አለመቻላችን ፣ እያንዳንዱ ትውልድ ባልተገባ መልኩ ፣ ላልተገባ ዓላማ ሕይወቱን እና ማኅበራዊ ተስፋውን እንዲገብር አድርጎታል። ለዘለቄታው በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን ወቅቶች በፈጠራቸው አቅሞች የተፈቱ በሚመስሉ ችግሮች እየተፈተነ የራሱን ሕይወት መኖር የሚችልበትን ዕድል ተናጥቀውታል።
እብሪት ፣ ማን አለብኝነት እና ኃይል አምላኪነት የሚፈጥራቸው እነዚህ ችግሮች ፣ለሰላም የተከፈሉ ዋጋዎችን ሳይቀር በማሳነስ ፣ ሀገር እና ሕዝብ ተረጋግቶ የተሻለ ሕይወት እንዳይኖር አድርገውታል። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ተረጋግቶ እንዳይኖር የስጋት ምንጭም ሆነውበታል።
ይህ እውነታ የየዘመኑ ታሪካችን አካል ቢሆንም ፣ከዚህ የታሪካችን ብዙ ምዕራፍ ከሆነው ችግራችን በአግባቡ መማር ባለመቻላችን ፣ ዛሬም አስተሳሰቡ ለፈጠረው እና እየፈጠረ ላለው ችግር ትውልዱ ባልተገባ መልኩ ፣ ላልተገባ ዓላማ ሕይወቱን እና ማኅበራዊ ተስፋውን እየገበረ ይገኛል።
ከዚህ ችግር ለዘለቄታው ለመውጣት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አለመግባባቶችንና የፖለቲካ ተቃርኖዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በለውጥ ኃይሉ በኩል የተደረጉ ጥረቶች እንደ አቅመ ቢስነት መቆጠራቸው፤ ችግሩ ሀገርን የማፍረስ ፣ ሕዝብን የመበተን ስጋት ውስጥ ከቶ እንደነበር የትናንት ትውስታችን ነው።
ይህን ሀገራዊ ስጋት ለመቀልበስ የተሄደበት ርቀትና የጠየቀው መስዋዕትነት የቱን ያህል ተጨማሪ የታሪክ ስብራት እንደሆነ ፣ በተለይ በሰሜን የሀገራችን ክፍል ለሚገኙ ወገኖቻችን የሚነገር አይደለም። እንደ ሀገር ተስፋ ባደረግናቸው ነገዎቻችን ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳም ምን ያህል የከፋ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የለውጥ ኃይሉ ችግሮችን ገና ከጅምሩ በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ለመፍታት ረጅም ርቀት ከመጓዝ ባለፈ፣ ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳም ብዙ ዋጋ በመክፈል ችግሩ በሰላም የሚፈታበትን ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመገኘት እውን አድርጎታል። በርካታ አካባቢዎች ከጥይት ድምፅ ነጻ ሆነዋል።
ከዚህም ባለፈ ግጭት በነበረባቸው የትግራይ ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች አቅሙ በሚፈቅደው ያህል የመልሶ ግንባታዎችን በማከናወን ፣የአካባቢው ሕዝቦች ወደቀደመ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል ። በአካባቢው የሰላም አየር እንዲነፍስ ፣ዜጎችም የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን በተስፋ እንዲቀጥሉ አስችሏል።
በክልሎች መካከል የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎችም ሰላማዊ አማራጮችን ታሳቢ አድርገው ፣በሕዝበ ውሳኔ የሚፈቱበትን አማራጭ በማስቀመጥ ፣ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸውን አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ሌሎች ሰላማዊ አማራጮች ካሉም ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ ሀገራዊ ሰላምን በማጽናት በልማት የሕዝባችንን ነገዎች ብሩህ የማድረግ ዓላማ የያዘው የመንግሥት ሰላማዊ የችግር አፈታት አማራጭ ፣ በመላው ሕዝባችን ተቀባይነት ያገኘ ፣ በአካባቢው ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ወንድማማችነት ከማደስ ባለፈ የአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሪ ተደርጎ የተወሰደ ጭምር ነው።
ችግሩ የተፈታበት መንገድ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚል አዲስ አህጉራዊ መነቃቃት የፈጠረ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድም ከፍ ያለ እውቅና እና ከበሬታ ያተረፈ ፣እንደ ሀገርም ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን መነጋገር ከቻልን ከኛ በላይ እንዳልሆኑ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
ከዚህ የመላው ሕዝባችንን ይሁንታና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ያተረፍን የትናንት ችግሮቻችንን ለዘለቄታው ለመፍታት የሄድንበትን መንገድ የሚያፋልስና ተመልሰን ወደ ቀደመው የግጭት አዙሪት እንድንገባ የሚያስገድድ የትኛውም አይነት ኃይልን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ፣ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት አይኖረውም።
በእብሪት ፣ በማን አለብኝነት እና በገዘፈ የኃይል አምላኪነት የሚፈጠሩ ችግሮች ትናንት እንደሆነው ሁሉ ሀገር እና ሕዝብን አላስፈላጊ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊሆኑ አይችሉም። ይችላሉ ብሎ መገመትም ከትናንት ስህተት ያለመማር ትልቅ ውድቀት መሆኑ አይቀሬ ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም