ማሽነሪ አምራቾችን፣ ፈላጊዎችንና አቅራቢዎችን ማስተሳሰርን ያለመው መድረክ

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር መሥራቱን ቀጥሏል።ዘርፉ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በፋይናንስ፣ በማምረቻ ቦታ አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት እና በመሳሰሉት ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተሠርተው ውጤቶችም ተመዝግበዋል።

ዘርፉ ከኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከሰሜን የኢትዮጵያ ጦርነትና ከእሱ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጫናዎች የተነሳ ከደረሰበት ጉዳት እንዲወጣና መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም እንዲሁ ብዙ ሰርቷል፤ በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ከሥራ ውጭ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መመለስ፣ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለውጥ ማምጣት፣… የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።በንቅናቄው አሁንም ዘርፉን ይበልጥ የሚያጎልብቱ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከሚያመርቱት መካከል ማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይጠቀሳሉ።ለእነዚህ አምራቾች ምርቶች ገበያ በማመቻቸት በኩል እየተሰራ ነው።ሰሞኑንም ማሽነሪ አምራች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ተግዳሮቶችና መልካም እድሎች ላይ የመከረና የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የማሽነሪ አምራቾች ማህበር አመራሮች፣ አምራቾችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመደገፍ በርካታ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።በዚህም የተለያዩ ስኬቶች ቢመዘገቡም፣ ሀገራዊ የመልማት ፍላጎትን የሚያሟሉ ግን አይደሉም።በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ታሳቢ ያደረጉና እውቀትና ተግባር ተኮር እንቅስቃሴዎችን ማድረግ በማስፈለጉ የተለያዩ ርብርቦች እየተደረጉ ይገኛሉ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የማሸነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅዶችና ተግዳሮቶች በሚል ርእስ ከማሸነሪ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄደውን ይህን መድረክ በዓይነቱ ልዩ ሲሉ ገልጸውታል።በመድረኩ የሚካሄደው ውይይት ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች ለመፍታት ዓይነተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት እሴት የተጨመረበት ምርት በማምረት ፈጣንና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ በማድረግ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሽግግር ለማምጣት፣ እያደገ ለሚሄደው የሕዝብ ቁጥር የሥራ እድል ለመፍጠር ሰፊና ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃን በሰፊው በመጠቀም ግብርናን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለአምራቾች ሰፊ የገበያ እድል በመፍጠር ማሽነሪዎችንና መሳሪያዎችን አምርቶ በማቅረብ የማኑፋክቸሪንግና የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ እንደ ሀገር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት እንዲመጣ ለማድረግ በመንግሥት ደረጃ ስትራቴጂዎች ፖሊሲዎች ተቀይሰው ወደ ሥራ ተግብቷል። የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የገቢ ምርት መተካት፣ የቆዳ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል።የአቅም ግንባታ ስትራቴጂ፣ የኬሚካል ስትራቴጂ በቅርቡ ደግሞ የማሽነሪ ማምረት ስትራቴጂና የመሳሰሉትና ትስስር የመፍጠር ስትራቴጂዎች እንደ ሀገር ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

በአደረጃጀት በኩልም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢንስቲትዩቶች፣ ከሥራና ክህሎት ጋር የተያያዙ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች ለዚህ ዘርፍ ራእይና ግብ መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ እንደጠቆሙት፤ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ትልልቅ ግቦች ተቀምጠዋል።በተለይ በልማቱ እቅዱ መጨረሻ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት፣ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል።

የገቢ ምርትን ለመተካት እየተከናወነ ባለው ተግባር 30 በመቶ የነበረውን የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ እንዲሁም ከ50 በመቶ በታች ወርዶ የነበረውን የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል።አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም በኩል ሰፋ ያሉ እቅዶች ተቀምጠው እየተሠራ ነው፡፡

ይህንን አቅድ ማሳካት እንዲሁም የሥራ እድል መፍጠር የሚቻለው ለዜጎች የማምረቻ መሳሪያዎችን በማምረት የመሥሪያ ቦታዎችን ማቅረብ፣ የፋይናንስና የግብዓት ማነቆዎችን መፍታት እንዲሁም በክህሎት በኩል ያሉትን ችግሮች ተደራሽ በሆነ መንገድ መፍታት ሲቻል ነው።

እነዚህ ነገሮች ከተስተካከሉ ሥራ አጥነት የኛ ችግር አይሆንም፤ ነገር ግን ፋይናንስ ሳንዘጋጅ የመሥሪያ ቦታ ሳናቀርብ በተለይ ደግሞ ማሽነሪ ሳናቀርብ የሥራ አጥነት ችግርን መፍታት አንችልም ሲሉ ያብራሩት ሚኒስትሩ፣ አንድ ማሸን ማቅረብ ቢያንስ ከአስር ላላነሱ ዜጎች በቀጥታ የሥራ አጥነት ችግሮቻቸውን ይፈታል ሲሉ አመልክተዋል። ይሄ ቀጥተኛ ፋይዳው መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርቱን በመጓጓዝ፣ በመሸጥ በኩል የሥራ እድል የሚፈጠርላቸውን ሌሎች ዜጎች ሳይጨምር መሆኑን አስታውቀዋል።በተለይ ማሽን በማምረት ላይ አተኩረን በመሥራት ማሽኑን ስናቀርብ የምንፈጠረው የሥራ እድል ጤናማና ዘላቂነት ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል።በዚህ መልኩ የሚፈጠረው የሥራ እድል ለዜጎች ተስማሚና ምቹ እንደሆነም ነው ያመለከቱት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሰፊ የሥራ አጥነት ችግር ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሀገር ሁሉንም ማሽኖች ከውጭ ማምጣት የሚሆን አይደለም።የማሽነሪ ችግርን በራስ አቅም ለመፍታት ጥረት ማድረግም ያስፈልጋል።እንደዚያ ከሆነ በየደረጃው ከትንሽ እስከ ትልቅ የማምረቻ መሳሪያዎችን በማቅረብ የሥራ አጥነት ችግሮችን መፍታት ይቻላል።

‹‹ከዚህ አኳያ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ብንል የማሽን ማምረት አቅማችን እያደገ፣ ከኛ አልፎም አንዳንድ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ጀምረናል›› ሲሉም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።ሚኒስትሩ ማሽኖቹ ሲታዩ እውን እዚህ ሀገር ውስጥ የተሰሩ ናቸው የሚል ጥያቄ ያስነሳሉ ብለዋል።የጥራት ደረጃቸው፣ ጥንካሬያቸው፣ የማምረት አቅማቸው ለሥራ ያላቸው ተስማሚነት እንደ ሀገር በዚህ ዘርፍ እየተፈጠረ ያለው አቅም በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ያመላክታሉ ሲሉም አብራርተዋል።

ከዚህ አኳያም በጣም ተስፋ ሰጪ የሆኑ ከውጭ ስናስመጣቸው የነበሩ ማሽኖችንና የማምረቻ መሳሪያዎችን እዚህ ማምረት የምንችልበት አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የሚያመላክቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አሉ ሲሉም አስታውቀዋል። የመለዋወጫ እቃዎች በማምረት ረገድም እንዲሁ እጅግ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ይህ ዘርፍ ባሉበት የገበያ ትስስር ማነቆዎች፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ እንዳላደገ አስታውቀው፣ ይህን ችግር በውይይት መፍታት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በአንድ በኩል ሰፊ የገበያ ፍላጎት አለ፤ ማሽን እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ ዜጎች ፣ ኩባንያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለማሽን ገበያ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉ አምራቾችም አሉ።መንግሥትም ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ለማድረግ ይፈልጋል፤ ዘርፉ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቱ /ጂዲፒ/ው አሁን ካለበት ሰባት በመቶ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ የግድ የማምረቻ ማሽኖችን እያመረቱ ለዜጎች ማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይፈልጋል።

በዚህ መድረክ ማነቆዎቹ ምንድናቸው? እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? ከማን ምን ይጠበቃል? በሚሉት ላይ መነጋገር ያስፈልጋል ሲሉ አመልክተው፣ መድረኩም በአንድ በኩል ለአምራቾቹ ገበያ በማመቻቸት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፤ በሌላ በኩል ማሽን እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ እንደ ልማት ባንክና የመሳሰሉት ተቋማት ከማን ምን ሊያገኙ እንደሚችሉ መረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ እንደ ሚኒስቴሩና ኢንተርፕራይዞች ልማት ይህን ትስስር የመፍጠር ኃላፊነት አለብን ሲሉ ገልጸው፣ ይህ ሥራ በተናጠል የሚሠራ እንዳልሆነም ተናግረዋል።‹‹ምን ዓይነት የቅንጅት ሥራ ሰርተን ነው ማሽነሪዎቹ ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ጠብቀው በተመጣጣኝ ዋጋ ለገዥዎቹ የሚቀርቡት የሚሉትን የቤት ሥራዎች ወስደን እንሠራለን» ሲሉም አስታውቀዋል።

መድረኩ እነዚህን ግቦች የሚያሳካ እንደሚሆን አቶ መላኩ ጠቅሰው፣ መድረኩ እንደተጠናቀቀ ማን ከማን ምን ይገዛል የሚለውን አውቀን በዚያ መሠረት ዝግጅት የምናደርግበትም ይሆናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ አምራች ኢንዱስትሪው ያሉትን እምቅ አቅሞች አስመልክተው አብነቶችን ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን የማዳበሪያ ጆንያም ከውጭ ይመጣ እንደነበር አስታውሰዋል። በቅርቡ የሀገር ውስጥ ጆንያ ማምረቻዎች ይህን መሥራት ይችላሉ አይችሉም በሚለው ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ገልጸው፣ በዚህም ሙሉ በሙሉ ጥራቱን የጠበቀ ጆንያ የሚያመርቱ ወደ ስድስት የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች መገኘታቸውንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም በአንድ ሳምንት ብቻ እነዚህ ኢንዱሰትሪዎች አራት ሚሊዮን ጆንያ እንዲያመርቱ ትእዛዝ ተሰጥቷል።በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫና ከገንዘብ ሚኒስቴር በወረደው ትእዛዝ መሠረት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታት ከእነዚህ አምራቾች ጋር በቀጥታ ግብይት መፈጸም አለበት የሚል ግልጽ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውሰው፣ በዚህ መነሻነትም እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ከኢትዮጵያ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ጋር እንዲተሳሰሩ ተደርጓል ብለዋል።

እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ለኤሌክትሪክና ለመሳሰሉት የሚውሉ ስማርት ምሰሶዎችም/ፓሎች/ ከውጭ እንዲመጡ ይደረግ ነበር።ለዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር አምስት ኩባንያዎች ምሰሶዎቹን ለማምረት ውል እየገቡ ናቸው።ኢንዱስትሪዎቹ ለጊዜው አንድ ሺ የሚሆኑ ምሰሶዎችን እንዲያመርቱ ትእዛዝ ተሰጥቷል።

ለቱሪስቶች የሚሆን ‹‹ሳፋሪ›› የሚባል ተሽከርካሪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚገዛው ከታንዛኒያና ኬንያ እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹እነኚህን ተሽከርካሪዎች እንድንሰራ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀማሪ ናችሁ አትችሉም ሳይሉን በሀገር ውስጥ ያሉትን ኢንዱሰትሪዎች ማበረታት የምንችለው ደፍረን ይህን ማድረግ ስንችል ነው ብለው አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ሰጥተውን ቀሪ አካላቸውን እዚህ ሰርተን ወደ ገበያ እንዲገቡ እያደረገን ነው›› ሲሉም አብራርተዋል።አያይዘውም የኤሌክትሪክ ገመዶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራም በስፋት እየተጀመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማሽነሪዎች እዚህ እየተመረቱ ወደ ጅቡቲና ሶማሌ እየተላኩ ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ ስለዚህ ያልተጠቀምንባቸው እምቅ አቅሞች አሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።ከዚህ አኳያ ለአነስተኛም ለመካከለኛም ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ ማሽኖች በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እንዳለ በተጨባጭ ማረጋገጥ ተችሏል፤ አሁን የሚፈጠሩ ትስስሮችም ይህን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

ስለዚህ የመንግሥት አካላት ሁላችንም በየደረጃው ኃላፊነታችንን በተሟላ መልኩ እንወጣለን፤ አምራቾችና የሊዝ ፋይናንስ ተቋማትም በእያንዳንዱ ምርት ላይ ያሉትን የእናንተን ተፈላጊ መስፈርቶች/ ስፔስፊኬሽን/ በሚያሟላ መልኩ ምርቶቹ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ መሥራት አለባችሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።

ይህ ካልሆነ ካለብን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተዳምሮ የማሽነሪና የመለዋወጫ ገበያና ፍላጎቱን ልናሟላ አንችልም።ይህም መድረክ እነዚህን ግቦች በሚያሳካ መልኩ የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ የተነቃቃና ውጤታማነቱ በግልጽ የሚታይ አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመገንባት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።በዚህም እንቅስቃሴ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ15 ሺ በላይ አዳዲስ አምራች አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መፍጠር ተችሏል።ኢንተርፕራይዞቹም በልዩ ልዩ መልኩ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ አምራቾች የመሥሪያ ቦታ ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የገበያ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አገልግሎት እንዲሟላላቸው ተደርጓል፡፡

መድረኩ የአምራቾች ኢንዱስትሪዎች ዋንኛ አቅም የሆነውን ማሽነሪና መለዋወጫ በራስ አቅም እያመረቱ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንም ሆነ ፈጠራን ከሀገራዊ አቅም ጋር በማጣጣም ቁልፍ አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑትን የማሽነሪ አምራቾችን ለማገዝ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም መፍጠርን ያለመ ነው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ የማሽነሪ አምራቾች በዘመናት በዘርፉ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ በመኖራቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በተናጠልና በግላቸው ለመፍታት ጥረት አድርገዋል፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መፍጠር ከተቻለ በኋላ ደግሞ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመመቻቸት ላይ ይገኛል።በዚህም የማሸነሪ አምራቾች ተሰባስበው ራሳቸውን ከማደራጀት ባሻገር በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ራሳቸውንና ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ናቸው።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ አቅም፣ ምርትና ምርታማነት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማሽነሪ አምራቾች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ብቻ ሳይሆን ማሽነሪ አምራቾችን ከአምራች ኢንተርፕራይዞች እኩል መደገፍ ለዘርፉ ልማት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ32 ሺ በላይ ማሽነሪዎች ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንስ እንዲተላለፉ ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አለባቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ ከሀገር ውስጥ ማሽነሪ አምራቾች የተገዙት ማሽኖች በጣም ጥቂት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።ለዚህም ዋናው ምክንያት በማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎችና በሊዝ ፋይናንስ ተቋማት መካከል ያለው ሰፊ የመረጃና ተቀናጅቶ የመሥራት ክፍተት ነው ብለዋል።

ይህ አካሄድ ከውጭ የሚመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካትና በሂደትም ሀገራዊ የማምረት አቅምን ለማገንባት እንደማያስችል ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሬ አቅምንም የሚፈታተንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራውን እንደሚጎዳም አመልክተዋል።‹‹መድረኩ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢንተርፕራይዝ ልማት በጋራ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ታምርት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ማሽነሪዎችንም ታምርት፤ እኛም እንሸምት›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You