የኢትዮጵያን የ100 ዓመታት የግብርና ታሪክ የሚዳስስ መጽሐፍ ሊመረቅ ነው

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ የ100 ዓመታት የግብርና ታሪክ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የተወሰዱ ርምጃዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን የሚዳስስ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል።

“ኢትዮጵያ ከግብርናና ከምግብ ቀውስ ነፃ ስለመውጣት፤ ተቋማዊ ዝግመተ – ለውጥና የግብርናና ገጠር ልማት ሽግግር ጎዳና” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ እና ተመራማሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) የተዘጋጀ ሲሆን፤ አሳታሚው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ነው።

የመጽሐፉ አዘጋጅ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ መጽሐፉ የግብርናው ዘርፍ አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረጉ 12 ምዕራፎች አካቶ ይዟል። በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም የእርሻ ታሪክ ውስጥ የነበራትን ሚና የሚዳስሱ ሦስት ምዕራፎች ተካተዋል።

መጽሐፉ በኢትዮጵያ የ100 ዓመታት የግብርና ታሪክ ውስጥ የተወሰዱ ርምጃዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን ይዳስሳል ያሉት ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፤በ100 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መንግሥታት እና ተቋማት በግብርናው ዘርፍ የተወሰዱ ርምጃዎች የኢትዮጵያን የግብርና ሥርዓት ምን ያህል ማሻሻል ችለዋል የሚለው በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ተዳስሷል ብለዋል።

መጽሐፉ የግብርናውን ዘርፍ ከጊዜ፣ ከመዋቅር፣ ከተቋም እና ከውጤት አንፃር በስፋት ይዳስሳል ያሉት ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፤ መጽሐፉ እነዚህን ጉዳዮች በአርሶ አደሩ፣ በአርብቶ አደሩ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያመጡት ለውጥ እንደሚያስረዳ ተናግረዋል።

መጽሐፉ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የታተመ ነው። በአማርኛ ቋንቋ የታተመው 347 ገጾች ያሉት ሲሆን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የታተመው ደግሞ 435 ገጾች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በዓለም የግብርና ታሪክ ኢትዮጵያ የረቀቀ ሞፈርና ቀንበር የነበራት እንዲሁም የጤፍ፣ የገብስ እና የበርካታ እህሎች መገኛ ሆና ተገልጻለች። በመጽሐፉም ኢትዮጵያ በዓለም የእርሻ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኗን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች ተጠቅሷል።

በዚህም በኢትዮጵያ የግብርና እድገት ውስጥ የነበሩ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፍትሔ ሃሳቦች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የነበራቸው ውጤት በስፋት ተዳሷል ያሉት ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፤ በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ ምን ምን ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ እና በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ምን አይነት የመፍትሔ ሃሳቦች ማዘጋጀት እንደሚገባ መጽሐፉ ይጠቁማል ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You