የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ፈተና የሆኑበት እውነታ የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህም እንደ ሀገር ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መንገጫገጮች ውስጥ ለመግባት የተገደድንባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።
ለውጡን ተከትሎ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችን በሠለጠነ መንገድ በውይይትና በንግግር መፍታት አለመቻላችን ችግሩ ሀገራዊ ገጽታ እንዲኖረው አድርጓል፤ የሀገርን ህልውና ስጋት ውስጥ ከመጨመር ባለፈ ለዘመናት ተከባብሮና ተፈቃቅሮ የኖረውን የሕዝባችንን ማህበራዊ መስተጋብር ተፈታትኖታል ።
እነዚህ የጥላቻ ንግግሮች እና በሀሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎች የበሬ ወለደ ትርክትን ጨምሮ የፖለቲካ አመራሮች ፣ግለሰቦች ፣ቡድኖች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያነጣጠሩ ፣ ዘመናትን እንደ ሕዝብ ያሻገሩንን የቀደሙ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ እሴቶቻችን እና ብሔራዊ ማንነታችንን የተገዳደሩ ናቸው።
ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በሕዝቡ ውስጥ በማስረጽ በሚፈጠር ሀገራዊ ትርምስምስ የፖለቲካ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን በሚሉ፤ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ የተገዛ ፣ ማንንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የማይችል የጥፋት መንገድ ሀገርና ሕዝብን ያልተገባ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል ።
በዚህ ሀገርን የማተራመስ የጥፋት መንገድ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ማደጋችን የሚያሰጋቸው ኃይሎች ተሳትፈውበታል። ከሚያደርጉት የገንዘብ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ ጋር በተያያዘም ለጥፋት ኃይሎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን ችግሩ እየገነገነ እንዲሄድ አድርጎታል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሺዎች የሞቱበትና የቆሰሉበት ጦርነት ውስጥ ገብተናል፤በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና የሰላም እጦት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎቻችን ለሞትና ለአካል መጉደል ተዳርገዋል፤በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ከቤት ንብረት ተፈናቅለው ምጽዋት ጠባቂ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
“ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን” በሚል ሀገራዊ መነቃቃት ማግስት በጥላቻ ንግግሮች እና በሀሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎች በፈጠሩት ግራ መጋባት ፤በቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት እና ንብረት ለውድመት ተዳርጓል። ችግሩ የፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትም ተመልሰን እጃችንን ለምጽዋት እንድንዘረጋ ተገድደናል።
በዚህ ያልተገባ መንገድ ለሀገራቸው ብዙ የሠሩ ባለውለታዎች ፤ለሀገር የነገ ተስፋ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚተጉ ግለሰቦችን ጨምሮ የትናንት የጋራ ታሪካችን አውራዎች ሳይቀሩ በጥላቻ ንግግሮች እና ዘገባዎች ተብጠልጥለዋል፤ጸያፍ ስድቦች ፣ዘለፋ እና እርግማኖች ደርሰውባቸዋል።
ለዚህም ዘመኑ ያፈራቸው ዲጅታል ማህበራዊ ሚዲያዎች እያበረከቱት ያለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ቢሆንም፤ ሕዝባችን መረጃዎችን በሰከነ መንፈስ ማየት የሚያስችል ዝግጅት አለመፈጠሩ ችግሩ ግዝፈት አግኝቶ ጥፋቱ እንደ ሀገር ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን እንድንከፍል አድርጎናል።
በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ መኖሪያቸውን ያደረጉ በተቃርኖ የተሞሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ፤በሀገር ውስጥም ከራሳቸው ማህበራዊ ማንነት ጋር የተጋጩ ፅንፈኛ ኃይሎች እና ቡድኖች ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደረግን ጽንፍ የወጣ ፕሮፓጋንዳ እንደ አንድ የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው መውሰዳቸው እና ለዚህ የሚሆን ማንነት መላበሳቸው ችግሩን አግዝፎታል።
ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው የስድስት ወራት የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የተመለከተ ሪፖርት ያመላከተውም ይህንኑ እውነታ ነው። በሀገሪቱ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ እያስከተለ ያለው አደጋ ሰፊና ውስብስብ ሆኗል። ለችግሩም የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሚና ጉልህ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት የተሰራጩት የጥላቻ መልዕክቶች ለአመጽና ለጥቃት የማነሳሳት፣ የግለሰብን ሰብዕና የመጉዳት፣ የማህበረሰብን ባህልና ወግ በመናድ የሕዝብን አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸርን የሚያስከትሉ ሆነው መታየታቸውን አመልክቷል።
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ እያስከተለ ካለው አደጋ ሰፊና ውስብስብ እየሆነ ከመምጣቱ አንጻር በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸውን ማህበራዊ ትስስር አውታሮች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አዋጁን ለማስፈጸም ሚና የተሰጣቸው መንግሥታዊ አካላት፣ የሲቪል ማህበራትና ኅብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል።
በተለይም መላው ሕዝባችን የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎች የሀገርን ሰላምና መረጋጋት ፤የሕዝባችንን የዘመናት አብሮ የመኖር እሴቶች በማጥፋት በአቋራጭ ለመያዝ የሚደረግ ዛሬ ላይ ጭምር ያልተሻገርነው የተበላሸ የፖለቲካ እሳቤ አካል በመሆኑ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ፤ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፈጥኖ መንቃት ይኖርበታል።
ዛሬን በሰላም መኖር ፤በነገም ተስፋ መሰነቅ የሚቻለው ፤ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ ስትኖር ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ከሚሰማቸው የጥላቻ እና የሀሰት መረጃዎች እራሱን መጠበቅ፤ ከቀደሙ የሞራል እሴቶቹ ጋር ያለውን ቁርጠኝነት ማጠንከር ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም