“የመረጃ አሰጣጣችን የተዓማኒነት መጠኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል” አቶ ፈጠነ ተሾመ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በእያንዳንዱ ወቅት የሚኖረውን አጠቃላይ የአየር ፀባይ ትንበያ በመስጠት የሚታወቅ ተቋም ነው። መረጃው፤ ያለውን እድልና ስጋት አመላካች በመሆኑ ከሚሰጠው መረጃ በመነሳት የአየር ፀባይ ሁኔታው በሚያመጣው እድል መጠቀም የሚጀምር ሲሆን፣ ከሚመጣው ስጋት ደግሞ በመጠንቀቅ ዝግጅት ይደረግበታል።

ከዚሁ ከአየር ሁኔታና የአየር ጸባይ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን ከኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከአቶ ፈጠነ ተሾመ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። በቆይታውም ስለ አየር ሁኔታና ጠባይ ምንነት፣ ተቋሙ ስለሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ፣ የበልግ ዝናብን በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ፈጠነ ተሾመ መረጃ አግኝቷል። መልካም ንባብ።

 አዲስ ዘመን፡- የአየር ትንበያ መረጃ ሲባል የሚያካትተው ምንድን ነው?

አቶ ፈጠነ፡- የአየር ትንበያ ምንነትን ከመጥቀሴ በፊት የአየር ሁኔታ እና የአየር ጸባይ የሚባሉ ነጥቦች አሉ። የአየር ሁኔታ ሲባል የአጭር ጊዜ ሲሆን፣ በቀኑ ውስጥ የሚለዋወጠውን የአየር ሁኔታ የሚመለከት ነው። የአየር ጸባይ ሲባል ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ የሚታይ የአየር ንብረት ሁኔታ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። እነዚህን ነገሮች ለመለየት ሁለቱንም አጣምሮ የሚያጠናው ሚቲዎሮሎጂ የሚባለው ነው።

ሚቲዎሮሎጂ ሲባል የአየር ሁኔታንና የአየር ጸባይ መረጃዎችን ይሰበስባል፤ የሚሰበስበውም መረጃ ከምድር በታች ከአንድ ሜትር ጀምሮ ያለውን የአፈር ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ በአካባቢ አየር ውስጥ ደግሞ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ድረስ በተለያየ ደረጃ ያለውን የሙቀት መጠን፣ የአየር ግፊት፣ የነፋስ ፍጥነት፣ የዝናብ ሁኔታና መጠንን ነው።

የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ የሚሰጠው በሚቲዎሮሎጂ መረጃ ላይ በመመስረት ነው። መረጃዎቹ ከገጸ ምድር በታች፣ በገጸ ምድርና በካባቢ አየር ውስጥ ያሉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ተተንትነውና በባለሙያው ተጠናቅረው በጥሬ መረጃ የሚሰጡ አሉ፤ እንዲሁም ወደትንበያ የሚቀየሩ አሉ።

ስለዚህ ወደፊት እያንዳንዱ ተመራማሪ የአየር ሁኔታንና የአየር ጸባይ መረጃን በተመለከተ ማጥናት የሚፈልግ በሚቲዎሮሎጂ መረጃ ላይ ይመሰረታል። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመላ ሀገሪቱ ከአንድ ሺ 300 በላይ የገጸ ምድር የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ያሉትም ለዚህም ነው። ከዛ በተጨማሪ በዘመናዊ መልክ አውቶማቲክ የሚቲዎሮሎጂ መሰብሰቢያ የሚባሉ በየ15 ደቂቃ ልዩነት ዋናው መሥሪያ ቤት ከሚገኘው ሰርቨር ጋር ተገናኝተው የሚሰጡ መረጃዎች አሉን።

ሌላው የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር የሚባለው ደግሞ 250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለውን የሚቲዎሮሎጂ መረጃን የሚሰበሰብ ነው። ስለዚህ ሽፋኑ እንደጣቢያው ወይም እንደ መሳሪያ ዓይነት ልዩነት አለው። እንዲህም ሲባል አንደኛው ዘመናዊ በሆኑ መሳሪያዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ሲሆኑ፣ ሌላው ደግሞ በሰው መረጃ አቀባይነት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ናቸው። እነዚህ ተደራሽነታቸው ውስን የሆኑ ቦታዎች ላይ ነው።

ሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ከመስጠቱ በፊት መሠረት የሚያደርገው የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ላይ ነው። መረጃ ከሌለው ትንበያ መስጠት አይችልም። ስለዚህ የሀገር ውስጥ መረጃን ያያል፤ ሌላው የአየር ጸባይና ሁኔታ በሀገራት ዳር ድንበር የሚወሰን አይደለም። ተሻግሮ የሚሄድ ነው። ስለዚህ ሕንድ ውቂያኖስ፣ አትላንቲክ ውቂያኖስ፣ በቀይ ባህር፣ በሰሃራ በረሃ እንዲሁም ባህረ ሰላጤ አካባቢ ያለው የአየር ጸባይ የእኛን የበጋ፣ ክረምት እና የበልግ ዝናብን ሁኔታ በመጨመርም ይሁን በመቀነስ ደረጃ ወሳኝ ሚና አላቸው። ይህ ማለት ከኢሊኖ እና ላሊና ጋር የሚያያዝ ነው። በመሆኑም ይህን ሁኔታ ለሀገር ውስጥ መረጃ እንደ አንድ ግብዓት እንጠቀማለን።

በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ትንበያ ማዕከላት የሚተነበየውን በሕንድ ውቂያኖስ፣ በአትላንቲክ ውቂያኖስ እንዲሁም በቀይ ባህር ላይ የሚታየው የባህር ወለል መሞቅና መቀዝቀዝን ኢትዮጵያ ከግምት ውስጥ ታስገባለች፤ እንዲሁም በተመሳሳይ ዓመታት ከአየር ጸባይ ጋር ተያይዞ የተከሰተውንም ከግምት በማስገባት ከየትኞቹ ዓመታት ጋር ይመሳሰላል በማለት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ትንበያ እንሰጣለን። የአጭር ጊዜ ትንበያ የምንለው ከሰዓታት ጀምሮ እስከ ሶስት ቀን ድረስ ያለውን መረጃ ነው። የመካከለኛ የሚባለው ደግሞ ከሶስት ቀን እስከ አስር ቀን ያለውን ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ የሚባለው ከአንድ ወር ጀምሮ እስከ ወቅት ድረስ ያለው ነው። እኛም መረጃ የምናደርሰው በሶስቱ የጊዜ ሰሌዳዎች ዙሪያ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ የምንሰጠው የረጅም ጊዜ ትንበያውን ነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ባሉት መልኩ የተጠናቀሩትን የአየር ትንበያ መረጃዎች ለሚመለከተው አካል በአግባቡ ማድረስ ፋይዳው የት ድረስ ነው ይላሉ?

አቶ ፈጠነ፡– ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። በዚህች ምድር ላይ ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የአየር ሁኔታ ነው። ስለዚህ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ አንደኛ ሕይወትንና ንብረትን ከአደጋ ለመታደግ ወሳኝነት አለው። ሕይወትንና ንብረትን ከአደጋ ለመታደግ ስንል አንዳንድ ጊዜ ድርቅ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከከፍተኛ ዝናብ የተነሳ የጎርፍ አደጋ ያጋጥመናል። ሁለቱም በአግባቡ ካልተመሩ በሕይወትና ንብረት ላይ የራሳቸው የሆነ አደጋ ያሳርፋሉ።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ የተከሰቱትን የድርቅ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን ብናይ በቅርቡ የቦረና፣ የጉጂ፣ የባሌ ቆላማ አካባቢዎች ላይ እና ሱማሌ ያጋጠመው ይጠቀሳል፤ በተለይ የቅርቦቹን የድርቅ ክስተት ስናጤን ለአምስት ተከታታይ ወቅት ዝናብ ሳያገኙ በመቅረታቸው የመጣ ነው። በዚህ ሳቢያ ደግሞ የአርብቶ አደሩ እንስሳት በብዛት አልቀዋል።

ድርቅ የሚያጋጥመው ለምንድን ነው? የሚለውን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በምናይበት ጊዜ የኢትዮጵያን የአየር ሁኔታ የሚወስኑ አስቀድሜ የጠቀስኳቸው የሕንድ ውቂያኖስ እና የአትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ የተከሰቱት ክስተቶች በመኖራቸው ናቸው። ይህም ማለት የባህር ወለል ሙቀት መጨመርና መቀነስ ነው። ስለዚህ የኢሊኖ እና ላሊና ክስተት በምናይበት ወቅት በተለይም ኢሊኖ በጋ እና ክረምት ላይ በሚከሰትበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን እንዲኖር ያደርጋል።

እንደሚታወቀው በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች የክረምት ዝናብ የሚያገኙ አይደሉም፤ የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍል በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው፤ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። ለቦረና፣ ጉጂ፣ ሱማሌና በቀድሞ አጠራር የደቡብ ክልል በተለይ የኮንሶና ቡርጂ አካባቢዎችን ብንወስድ በልግ ዋንኛ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። የክረምት ወቅት ደግሞ ለእነርሱ ደረቅ ጊዜ ነው። በመሆኑም የክረምት ወራትን እንደተቀረው የሀገሪቱ ክፍል አይጠብቁም።

የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢ እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍልን ደግሞ በምናይበት ጊዜ ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። የተወሰነ ሰሜን አጋማሽ ምሥራቃዊ ክፍል የእነራያና ወሎ አካባቢ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። ስለዚህ ለእነርሱ በጋ ደረቅ ወቅት ነው። በአካባቢያቸው በበጋ ወቅት ዝናብ ቢዘንብ የሚባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ነው። የምዕራብ አጋማሹ እንደ እነኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ ያሉ አካባቢዎች ደግሞ በዓመት ውስጥ እስከ ስምንት ወራት ድረስ ዝናብ የሚያገኙ ናቸው። በበልግ ወቅት ዝናብ ብዙ አይጠበቅም።

አሁን ወቅቱ የበልግ ነው፤ በልግ ደግሞ በኢሊኖ ተጽዕኖ ስር ስለሆነ ቦረና ላይ የምናው ዓይነት ድርቅ አይኖርም። ስለዚህ ትንበያውን ቀድመን በምንሰጥበት ጊዜ ሁሉም ይዘጋጃል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የግብርና ሴክተሩ፣ የውሃ ሴክተሩ እንዲሁም የጤና ሴክተሩ ሲሆኑ፣ እነዚህም ዝግጅት ያደርጋሉ። ለዚህም ሲባል ባለፈው ጥር ወር ከየሴክተሩ ለተውጣጡ ወደ 300 አካላት ከየካቲት እስከ ግንቦት የአየር ትንበያ መረጃ ሰጥተናል። ለሁሉም ሴክተር እንደየሥራው ባህሪ የተለየ ጥቅም ያለው በመሆኑ እንደሚያገኘው መረጃ ዓይነት የየራሱን ዝግጅት ማድረግ ያስችለዋል።

መረጃው በተለይ በቅርቡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረ የበጋ ስንዴ ሥራ በአግባቡ ለማስኬድ ያስችል ዘንድ መረጃን በመጠቀም ከወዲሁ ውሃ መያዝ የሚገባ ከሆነ በመያዝ ጭምር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ማለት ነው። ጤና ላይ ለምሳሌ የወባ ሥርጭትን አስመልክቶ የተተነበየውን መረጃ ከግምት በማስገባት ሴክተሩ እንዲዘጋጅ እድል ይሰጠዋል። በዚህ መሠረት ከግብርና፣ ከውሃ፣ ከጤና፣ ከአደጋ ስጋት አመራር ጋር የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕቀፍ ብለን የጋራ ስምምነት ተፈራርመናል። ስለዚህ በየጊዜው መረጃዎቻችንን ይጠቀማሉ። ይህን በማድረጋቸው አንደኛ የአደጋ ተጋላጭነትን ይቀንሱበታል፤ ሁለተኛ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋሉ።

ውሳኔ ሰጪ አካላት በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ላይ ብቻ ተነጋግረው አያበቁም። ታች ያለው ላይ ችግር እንዳይሆን የክልል ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች የሚሳተፉበት፣ የሚመለከታቸው የአደጋ ስጋትና የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙበት ውይይቶች ይደረጋሉ። በዚያ ውይይት ወቅት ሚቲዎሮሎጂ መረጃ ያቀርባል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጎርፍ በሚበዛበት ወቅት “የከፍተኛ ተፋሰስ አስተዳደር ምክር ቤት” በሚል ስያሜ የሚታወቅ ተቋም አለ፤ ይህ ተቋም ጎርፍ የሚያጠቃቸውን አካባቢዎች ታሳቢ በማድረግ ለምሳሌ አዋሽ ከመነሻ ጀምሮ እስከ መድረሻ እንዲሁም የጣና በለስ፣ ባሮ አኮቦ፣ የገናሌ ተፋሰሶች እነዚህ ችግር እንዳያመጡ አቅጣጫዎች የሚሰጡበት ሁኔታ አለ። በተለይ የሚከተሉት ስትራቴጂ ሕዝብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ቀድሞ የመከላከል ነው።

ሌላው የትንበያ ፋይዳው ለየኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ነው። ለባለስልጣኑ የትንበያ መረጃ የሚሰጠው የረጅም ጊዜ ትንበያ ተጠብቆ ሳይሆን ከሰዓታት ጀምሮ እስከ አጭር ቀናት ድረስ ነው። ተቋማችን ካለው የሰው ኃይል ውስጥ ወደ አንድ መቶ የሚጠጋ የሰው ኃይል ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ነው። ስለዚህ የትኛውም አውሮፕላን ከመነሳቱ በፊት እና ከማረፉ በፊት እንዲሁም በበረራ ወቅት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ይደርሰዋል። እንደሚታወቀው ብዙ ጊዜ የአውሮፕላን አደጋ የሚከሰተው 70 በመቶው ከአየር ጸባይና ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነው።

እኛ የባህር በር ስለሌለን ነው እንጂ ማሪን ሚቲዎሮሎጂ ተብሎ በመርከቦች እና በጀልባዎች ላይ ሚቲዎሮሎጂ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ይተከሉና ከፍተኛ የባህር ላይ ሞገድ በሚነሳበት ወቅት መረጃ ይሰጣሉ፤ ለምሳሌ ሞገዱ ምን ጊዜ ይመጣል? የሚለውን መተንበይ ስለሚያስፈልግ ለዛ ሲባል መረጃው ይሰጣል። በኢትዮጵያም በኩል የባህር በሩ ከተሳካ በዘርፉ ጥሩ የሆነ መረጃን በማቀበል ሱማሊያን ማገዝ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የሚያደርሰው መረጃ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ጠቀሜታው ለግብርና ዘርፉ ብቻ እንደሆነ ይታሰባል። ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ ፈጠነ፡– በርግጥ መረጃው ለበርካታ ዘርፍ ወሳኝ ነው። ለግብርናው፣ ለጤናው፣ ለአደጋ ስጋት አመራሩ እና ለሌሎችም ሴክተሮች ጠቀሜታው የጎላ ነው። ለምሳሌ ለአደጋ ስጋት አመራሩ በቀጣዩ ዓመት ምን ያህል ተረጂ እንደሚኖረውና ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት ያመቸው ዘንድ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይ ከውሃ አስተዳደር ጋር ተያይዞ ለምሳሌ በግድቦቹ ያለው የውሃ መጠንን ይዞ ለማቆየትም ሆነ ለማስተንፈስ መረጃው ወሳኝ ነው። ሌላው ደግሞ የአየር በረራ አገልግሎትም እንዲሁ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መረጃ ለሁሉም አስፈላጊ ቢሆንም፤ እነዚህ የጠቀስኳቸው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ በጣም ወሳኝ በሆነ መንገድ የሚያስፈልጋቸው ሴክተሮች ናቸው። በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅትም የአየር ጸባይ አገልግሎት ማዕቀፍ በሚል የተፈራረምናቸው ከእነዚሁ ሴክተሮች ጋር በመሆን ነው።

በተጨማሪ ደግሞ ከተሞችም እንዲሁ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዳይስተጓጎል መረጃው አስፈላጊው ነው። ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ዘርፉ አንድን ሕንፃ በሚያንጽበት ወቅት ፈጥኖ ከመሠረቱ መውጣት ያለበትን የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መረጃው ሊያመላክተው ይችላል። እንዲሁ የመንገድ ሥራም ሊሆን ይችላል የአየር ሁኔታውና ጸባዩ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍበት ስለሚችል ቀድሞ ለመጠንቀቅ መረጃው ወሳኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መረጃ ፖሊሲ እስከማስቀየር የሚደርስ እንደሆነ ይነገራልና እዚህ ላይ ማብራሪያ ቢሰጡን?

አቶ ፈጠነ፡- ለፖሊሲ አውጪዎች ለምሳሌ አንድ ሀገር የኢነርጂ ፖሊሲ ይኖረዋል፤ የእኛ የኢነርጂ ምንጭ ታዳሽ

ኢነርጂ የሚባለው ነው። ይህ ታዳሽ ኢነርጂ ደግሞ መሠረት ያደረገው አንዱ ውሃ ላይ ነው። እንዲያውም ኃይል ሲታሰብ የእኛ ሀገር በብዛት የተመሰረተው ውሃ ላይ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ንፋስ ሲሆን፣ ሶስተኛው ደግሞ የእንፋሎትና የፀሐይ ኃይል ነው። እነዚህ የኃይል ምንጮች ሁሉ የሚቲዎሮሎጂን መረጃ የሚፈልጉ ናቸው።

ስለዚህ ትንሽ ሰፋ የሚል ስለሆነ ውሳኔ ሰጪ አካላት ብዙ ጊዜ እቅዶቻቸውን እንደየሁኔታው ይከልሳሉ። ለምሳሌ ዘንድሮ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከሚሰጠው መረጃ በተጨማሪ በሚከሰተው የዝናብ እጥረት ውስጥ ጣልቃ እየገባን መምጣት ጀምረናል። ለምሳሌ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር በመነጋገር ዳመናን ወደዝናብ (ክላውድ ሲዲንግ ቴክኖሎጂ) የመቀየር ማለትም ዳመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂን መጠቀም ጀምረናል። ይህ ማለት ሁሉም ዳመና ዝናብ ሰጪ ነው ማለት አይደለም። ቁልል ደመና ተብሎ የሚጠራው መኖሩ ሲረጋገጥ ነው። ስለዚህ ይበተን የነበረ ዳመና በዝናብ መልክ እንዲወርድ ይደረጋል፤ ይህንን ላለፉት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ አድርገናል።

ብዙ ጊዜ ከአረብ ሀገር ባለሙያዎች ይመጡ የነበረው በልግ ላይ ነው። በዚህ ዓመት ግን አልጠራናቸውም። ምክንያቱም ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚጠበቅ ስለሆነ ነው። ከዚህ የተነሳ የእቅድና የአቅጣጫ ለውጥ አድርገናል ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት እንኳ በአንዳንድ ቦታ ላይ ጎርፍ የሚያስከትል ዝናብ ይኖራል ብለን ስለጠበቅን በዚህ ላይ ዳመናን ወደዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን መጠቀሙ አግባብ አይደለም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፓርላማ ላይ ዘንድሮ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የምንጠብቅ ስለሆነ ዳመናን የማዘነቡ ነገር እንደማይኖር አስረድተዋል። ስለዚህ የእቅድ ለውጥ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ለምሳሌ መሬታችንን በመስኖ ማልማት ቢፈለግ በቂ የሆነ የዝናብ ውሃ ስለሚኖረን ሌላ ፍለጋ አንሄድም። በሌላ በኩል ደግሞ ምርት አሰባሰብ ላይ ብክነት እንዳይመጣ የመረጃው በአግባቡ መድረስ ሚናው ላቅ ያለ ነው። በቂ መረጃ የማይኖረን ከሆነ ምርት ሊባክን ይችላል፤ መረጃው ካለ ግን ተማሪዎችንም ሆነ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል በማስተባበር ምርት እንዲሰበስቡ ማድረግ ይቻላል። በዋናነት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜን ትንበያን በመጠቀም እቅዶቻቸውን መከለስ ይችላሉ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አኳያ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል ማለት ይቻላል?

አቶ ፈጠነ፡- እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቴክኖሎጂው እየተለወጠና አቅሙንም እያጠናከረ መጥቷል። የእኛም ተቋም ከቴክኖሎጂ አንጻር አቅሙን እያጎለበተ የመጣ ነው። ከአንድ ሺ 300 በላይ በሰው ኃይል መረጃ የሚሰበሰብባቸው ጣቢያዎች አሉን። የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያዎች በየትኛውም ዓለም ስታንዳርዱን የጠበቀ በመሆኑ ተመሳሳይ ነው። ስታንዳርዱን የሚወስንልን የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያም የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል ናት። በመሆኑም ከዚያ ወጣ ያለ ብዙ አሰራር አይኖረንም።፡

ነገር ግን ቴክኖሎጂው በየሶስት ሰዓቱ ልዩነት ተመልካች እየሔደ መረጃ የሚሰበስብበትን አሰራር ለማስቀረት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው። ሚቲዎሮሎጂ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በሰው የሚሞላ መረጃን ሲጠቀም ነበር። ይህ እኛ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የሚሰራበት ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ዓለም ወደዘመናዊነት እየተሸጋገረ ነው። ለዚህ ማሳያ ከሆኑት አንደኛ ሰው አልባ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ (Automatic Weather Sta­tion) የሚባለው ሲሆን፣ ከየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ ለምሳሌ ጎዴ ላይ ወይም ሁመራ ጫፍ ተተክሎ በ15 ደቂቃ ልዩነት እኛ ሰርቨር ላይ መረጃውን የሚያደርስ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መሳሪያ 300 ጣቢያ ላይ ተክለናል።

ሁለተኛው ደግሞ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ነው። ቀደም ሲል ራዳር አልነበረንም። አንደኛ ከዋጋ አንጻርም በጣም ውድ ነው። አንድ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር እስከ 130 ሚሊዮን ብር ይፈጃል። ስለዚህ አንድ ሻውራ በሚባል ቦታ ጣና በለስ አካባቢ ያለውን የጎርፍ ክስተትን እንዲሁም ለዳመና ማዝነብ የሚሆኑ የዳመና ዓይነቶችንም ለመለየት የሚጠቅመን መሳሪያ ነው።

ከዳመና ማዝነብ ጋር የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረግነው ወደጣና በለስ አካባቢ ነው። አካባቢው የተመረጠበት ምክንያት ራዳሩ እዛ አካባቢ ስላለ ነው። መሳሪያው ቀደም ሲል የተተከለ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ከመጡ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደሥራ በማስገባት ከአራት ዓመት በፊት እንደየሁኔታው እየታየ ጠቀሜታ ላይ እንዲውል ማድረግ ችለናል።

በኋላ ላይ ደግሞ ከፊንላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሶስት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ ለመተከል ወደየቦታው በመሔድ ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር አራት ራዳር ማድረስ ተችሏል። ይህ ራዳር በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለውን የዝናብ መጠን፣ ሊመጣ ያለውን የጎርፍ አደጋ፣ ሊበለጽግ የሚችል የዳመና ዓይነት ለመለየት እንዲሁም ለአውሮፕላን በረራ ስላለው የአየር ሁኔታ ምልክት የሚያሳይ ነው። ይህ መሳሪያ ሁለተኛው የዘመናዊነት መገለጫ ነው።

ሌላው የከፍታ አየር መመዝገቢያ ራዲዮሶንዴ ባሉን (Radiosonde balloon) የሚባለው ነው። መሳሪያውን ከባቢ አየር ውስጥ በመልቀቅ ያለውን መረጃ እየመዘገበ እንዲልክ የሚደረግ ነው። በተለይም ምን ዓይነት የእርጥበት ዳመና አለ? ምን ዓይነት የሙቀት መጠን አለ? ምን ዓይነት የንፋስ ፍጥነትና አቅጣጫ አለ? የሚለውን ይመዘግባል። ወደ ከባቢ አየር ለሚለቀቀው ባሉን እስከ 300 ዶላር ወጪ ያስወጣል።

ሌላው የሳተላይ መረጃ የሚባለው ነው። እንደገና ከዓለም አቀፍ ሚቲዎሮሎጂ ማዕከላት ጋር በመተባበር መረጃዎችን በነፃ እናገኛለን። ምክንያቱም ለዚህ ስምምነት አለን። ለዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባልነት ዓመታዊ መዋጮ እናዋጣለን። ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ጋር በመነጋገርም ሳተላይቶችን ማምጠቅ ችለናል።

ለአየር መንገድ ከራሱ ባህሪ አንጻር በአራት ዓለም አቀፍ በረራን በሚያስተናግዱና 18 የሀገር ውስጥ በረራን ለሚያስተናግዱ የአየር ጣቢዎች ለእያንዳንዳቸው አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ መመልከቻ ሥርዓት (Auto­matic Weather Observing System) የሚል ስያሜ ያለው መሳሪያ ተተክሏል። ይህ መሳሪያም ዘመናዊ ነው። ከዚህ በፊት መረጃው ይሰበሰብ የነበረው በሰው ነው። አየር መንገዶቹ በሚቋቋሙበት ወቅት በጋራ የምንሰራው እነዚህን ነገሮች አስበን ነው። ስለዚህ የመረጃ አሰጣጣችን የተዓማኒነት መጠኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በሰው ኃይሉ ላይም የተሠሩ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ወደ 61 ባለሙያዎችን በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቀናል። እንደገና ደግሞ በቻይና እና በሌሎች ሀገራትም ጭምር ወደ ሰባት የሚሆኑ ባለሙያዎች የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ኢንስቲትዩቱ በአንድ በኩል አገልግሎት ሰጪ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የምርምር ተቋምም ሆኖ እንዲሰራ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ከሚቲዎሮሎጂ አንጻር ከሀገራት ጋር ያለው ትስስር ምን ይመስላል?

አቶ ፈጠነ፡- እንደሚታወቀው ያለን ትስስር ከሚቲዎሮሎጂ አንጻር ነው። የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል ነን። በዚህ ድርጅት ውስጥ ሚናችን ከፍ ያለ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍ እና በቀጣናው ላይ ያላት ተሳትፎ ትልቅ ነው።

በዚህ መሠረት የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ድርጅትን በመወከል አባል በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ። ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው 27 መቀመጫ ነው። ከዚህ ውስጥ አፍሪካ ዘጠኝ ወንበር አላት። ከዘጠኙ አፍሪካ ሀገራት ወንበር ውስጥ ደግሞ አንዱ የኢትዮጵያ ነው። እኤአ ከ2015 ጀምሮ ቦታችንን ሳንለቅ በየአራት ዓመቱ የተካሔዱትን ያለፉትን ሁለት ምርጫዎች ማሳካት ችለናል።

ሌላው ደግሞ በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ውስጥ ስድስት ቀጣናዎች አሉ። ቀጣና አንድ ተብሎ የሚጠራው አፍሪካ ሲሆን፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው። እርስ በእርስ እየተመካከሩ ከተቻለ በስምምነት፤ ካልሆነ በድምጽ ብልጫ ይመረጣል። እንደ አፍሪካ ከተወሰደ ብዙ ነገሮቻችንን እንድንጨርስ ያደረግነው በስምምነት ነው። በተለይም በምርጫው አካሄድ እጩዎቻችንን ተስማምተንበት ያቀረብንበት መንገድ አውሮፓን ዴሞክራሲ ያስተማርን የሚያስብለን ነው።

በቅርቡ የዛሬ ዓመት ኢትዮጵያ ላይ እንዲሁ የአፍሪካ ቀጣና ምርጫ ተካሒዶ ነበር። ምርጫውን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ከሥራ አስፈጻሚነት በተጨማሪ በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት በመሆን እየሠራን እንገኛለን። የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽሕፈት ቤትም ያለው በሀገራችን ኢትዮጵያ ነው። ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በፊት ቡሪንዲ የነበረ ቢሆንም፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ወደ ጄኔቫ ተዘዋውሮ ነበር።

ጽሕፈት ቤቱ ወደአህጉሩ ይመለስ በሚል የተወሰነ በመሆኑ በሀገራቸው እንዲሆን አስር ሀገራት ተወዳድረው ነበር። ከእነዚህ አስር ተወዳዳሪ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና ግብጽ የተለዩ ሲሆን፣ እኛ እነዚህን በምርጫው አሸንፈን ጽሕፈት ቤቱን ወደሀገራችን ማምጣት ችለናል። ኢትዮጵያ ሊያስመርጣት የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ስለነበሩ ጽሕፈት ቤቱ እኤአ በ2016 አዲስ አበባ መሆን ችሏል።

ሌላው አሜሪካ ሀገር የብሔራዊ የውቂያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር (National Oceanic and At­mospheric Administration) የሚባለው የአፍሪካ ዴስክ ባለሙያዎቻችንን የአጫጭር ጊዜ ስልጠና ጭምር በመስጠት ያግዘናል። ከእነርሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን። ከኢጋድ ጋር የኢጋድ የአየር ጸባይ ትግበራ ማዕከል የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ (IGAD Climate Prediction) የሚባል አለ፤ እዚያ ላይ ከፍተኛ ሚና ስንጫወት ነበር። ሌላው የአፍሪካ ሜትሮሎጂ ልማት ማዕከል (African Center of Mete­orological Application for Development) ከሚባለው ጋርም ጥሩ ሥራ እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በበልግ የሚጠበቀው የአየር ሁኔታና ጸባይ እንዴት ይገለጻል? ይዞ የመጣው እድል ነው ወይስ ስጋት?

አቶ ፈጠነ፡- ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ሶስት ወቅቶች አሏት። አንደኛው ክረምት ሲሆን፣ ከሰኔ እስከ መስከረም ያለውን የሚያጠቃልል ነው። ሁለተኛው በጋ ሲሆን፣ ከጥቅምት እስከ ጥር ወር ያለውን የሚይዝ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የበልግ ወቅት ሲሆን፣ ከየካቲት ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር ያለውን የሚያጠቃልል ነው። እነዚህ ወቅቶች እንደየአካባቢው የሚለያዩ ሲሆን፣ አንዱ ጋ ያለው የዝናብ ወቅት ክረምት ሲሆን፣ ሌላው ጋ ደግሞ በልግ ላይ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ እነዚህ ወቅቶች ከመግባታቸው በፊት ትንበያ ይሰጣል።

የዘንድሮው የበልግ ወቅት የሚኖረውን የዝናብ መጠንና ያም የዝናብ መጠን በውሃ፣ በግብርና፣ በአደጋ መከላከል፣ በጤና ሴክተር ላይ ጭምር የሚኖረውን አሉታዊና አዎንታዊ ተጽዕኖ በተመለከተ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ ላይ መረጃው ተሰጥቷል። እናም በዚያን ወቅት በሰጠነው ትንበያ መሠረት የበልግ ዝናብ ቀድሞ ሊገባ እንደሚችል እና ከአወጣጥ አንጻር ደግሞ ሊዘገይ እንደሚችል ጠቁመናል፤ ይህም ማለት ከክረምት ወቅትም ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ለማመላከት ሞክረናል።

በልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚጠበቅ፤ በበልግ ወቅት ከሚጠበቀው ዝናብ የተለየ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚኖር፣ በሌሎቹም አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚሆን ትንበያ ተሰጥቷል።

ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የተገለጸው ከግብርና አንጻር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ መቀጠል ሲሆን፣ እንዳለፉት የበልግ ወቅቶች የዝናብ እጥረት የማይታይበት መሆኑን ለመግለጽ ተሞክሯል። ግማሽ ያለፉትን ሁለት ወራት የካቲትና መጋቢት አፈጻጸማቸውን ገምግመን የሚጠበቀውን ይፋ አድርገናል።

የሚጠበቀው መልካም አጋጣሚዎች አሉት። ይኸውም ቦረና፣ ሱማሌ እና ጉጂ አካባቢዎች ዘንድሮ እንዳለፈው ጊዜ ለተከታታይ አምስት ወቅት ያጡትን ዓይነት የዝናብ እጥረት ስለማያጋጥም ለአርብቶ አደሩ የምስራች ነው። እነርሱ የሚፈልጉት ወቅት ይህን ወቅት በመሆኑ በዚህ ወቅት ዝናብ አለ፤ ክረምት ላይ ግን የእነርሱ በጋ ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ በሚያገኙት ዝናብ ውሃ መያዝ የሚያስችል ግድቦችን በመሥራት ውሃ ቢይዙ በበጋ ወቅት ላለው እንቅስቃሴያቸው አይቸገሩም። ለከብቶቻቸውም ሆነ ለመጠጥ ውሃ ያገለግላል።

በሌሎቹ አካባቢዎች በልግ የዝናብ ወቅታቸው ላልሆነና በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አካባቢዎች ደግሞ አሁን የመኸር አሰባሰቡ ስላለቀ ዝናቡ የሚያበላሸው ሁኔታ ስለሌለ ምርትና ምርታማነት ስለሚጨምር በበጋ የሚመረተው ስንዴ ላይ የውሃ እጥረት ሳያስከትል ጥሩ ምርት እንዲኖር ያስችላል።

ሌላው ከውሃ አስተዳደር አንጻር የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዳይኖር ያደርጋል። በዚህ ምክንያት ምናልባት የመስመሮች መቀያየር በከተሞች አካባቢ ካልሆነ በስተቀር በውሃ እጥረት የሚመጣ የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ እንዲሆን የሚያስደርግ ነገር አይኖርም።

ከጉዳት አንጻር ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ ስለሆነ የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎችን እንዲሁም በልግ በማይጠቀሙ አካባቢዎችም የጎርፍ ክስተት ሊያጋጥም ይችላል። ይህን ጉዳት ለመቀነስ ከአሰፋፈር አንጻር ለምሳሌ ወንዞች ዳርቻ መስፈር የመሳሰሉት ላይ ጥንቃቄ ሁልጊዜ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁለተኛው ደግሞ በከተሞች አካባቢ የውሃ ማስወገጃ ቦዮች ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ስለዚህ በችግሩና በመልካም አጋጣሚ መካከል ያለውን ሁኔታ ሚዛን አስጠብቆ መሄድ ጠቃሚ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ፈጠነ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You