ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ፋይዳዎቹ

ኢትዮጵያ በቀደመው ታሪኳ የላቁ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራቷ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በአንድነት ኖራለች:: ከነዚሁ የጎረቤት ሀገራት አልፎ አልፎ የሚገጥሟትን ጦርነቶችና ግጭቶችንም ቢሆን በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስቀረት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች:: ወትሮም ግጭትና ጦርነት በማይጠፋው በዚህ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ኢትዮጵያ ብዙዎቹ የጎረቤት ሀገራት ከእርስ በርስ ግጭት ወጥተው በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን የአሸማጋይነት ሚና ስትጫወት ቆይታለች::

ይህ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዋ ከምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አልፎ በተቀረው ዓለም ላይም በርካታ ትሩፋት አስገኝቶላታል:: የኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንና ኋላ ላይ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልነትም የዚሁ ጠንካራ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውጤት እንደሆነ ይታመናል:: አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራትን የዲፕሎማሲ ልምድ ተጠቅማ በጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፋ ሌሎች የጎረቤት ሀገራትን እየጠቀመች ነው:: ለመሆኑ ይህን ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ እንዴት ማጠናከርና ማስቀጠል ይቻላል ስንል ለዲፕሎማሲው መስክ ቅርበት ያላቸው ምሁራን እንደሚከተለው ያብራሩታል::

የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) እንደሚሉት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይና የሽግግር ግዜ ፖሊሲ ሰነድ በመጀመሪያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያስቀምጣል:: ከዚህ አኳያ በጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ:: ይህ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ግን ከዚህ ቀደምም የነበረና አሁንም የቀጠለ ነው::

ስለዚህ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ጋር የሚኖራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ አለው:: አንደኛውና ቀዳሚ በኢትዮጵያ ድምበር አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያና የሌሎችም ጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች አብረው የሚሰሩበትና መገበያየት የሚችሉበት እድልና ሁኔታ እየተጠናከረ ይሄዳል:: ለምሳሌ ቦረናና ቱርካና ሃይቅ አካባቢ ያሉ ሕዝቦች በሽልንግም በብርም ይገበያያሉ::

በሌላ በኩል በድምበር አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጎረቤት ካሉት ሕዝቦች ጋር ተመሳሳይ የሕይወት መስተጋብር ያላቸው ናቸው:: ለአብነትም በጋምቤላ የኑዌር ጎሳ ተወላጆች በደቡብ ሱዳን ካሉ የኑዌር ተዋላጆች ጋር በቋንቋ፣ በባሕል፣ በአኗኗር ዘይቤያቸውና በእምነት የተሳሰሩ ናቸው:: ከዚህ አኳያ ይህ የአንድነትና ትስስር የኢትዮጵያን ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ከማጠናከር ባለፈ ለሰላምም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል::

ሁለተኛ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን ሠርታ የንግድ ትስስር ፈጥራለች:: ከነዚህ ሀገራት ጋር በመንገድ መሰረተ ልማት መልካም ግንኙነት መኖሩ የንግድ እንቅስቃሴውን ይበልጥ ሊያፋጥነውና ኢትዮጵያውያን ወደነዚህ ጎረቤት ሀገራት ሄደው ሊሠሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል::

የሶማሊያ መንግሥትን ያቆመችውና ከጥቃት ስትከላከል የቆየችው ኢትዮጵያ እንደሆነች ይታወቃል:: ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ በኩል ሰፊ ጎረቤት ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራ መሠራቱን ያመለክታል:: በተመሳሳይ የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በተለይ የሲቪል መንግሥት እንዲቋቋም ኢትዮጵያ ብዙ ጥረት አድርጋለች:: አምባሳደሮች በሱዳን መድባ ሲረዱ ቆይተው ሰላም መጥቶ እንደነበርም ይታወሳል::

ደቡብ ሱዳን ከነፃነቷ ጀምሮ ከሱዳን መንግሥት ጋር የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው:: ኤርትራም ብትሆን ከኢትዮጵያ ጋር በተለይ በአዋሳኝ ድምበሮች አካባቢ የንግድ ግንኙነት እንዳላት ነው የሚነገረው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ለቀጠናው ሀገራት ለኢኮኖሚም ሆነ ለሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለና በተቻለ መጠን በዚሁ መቀጠል ያለበት ነው::

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ባላት የኢኮኖሚ የበላይነት ወሳኝ ሚና እንድትጫወት ያስችላታል:: የጎረቤት ሀገራት ሕዝቦችን መርዳት የምትችል ናት:: በዚሁ ቀጠና ከፍተኛ ገበያ ያላት ሀገርም ናት:: የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ደግሞ ለቀጠናውም ሰላም መሆን አይነተኛ አስተዋኦ ይኖረዋል::

በተለይ የአፍሪካ ቀንድ በጦርነትና አለመረጋጋት የሚታወቅ ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ በቀጠናው የምታደርገው ጎቤት ተኮር ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ለቀጠናው ሰላም መረጋገጥና በኢኮኖሚ አብሮ የመልማት ፍላጎት እውን መሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል:: ይህ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ቀጠናውን ከማረጋጋት ባለፈ የነበረውን መጥፎ ገፅታም ይለውጣል:: የሕዝቦች ሁለንተናዊ እድገት ይጨምራል:: ለግጭትና ለጦርነት የሚወጣውም ገንዘብ ለሰላምና ለልማት የሚውልበት እድል ይፈጠራል:: ስለዚህ በተቻለ መጠን ይህን ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ እያጠናከሩ መሄድ ያስፈልጋል::

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚገልት ኢትዮጵያ በዲፕማሲው ሥራ ከፍታ ላይ ነበረች:: የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሀገር ልትሆን የቻለችውም በሠራችው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆነችውም በተመሳሳይ በነበራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ምክንያት ነው:: የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ሊሆን የቻለውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ከመሆኗ ባሻገር የዲፕሎማቶቿ ከፍተኛ ጥረትም ጭምር ነው:: የገለልተኛ ሀገራት አባል መሆን የቻለችውም በዚሁ የዲፕሎማሲ ጥረቷ ነው::

ስለዚህ እነዚህ ሁሉ አንድምታዎች ሲታዩ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለም ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምትሰጠው ትኩረት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያመለክታል:: ከዚህ ረጅም ግዜ ከቆየው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ልምድና አቅም አኳያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲዋን ለማጠናከር ብዙ ይቸግራታል ተብሎ አይታሰብም:: ይሁንና እያደገ ከመጣው ጥልቅና ውስብስብ የዲፕሎማሲ ሥራ አኳያ ዲፕሎማቶች በዚህ ደረጃ የላቁና የበቁ ብሎም ብሔራዊ ጥቅምን በሚገባ የሚያስከብሩ ለማድረግ ተገቢውን ሥራ መሥራት ይገባል:: ይህንን ሥራ በሚገባ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንን መለየትና በከፍተኛ ደረጃ የድርድርና የንግግር ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራትም ይጠይቃል::

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ወይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምትሰጠው ትኩረት መነሻ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦችና በጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለው ጠበቅ ያለ የባሕል፣ እምነት፣ ቋንቋ .. ወዘተ ትስስር ነው:: በጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች መካከል የረጅም ግዜ ትውውቅ በመኖሩ፤ ከቅርበትም አኳያ አንዱ ጋር ያለው ተግዳሮት ሌላው ጋርም ስለሚኖር ብሎም አንዱ ጋር ያለው አስቻይ ሁኔታ ሌላኛው ጋር ሊኖር ስለሚችልና ተፅእኖም ስለሚኖረው የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲም ከዚሁ ይመነጫል::

ከዚህ አንፃር የጎረቤት ሀገራት ሰላም የኢትዮጵያ ሰላም ነው:: የጎረቤት ሀገራት እድገት፣ ልማትና ብልፅግና የኢትዮጵያ እድገት፣ ልማትና ብልፅግና ነው:: የሰላም፣ የእድገት፣ የልማትና የብልፅግና ትሩፋቱም በቅርበት የሚታይ ነው:: ስዚህ የጎረቤት ሀገራት እንዲረጋጉ፣ በጎረቤት ሀገራት ሰላም፣ ልማትና እድገት እንዲኖር ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለራሷም ጭምር የሚጠቅም ነው::

ይህ የኢትዮጵያ የጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ጠቀሜታዊ ሲታይ ደግሞ እጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ ይታወቃል:: ምክንያቱም በሀገራቱ መካከል በተለያዩ መስኮች መተማመንና መቀራረብ ስለሚኖር ነው:: ለአብነትም በሀገራቱ መካከል በንግድ፣ ግብርና፣ ኢንደስትሪ፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት ዘርፎች መተሳሰር ይቻላል:: በቀጠናዊ ደህንት ጥበቃም እንደዚሁ ትስስር ይኖራል:: ምክንያቱም አንዱ ሀገር ተግዳሮት በሌላኛው ሀገር ላይ ተፅእኖ ስለሚያሳድር ነው:: እነዚህም በቅርበት የሚኖሩና የሚታዩ የጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ፋይዳዎች ናቸው::

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚያብራሩት የኢትዮያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ በንግድ፣ ግብርና፣ ኢንደስትሪ፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት ዘርፎች እንዲሁም በቀጠናዊ ደህንነት ማስጠበቅ ዙሪያ ትስስር እንዲኖር ከሚያስገኘው ጠቄሜታ ባለፈ በሌላው ዓለም ላይ ተፅእኖና ተሰሚነት እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል:: ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሁለንተናዊ መልኩ መተባበር፣ የኢጋድ አልፎም ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት መጠናከር ሀገራቱ በሌላው ዓለም ላይ ድምፃቸው ጎላ ብሎ እንዲሰማ በማድረጉ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው:: ትኩረት እንዲያገኙና ከሌላው ዓለም የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት፣ ከግንኙነቱ ማግኘት የሚፈልጉትን ትሩፋት ለመቋደስ ያስችላቸዋል::

ከዚህ አኳያ ይህ የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ በትልቁ የሚታይ እንጂ እንዲሁ ለይስሙላ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ለማስደሰት የሚደረግ አይደለም:: ከዚህ ይልቅ ተጨባጭ የሆኑ ጠቀሜታዎች ስላሉት ነው::

ምስራቅ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭት ከተንሰራፋባቸውና በተደጋጋሚ የሰላም መደፍረስ ከሚታይባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው:: በሰላም መደፍረስ ምክንያት የእርስ በርስ ግጭት፣ የውስጥ ግጭት መፈናቀል፣ በድርቅ ጎርፍና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች የሚጠቃ አካባቢ ከመሆኑ አኳያ ለዚህ ችግር ትኩረትና ቅድሚያ መስጠት የሁሉ ነገር መሰረት መሆን አለበት:: ለዚህ ቀጠና ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር ለማምጣት፣ ልማትና እድገት ደግሞ ሰላም ትልቅ ጉዳይ ነው::

ስለዚህ ምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና እንደመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የሚኖሩ ተግዳሮች ሁሉ የሚመለከቷት ስለሆኑ እንደ ግል ጉዳዩዋና እንደ ብሄራዊ ጥቅሟ አድርጋ ማየት ይኖርባታል:: ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲም ይህንኑ መሰረት ያደረገና በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድም ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል::

አምባሳደር ዲና እንደሚገልፁት ይህን የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ በቀጣይ በሚገባ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል:: የጎረቤት ሀገራትን ችግር ለመፍታት የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህም የጎረቤት ሀገራቱን ሉአላዊነታቸውንና ነፃነታቸውን ባከበረ መልኩ መሆን አለበት:: በቀጠናው ግጭቶች ሲከሰቱ ለማስታረቅ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጎረቤት ሀገራት እንደምታደርገው ሁሉ የተጋጩ ወገኖችን በማቀራረብና አንድ ላይ በማምጣት፣ በማገናኘትና አሸማጋይ በመሆን ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲያዋን ማጠናከር ይኖርባታል::

እንደውም የኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር ከተፈለገ ተቋማዊ መልክ ሊይዝ ይገባል:: ዲፕሎማሲው ዝምብሎ አልፎ አልፎ የሚሠራበት ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ሆኖ ከዓመት ዓመት በቋሚነትና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት:: በቀጠናው ችግሮች እስካሉ ድረስ የዲፕሎማሲ ሥራውን ለማሳለጥ የሚያስችል፣ የሚከታተል፣ በጥናት የተደገፈ እንዲሆንና ከግብታዊነት ነፃ በሆነ መልኩ ለመንቀሳቀስ የግድ ተቋማዊ የሆነ አደረጃጀትና የሰው ሃይል ጭምር ያስፈልጋል:: ይህን በማድረግ የጎረቤት ሀገር ተኮር ዲፕሎማሲን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መንቀሳቀስ ግድ ይላል::

ያለውን የዲፕሎማሲ አቅም ይበልጥ ለማዳበር በሰው ሃብት ረገድ ያለውን ክፍተት በሚገባ መሙላት ያስፈልጋል:: በተለይ የዲፕሎማሲ ሥራውን በግምባር ቀደምትነት የሚመሩ፣ እቅድ የሚያወጡና የሚገመግሙ ተቋማት በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል:: ብቁ ዲፕሎማቶችን ማፍራትና ተቋማትን ማቋቋም ይጠይቃል:: እነዚህ ዲፕሎማቶች በሚሠሩት ሥራ ከራሳቸው አልፎ ሌሎችንም እሴቶች መጠቀም ስላለባቸው፤ ለምሳሌ የሕዝብ ግንኙነቶችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የምርምር ተቋማትን፣ የሚዲያ ተቋማትን መጠቀምና ማንቀሳቀስ ይችላሉ::

እነዚህ ተቋማት ደግሞ ለሀገራቱ ግንኙነትና ለሰላም መስፈን ሚናቸው የጎላ ነው:: አልፎ አልፎም የተሳካ ሥራ ይሠራሉ ተብሎ ይታመናል:: ከዚህ አኳያ የተቋም አደረጃጀት፣ ጠንካራ የሰው ሀብት ማሟላት በፍፁም ግዜ የማይሰጠውና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው::

በሌላ በኩል ለውጡን ተከትሎ ጥሩ መልክ ይዞ የነበረውን፤ ነገር ግን አሁን ላይ የሻከረውን የኢትዮጵያና ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ትልቅ ጥረት ይፈልጋል:: ለዚህም በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው መጠነኛ ያለመግባባት ሁኔታ የተፈታበትን መንገድ እንደተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል:: አሁንም ይህ መጠነኛ ያለመግባባት መንፈስ በተፈታበት አግባብ ሌሎች ወዳጅ ጎረቤት ሀገራትን በማሳተፍ፣ በግልፅ በመነጋገር፣ ዓላማን በመግለፅ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ሰላማዊ በሆነ መንፈስ የመፍታቱ ነገር ኤርትራን ጨምሮ ከሌሎች ገረቤት ሀገራት ጋር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You