“እኔ ካልሠራሁት ልክ አይደለም”

እውቅና (Recognition) እና አድናቆት (Ap­preciation) እንዲሁም ሂስ (Criticism) በልክ ሲሆኑ የሰው ልጅ ራሱን ወደ ውስጥ እንዲመለከት ያስችሉታል። ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሳ መስፈንጠሪያ ይሆኑታል። በአንጻሩ ያልተገባ እውቅና እና አድናቆት እንዲሁም ሰዎች መሥራት የሚገባቸውን ያህል እንዳይሰሩ በማድረግ ሞራልን ያኮሰምናሉ፤ ያቀጭጫሉ።

ሊቃውንት “ተፈጥሮ ወናነትን ትጠየፋለች” ይላሉ፤ ብዙ ጊዜ ወናዎች በአግባቡ ሥራቸውን የሚሰሩ እና የማይሰሩ ሰዎችን ለይተው ተገቢውን እውቅና (Recognition ) እና አድናቆት (Appreciation) እንዲሁም ሂስ (Criticism) ከመስጠት ይልቅ በጭፍን መቃወም ወይም መመቅኘት ይቀናቸዋል። የቱንም ያህል ልክ እና ትክክል የሆነ ሥራ ቢሰራም ራሳቸው በቦታው ቢሆኑ እንደማይሰሩት ፤ ከሰሩትም የተለየ ነገር እንደማያደርጉ እያወቁ እኔ ስላላደረኩት ልክ አይደለም ይላሉ።

አሁን አሁን ምክንያት አልባ ሂስ፤ አንድናቆት፤ ጥላቻ እና ተቃውሞ እንዲሁም ምቀኝነት በሀገራችን እየተለመደ የመጣ ይመስለኛል። ምንም ያልሰራን፤ ለሀገር ፖለቲካል ኢኮኖሚ እድገት፤ ጋሬጣን የሆነን ግለሰብ ወይም ቡድን በግብዙ ማድነቅ እና ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ሌት ከቀን የሚሰራን ደግሞ በምቀኝንት ማጥላላት፣ መተቸት፣ ማቋሸሽ እና ማራከስ በስፋት እየተስተዋለ ነው። ይህ ትክክል ያልሆነ እና በጊዜ ሊታረም የሚገባው ነው።

በርግጥ አሸናፊዎች ሁሌም አላማቸውን የሚያዩ ናቸው፤ ተሸነፊዎች ደግሞ ወና (ሃሳብ አልባ) በመሆናቸው አላማቸውን ከመመልከት ይልቅ መሰናክሎችን ያያሉ። መሰናክሎቻቸውም በመደርደር ተራማጆችን አላራምድ ማለታቸው የማይቀር ነው። ይህ በእለት ተእለት ሕይወታችን ሳይቀር የምንታዘበው እውነታ ነው።

እንደኔ እንደኔ በአጭር ዘመን የሕይወት ቆይታችን ልናደርግ ከሚገቡን ነገሮች መካከል ዋነኛው ሰዎች ያደረጓቸውን እና የሚያደርጓቸውን መልካም ነገሮችን ሁሉ የማድነቅን ልምድ ማዳበር ነው። ይህም ከአውንታዊ አስተሳስብ የሚመነጭ ነው። አውንታው አስተሳብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ጤነኛ አእምሮ ያላቸው ናቸው። ጤነኛ አእምሮ ያለው ደግሞ ኃላፊነትን መሸከም የሚችል እና በሀገረ መንግሥት ግንባታ አውንታዊ ሚና ሊያበረክቱ የሚችሉ ናቸው። ለዚህም ነው ባለቅኔዎች

ሰናይ ለብእሲ ያወጽኣ ለሰናይት፤

“እም ሰናይት መዝገበ ልቡ። (በጎ ያለው ከበጎ ልቡ በጎ ነገርን ያወጣል)” ሲሉ ቅኔን መቃኘታቸው።

የማድነቅ ተቃራኒ ማንቋሸሽ ነው፤ ይህም በአብዛኛው ከከፋ ቅናት የሚመነጭ ነው። ቅናት ደግሞ የሚመነጨው ራስን ከሌላው የበለጠ ለማድረግ ካለ ወና ጉጉት ነው። ቅናተኞች የአእምሮ ጤናቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር ሰዎችን ጠልፈው ለመጣል አለፍ ሲልም ለመግደል ይነሳሳሉ። በሀገራችንም ፖለቲካል ኢኮኖሚ በስፋት የሚስተዋለውም ይህ ችግር ይመስለኛል።

በሀገራችን የሚገኙ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ተመሳሳይ ርእዮተ አለም እና ሃሳብ ያላቸው ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም። ግን አንድ መሆን ወይም በጋራ መስራት ያቅታቸዋል። ምክንያቱም እነሱ የሚፈልጉት ነገር በሌላኛው ወገን ከተደረገ ነገሩ ልክ እንዳልሆነ ለማሳየት በሚያደርጉት ያልተገባ ፍተጊያ ነው። የሚያስቡትን ሃሳብ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው ከመከወን ይልቅ ትከሻ ለትከሻ በመገፋፋት መላላጥን ይመርጣሉ።

እነዚህን እና መሰል አካሄዶች ስመለከት ሰዎች የሚቃወሙት ሰውየውን ነው ወይስ ሃሳቡን? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ያደርገኛል። ጥናት ባላካሂድም ብዙ ሰው ግን የሰውየውን ሃሳብ ሳይሆን እራሱ ሰውየውን የሚቃወም ይመስለኛል። ይሄንንስ ለምን ሰዎች ያደርጋሉ? ብዬ ራሴንም ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ አንድም ድፍን ጥላቻ ነው፤ሌላው ደግሞ “ሊደረግ ከታሰበው መልካም ነገር በኋላ፤ የሚመጣው ውዳሴ እና ቅዳሴ ሁሉ ለኔ ነው የሚገባኝ!” ከሚል የቀጨጨ እና የቀነጨረ አስተሳሰብ ነው።

እኔ ይህንን ስል ግን ልክ ያልሆነን ነገር ሁሉ ልንስማማበት ይገባል ከሚል የሞኝ ሃሳብ የመነጨ እንዳልሆነ እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። እንደውም እኔ በግሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ አቋም ሰው እውነተኛ ነው የሚባለው እውነትን ብቻ ስለተናገረ ሳይሆን ሀሰትንም ሀሰት ነው ብሎ ለመቃወም ድፍረቱ ሲገኝ ነው። ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለሚሰሯቸው በጎ ተግባራት እውቅና የማንሰጥ ፣የማንደገፍ እና የማናደንቅ ከሆነ ተጠላልፈን ከመውደቅ እና ባለንበት ከመርገጥ ውጭ ምንም ለውጥ ማማጣት አንችልም።

በርግጥ የአብዛኛዎቻችን አስተዳደግ ስንሳሳት በቁጣ፤ ባስ ሲልም በዱላና በስድብ ውርጅብኝ ታጅበን ነው። ላደረግነው መልካም እና በጎ ሥራ “ጎሽ ! ጥሩ አድርገሃል” ብሎ እውቅና የሚሰጥ የአስተዳደግ ሥርዓት ውስጥ አላለፍንም። በዚህ ተጽእኖ የሚፈጠር ባህሪ አብሮን አድጎ! ትምህርት ቤት ተከትሎን ይሄዳል፤ሥራ ቦታ ተከትሎን ይሄዳል፤ የህይወት ዘመን ጥላ ሆኖ ይከተለናል።

“ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም“ ነውና፤ ይሄ ሽፋኑን “አላመንኩበትም ወይም ነገሩ ልክ አይመስለኝም” የሚል ሃሳብ ውስጡ ክፋት እና ጥላቻን ይዞ ሰዎችን ማድነቅ እንዲያቅተን ያደርጋል። በመጨረሻም ቀደም ሲል እንደገለጽኩት፣ እኛም ሳናውቀው ምቀኞች እና ጨለምተኞች ሆነን እናርፈዋለን።

ወናዎች (ሃሳብ አልባ ምቀኞች) ምክንያት አያጡም። ጓደኞቻቸው ትምህርታቸውን ‘በጥሩ ውጤት አለፉ’ ሲባሉ፤ አስተማሪው ውጤት ጨምሮላቸው ነው ወይም ኮርጀው ነው ይላሉ። “እከሌና እከሊት ቤት ሰሩ።” ሲባል “ጉቦ በልተው ነው።” እከሌ ሹመት አገኘ የእንትን ብሔር አባል ስለሆነ ነው። ይላሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ሁሉንም ለማለት ሰዎችን በትክክለኛው ሚዛን መመዘን ያስፈልጋልና።

መንግሥት ለነዋሪዎች ቤት ሲሰራ፤ የተሰራውን ቤት የሰጠው ለራሱ ብሔር ብቻ ነው። የተሽከርካሪዎች መንገድ ጠባብ በመሆኑ እግረኛው እና ተሽከርካሪው እየተጨናነቀ ነው፤ መንግሥት አስፓልት ሊሠራ እና ሊያስፋፋ ይገባል! እንልና መንግሥት እሺ ልስራ ሲል አሁን በዚህ ኑሮ ውድነት አስፓልት ምን ያደርጋል! አስፋልት ምግብ ሆኖ አይበላ? የሚል ትችት እንሰነዝራለን።

ይህ አይነቱ አመለካከት በተለይ ከፖለቲከኞች እና ከምሁራንም ሲነሳ ሳቅ ያጭራል። እኔ በግሌ ይህንን ስል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች የሉም ለማለት ፈልጌ አይደለም። ነገር ግን ለተሰራው በጎ ሥራ አመስግኖ ያልተደረገን እንዲደረግ መጠየቅ እንጂ ሁሉንም መተቸት እና መውቀስ ብቻ አላስፈላጊ እና ለሚደረገው የሀገረ መንግሥት ግንባታ አሉታዊ ጥላ ያጠላል።

ክፉ ሰዎች ነፍሳቸውን በስጋቸው የሚጨቁኑ ናቸው። “የማይገለጥ ሽሽግ የማይታይ ስውር የለም” እንዲሉ ጠቢባን፤ ጊዜው ይረዝም እንደሆነ እንጂ እነዚህ ነፍሳቸውን በስጋቸው የሚጨቁኑ ሰዎች እንከፍ ስራቸው ለሕዝብ እየተገለጠ መምጣቱ የማይቀር ነው። ስለሆነም እኔ ካላደረኩት ልክ አይደለም ከሚል ሃሳብ ወተን እኔ በቦታው ብሆን ከዚህ የተለየ ምን አደርግ ነበር ከሚል ሃሳብ ተነስተን፤ ሁላችንም የስኬት እና የመልካም ነገሮች አድናቂ፤ ጥያቄ ሲኖር በአግባቡ ጠያቂ በመሆን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላችንን እንወጣ!።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም

Recommended For You