ስለ ሕዝባችን ሰላም ቀድመን ከራሳችን ሰላም ጋር እርቅ እናድርግ!

ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው ሲባል ከጦርነት ጭንቀት ማሳረፉ ወይም ሞትና ውድመት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ጦርነትን ተከትለው የሚመጡ ብዙ ተያያዥ ችግሮች ስላሉት ጭምር ነው።በጦርነት ውስጥ ሆኖ ያደገ ሀገር የትም አይገኝም። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ለአንዳንድ ሀገራት ሠርግና ምላሽ እንደሆነላቸው ከዳር ሆነው እሳቱ እንዳይጠፋ ለሚያራግብ እንጂ ለሁለቱም በዘመናት ለማይወጡበት አዘቅት እየከተታቸው ነው።በእስራኤል ሀማስ ጦርነት እየወደመች ያለችው ጋዛ ትሁን እንጂ እስራኤል በፖለቲካዋ፣ በኢኮኖሚዋ፣ በዲፕሎማሲዋ፣ በሕዝቧ ሥነ ልቡናም ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡

የጦርነት አስከፊነት በጦርነት ወቅት የሚከሰተው ሞት፣ ውድመት፣ መፈናቀል፣ ስደትና ሌሎች ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ በኋላ መልሶ የነበረን ሥነ ልቡናን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው።ያለዚህ ሥነ ልቡና ደግሞ ሰው ተስፋ ወደ መቁረጥ ይገባል።በሀገሩ ተስፋ የቆረጠ ደግሞ ወይ ይሰደዳል፣ ባስ ሲልም ወደ አጥፊነት ይቀየራል።

ይህ በብዙ ሀገራት ውስጥ የተከሰተ ነው።ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ኢራቃዊያንና አፍጋኒስታናዊያን ምንም በሌለበት የሚበረግጉ፣ ያልተረጋጉ ማህበራዊ ቀውስ ያጋጠማቸው ሆነዋል።ኢራቅ በጦርነቱ በቀጥታ ከደረሰባት ውድመት ይልቅ ከጦርነቱ በኋላ ራሷን ለማረጋጋት ያወጣችው ወጪ በብዙ እጥፍ ይልቃል።

ሊባኖስም እንዲሁ ከእርስ በርስ ውጊያ ከተላቀቀች አስር ዓመታት ብታስቆጥርም አሁንም ግን በሕዝቡ ውስጥ ልዩነቱ፣ ፍርሃቱ፣ ጥርጣሬው ወይም ትራወማው አለቀቀም።ትራሱ ስር መሳሪያ የሚያስቀምጥ ሊባኖሳዊ አሁንም ብዙ ነው።የሰላምን ዋጋ ሰላምን ያጡት ያውቁታል።

ከጦርነት ታሪካችን ከአስከፊው ኪሳራችን መማር ባለመቻል በሕዝብ ደህንነት በኩልም ሆነ በሀገር እድገት ከሌሎች በታች አድርጎናል።አሁንም ድረስ ግጭት እና አለመግባባት የሰላም እጦት ሀገርና ሕዝብን በብዙ እየጎዳ ነው።ግጭትና አለመግባባት ሲኖር የሰው ሕይወት ይጠፋል ሀብትም ባልተገባ ቦታ ይውላል።

ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ያለን የጦርነት ታሪክ ነው።ሌሎች ሀገራት ከጦርነት ታሪካቸው በዘለለ ስለሕዳሴአቸው /ሬኔሳንስ/፣ ስለትራንስፎርሜሽናቸው፣ ስለኢንድስትሪ አብዮታቸው ሊያስተምሩ ይችላሉ።

እኛ ያለን ታሪክ የጦርነት ታሪክ ብቻ ነው ማለት ይቻላል።ከሱም ቢሆን በአግባቡ መማር አልቻልንም።ከጦርነት ወደ ጦርነት አሁንም እንደጋግመዋለን።ይህ መሆኑ ከፍተኛ ውድቀት አስከትሎብናል።አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ዝቅጠት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡

ችግርን በሰላማዊ አካሄድ ለመፍታት ዝግጁነት መጉደሉ ለቀውስና ኪሳራ ዳርጓል።ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የአንደኛውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጦርነትን አስከፊነት ተረድተው ሰላምን አምጥተው ሀገራት ራሳቸውን አሳድገዋል።ለዚህም ለሰላም የነበራቸው ቁርጠኝነት ወሳኝ ነበር።ትናንሽ የሚባሉ የአውሮፓ ሀገራት ሳይቀሩ ለሰላም በነበራቸው ቁርጠኝነት ከግጭት ወጥተው ትልልቅ የሚባሉ የአፍሪካ ሀገራትን እየረዱ ይገኛሉ፡፡

ጦርነት አዲሳችን ባይሆንም ሞት እንደማይለመድ እንግዳ እንደሆነ ሁሉ በየሰዓቱ እንኳን ቢከሰት በየሰዓቱ የሚያስደነግጠን፣ የሚያስለቅሰን ነው። ጦርነትም በፍፁም የማይለመድ የሁሉ ጠላት ነው።ጦርነት ጠላትነቱ ለሰላም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚን እሳት እንደገባ ቅቤ የሚያቀልጥ፣ ፍቅርን እንደሳይቤሪያ በረዶ የሚያቀዘቅዝ ፣ መተማመንን እንደ ጎርፍ የሚሸረሽር የሁሉ ነገር ፀር ነው።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር እንደተናገሩት፤ “የሕዝቡ ጥያቄ ግልፅ ነው።ሕዝቡ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ይፈልጋል፤ ሁሉ ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ፣ ልማት እንዲለማ፤ ድህነት እንዲቀንስ፤ ኢትዮጵያ ከችግር እንድትገላገል ይፈልጋል፤ ዴሞክራሲና ተቋማት እንዲገነቡ ይፈልጋል።ለምን ቢባል ሕዝብ ማለት የቀጣይነት ምልክት በመሆኑ ነው።ልጆች ያሉት ለልጆቹ የተሻለ ሀገር ይፈልጋል፡፡”

ርግጥ ነው ሕዝቡ ሰላምን አብዝቶ ይፈልጋል።ለመኖሩ የሰላም መኖር ቀዳሚ ጥያቄው ነው።የሰላም መኖር ለሕዝብ መኖር፣ መበልጸግ ብሎም መከበር ዋስትና ነው።ሰላም ዘርቶ ለመቃም፣ ወልዶ ለመሳም፣ ወጥቶ ለመግባት ሆነ ሰርቶ ለመለወጥ አስፈላጊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።ለዚህም ነው ስለ ሰላም ዋጋ ከፍተኛነት ሁሌም የሚነገረው።

ጦርነት የሕይወት ዋጋን ያለስሰት ያስከፍላል።ሀገርን የኋሊት ያስጉዛል።ልክ እንደእኛ የጦርነት ጠባሳው ያልሻረለት ሕዝብ ደግሞ እውነታው የተደበቀ አይደለም።መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ትላንት ፕሪቶሪያም ሆነ ዳሬሰላም ላይ በመገኘት አሳይቷል።በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ግጭቶችን በሰላም እንዲፈቱም አበክሮ እየሰራ ነው።

ደስታን ማጣጣም፤ ሀዘንንም መካፈል የሚቻለው ሀገር ሰላም ሕዝብም ጤና ሲሆን ነው።የሰላምን አየር መማግ ለናፈቀ፣ የግጭትን ማክተም ለሻተ፣ ስቃይና እንግልት በቃኝ ላለ ሕዝብ ይህ ግልፅ ነው።የትላንት ስህተታችን እንዳይደገም በእጃችን ያለው አንፃራዊ ሰላም እንዳይጠፋ ከሕዝብ እስከ መንግሥት ባለድርሻዎች ድረስ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።

ኢትዮጵያ የሰነበቱ የፖለቲካ ጥፋቶቿ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትሰነብት አድርገዋታል።ከዚህ አዙሪት ለመውጣት በመንግሥት የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መቀጠል እንዳለባቸው ሁሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሕዝብ ደህንነት ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ የሕግ ማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የተለያዩ ሃሳቦች ያሏቸው አካላት፣ የሕዝብ ጥያቄ ነው የሚሉት ጉዳይ ካለም አሁን ያለውን ትልቁን እድል ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን በመቆም ሥርዓት በጠበቀ መልኩ ችግሮቻቸውን በፍርድ ለመፍታት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት ሁሌም በሩ ክፍት ነው ማለታቸው ይታወሳል።ታጥቀው በየጫካው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እፈልጋለሁ የሚልና ኃላፊነት የሚሰማው የትኛውም አካል የልዩነት ሃሳቡን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ በመፍቀድ ሀገርን የማስቀጠል ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል።

የነገ ብሩህ ግቧን አልማ እየተንቀሳቀሰች ባለችው ሀገራችን የሰላም መደፍረሶች ይስተዋላሉ።መንግሥት በቀዳሚነት ሰላማዊ አማራጮችን ቀዳሚ አማራጭ አድርጎ ቢውስድም፤ የሀገርን ህልውና ከማስቀጠል አኳያ በመንግሥት በኩል የሚወሰዱ የሕግ ማስከበር ርምጃዎች ሀገርን የመታደግ ሕጋዊ አካሄድ ናቸው።

በየትኛውም ጉዳይ ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ጥያቄዎች ማንሳት ይችላል።ጥያቄዎች የሀገርን ሰላምና ደህንነት፤ የሕዝቦችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የማይፈታተን ሊሆን ይገባል። ዓለም አሁን ያለበት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ጥያቄ ተመልሶለት አይደለም፤ ጥያቄዎች የሚጠየቁበትና የሚመለሱባቸው መንገዶች ዘመኑን የሚዋጅ በመሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ ትክክል ሊሆንም ላይሆንም ይችላል።ይህንን የሚወስነው ሕዝብ ነው።ጥያቄዎች የምንጠይቅበት መንገድ ከመገዳደል በሃሳብ ወደ መገዳደርና በሰላማዊ የውይይት መድረክ መሆን አለበት።እንደ ሀገር ከሰላም ጋር ተያይዞ ችግር ቢኖርም ለችግራችን በአንድነት እልባት መስጠት ያስፈልጋል።ለሰላም መነጋገር መደማመጥ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ማውራት ወሳኝ ነው።ከዚህ ውጭ ስለ ዘላቂ ሰላም ማውራት አይቻልም።

ጥያቄዎች አልተመለሱም በሚል አላግባብ በሆኑ ስሜት ተኮር አካሄዶችና ተገቢ ያልሆኑ የትጥቅ ትግል መንገዶችን መከተል ከውጭ ለሚመጣ ጠላት ተጋላጭ ስለሚያደርገን ጥንቃቄ ያሻዋል።የውስጡ ልዩነት በጎረቤትና በሌላው ዓለም ለሚገኙ የሀገራችን ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ ይከፍታል።እንደመልካም አጋጠሚም ይጠቀሙበታል።

ባለመግባባት በምንሄድበት የጦርነት መንገድ፤ የሚሞተው ሰው ነው፤ የሚወድመው ንብረት ነው።ጦርነት የምንጨምረው ምንም ነገር የለም። ተጨማሪ ጣጣ ይዞብን ይመጣል።ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አስፈላጊ እንደሆነች ሁሉ ጦርነት በብዙ መልኩ ብሔራዊ ጥቅማችንን ይጎዳል።

ኢትዮጵያን ደካማ እና እንዳትረጋጋ በማድረግ በቋሚነት ግጭት ውስጥ እንድትኖር ማድረግ አለብን ብለው፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፀው የተቀመጡ፣ በገንዘብ፣ በመሳሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት የሚደግፉ ወይም ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት አሉ።በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እንዲኖር መሥራት የሀገራችንን ታሪካዊ ጠላቶች መሰሪ አካሄድ መደገፍ ነው።ሌሎች ጣልቃ ገብነቶችንም ያስፋፋል፡፡

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ሰላምን የሚሻውን ሕዝብ ማድመጥ ነው።መንግሥትም መሰል ሰላማዊ አካሄዶችን እንደሚከተል በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል።ከየትኛውም አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ ይገልፃል።

በግጭት በጦርነት የሕዝብና የሀገር ፍላጎት አይሳካም።ምክክርና ውይይት ሰላምን ለማስፈን ሁነኛ አማራጮች ናቸው።ከመገዳደል ተቀምጦ መወያየት ይመረጣል።የጦር መሳሪያ አስቀምጦ እስክሪቢቶና ሃሳብ ይዞ በመወያየት ለሰላም፣ ለብልፅግና ምቹ የሆነች ሀገር እንድትሆን መሥራት ያስፈልጋል።

ምንም ነገር ያለ ሰላም ማሰብ ከባድ ነው።የሕዝብ ኑሮ መሻሻልም ሆነ የሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት የሰላም መኖርና አለመኖር ጋር የተቆራኘ ነው።ሰላም እንዳይደፈርስ ግጭትም እንዳይኖር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ይጠይቃል።ችግሮች ከተፈጠሩም በኋላ የከፋ ጉዳትና ቀውሶች ሳይኖሩ በውይይት፣ በቁርጠኝነት መፍታት የመንግሥትና የሌሎችንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል።

ከግጭትና ጦርነት በፊት ስለሰላም ለውይይትና ምክክር እራስን ማስገዛት ካልተፈለገ ኪሳራ መውጫው ብቸኛ መንገድ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ከአለፈ ታሪክ መማር አለብን።ለሚያጋጥሙ አለመግባባቶች በውይይት ፈጣን መፍትሔ መስጠት የሚያተርፈው ሁሉም ነው።የጋራ መግባባት የጋራ ተጠቃሚነትን ያመጣል።

ጦርነት መልከ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለን ለማንኛችንም የተሰወረ ትርክት አይደለም፤ ከከፈልናቸው አላስፈላጊ ዋጋዎች ተምረን ስለሰላም ደቀመዝሙር ልንሆን ይገባል።በጦርነት ዘላቂ ድል ማግኘት አይቻልም ፤ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ለሰላም ለተዘረጉ እጆች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል።የትኛውም የሕዝባችን ጥያቄ ከሰላሙ አይበልጥም እና ስለ ሕዝባችን ሰላም ቀድመን ከራሳችን ሰላም ጋር እርቅ እናድርግ።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You