በረመዳን የጾም ወር ማብቂያ ላይ ተጨማሪ ስድስት የጾም ቀናት ያሉ ሲሆን፣ የእነዚህን ቀናት መጠናቀቅ ተከትሎ የሸዋል ኢድ ይከበራል። የሸዋል ኢድ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካለል ሐረርን የሚስተካከላት የለም። የሸዋል ኢድ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሐረር መከበር እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የሸዋል ኢድ በሐረሪዎች ዘንድ የሸዋል ጾም ከተጠናቀቀ በኋላ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። በዚህ በዓል በየትኛው ቦታ ያለ ሰው ወደ ሐረር መጥቶ ከቤተሰቡ ጋር የሚዘያየርበት እና ያላገቡ የሚተጫጩበት በዓል ነው። በዚህ በዓል የሚታደሙት በሐረር የሚኖሩ ሐረሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የብሔረሰቡ ተወላጅ ያልሆኑ እና በክልሉ የሚኖሩ፣ በመላው ኢትዮጵያ እና ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ሐረሪዎች ይህንን በዓል ለመታደም ይሰበሰባሉ። ይህም የበዓሉ አንዱ ድምቀት ለመሆን በቅቷል። አሁን አሁን ደግሞ ከሁሉም ኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ብሔር ብሔረሰቦች በሐረር በመገኘት የሸዋል ኢድን በጋራ እያከበሩት ይገኛሉ።
የሸዋል ኢድ ክብረ በዓል አከባበር የሚጀመረው ከዋናው በዓል ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው። በሐረሪ ሸዋል ኢድ የባህል አልባሳቶች የሚወጡበት፣ ያላገቡ ሐረሪዎች በጌጣጌጦቻቸው የሚዋቡበት ልዩ ቀን ነው። የሸዋል ኢድ በዓል ወጣቶች በይበልጥ የሚግባቡበትና የሚተጫጩበት እንደሆነ፣ ይልቁንም የሐረር ወጣቶች ባህልና አኗኗራቸውን የሚያንጸባርቁበት አጋጣሚም ነው።
ሐረር የጀጎል ግንብ እና አምስቱ በሮች፣ የወርቅ ሳንቲሞች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ መስጊዶች፣ የሥነ ሕንፃ፣ የታሪክን አሻራ የሚያንፀባርቁ የቤት ውስጥ ዕቃዎች ያሉባት የቱሪስት ማዕከል ነች። በዚህ እምቅ የቱሪስት ሀብቶቿ ላይ የሸዋል ኢድ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የዓለም ቅርስ አካል አድርጎ መመዝገቡ ለታሪኪቷ ከተማ ድርብ ግርማ ሞገስን አላብሷታል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስንሄድ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ነች። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ከታወቁ እና ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉም የኢትዮጵያ የብልጽግና መሠረትና የሕዝቦቿም የኑሮ መሠረቶች ይሆናሉ።
ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና እና ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። እንደ ሀገርም መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፤ኢንዱስትሪ፤ማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉ የመሪነት ሚና እንዲኖረው አድርጓል።
የቱሪዝም ቦታዎችን በማስፋትና በመንከባከብ እንዲሁም ለቅርሶች ተገቢው እንክብካቤ በመደረጉ ምክንያትም የሸዋል ኢድ አከባበር ሥርዓትን አከባበር ጨምሮ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦችን 16 በማድረስ በአፍሪካ ቀዳሚነቷን ማረጋገጥ ችላለች።
የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ኢትዮጵያ ብዝሃነት የሚንጸባረቅባት ሀገር መሆኗን ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ከማስቻሉም በላይ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ የሚያደርግ ነው። ይህ ታሪካዊ ውሳኔም ሐረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ በማወቅ፣ በመጠቀምና በመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል። በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም የተረዳ ዜጋ ለመገፋፋትና ለመጣላት የሚሆን ጊዜ ስለማይኖረው ያለንን እምቅ ሀብት ሥራ ላይ አውለን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ለነገ ልንለው የምንችለው ተግባር አይደለም።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ለቱሪዝም ዘርፉ እንቅፋት የሆነውን ጦርነትና ግጭት በማስወገድ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንድትጠቀም ማድረግ ያስፈልጋል። በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በማይዳሰስ ቅርስነት አምስተኛ ሆኖ የተመዘገበው የሸዋል ኢድ ከሃይማኖታዊ አከባበሩ ባሻገር የኢትዮጵያዊያን ብዝሃነት የሚታይበት ቅርስ በመሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ ይገባል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም