በክልሉ ከ5 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለመምህራን ተላልፈዋል

አዲስ አበባ፡– በተያዘው በጀት ዓመት እስከ የካቲት ወር 2016 ዓ.ም ድረስ በገጠር የክልሉ አካባቢዎች ለሚገኙ ከአምስት ሺህ 508 በላይ ቤቶች ተገንብተው ለመምህራን መተላለፋቸውን የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ በክልሉ ሦስት ሺህ 410 ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ የአራት ሺህ 627 ትምህርት ቤቶችን የማሻሻያ ሥራ በማጠናቀቅ ከእቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡

በትምህርት ቢሮው በምክትል ኃላፊ ደረጃ የዋና ኃላፊው አማካሪ ኤፍሬም ተሰማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል የመምህራንን ምቾት ለመጠበቅና የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡

በገጠራማ የክልሉ አካባቢዎች ለሚያገለግሉ መምህራን በየትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ ከአምስት ሺህ 500 በላይ ቤቶች መኖሪያ ተገንብቶላቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በገጠራማ የክልሉ ክፍሎች ያሉ መምህራን ሥራቸውን አከናውነው ሲጨርሱ የሚያርፉባቸውን አራት ሺህ የመምህራን መኖሪያ ለመገንባት መታቀዱን አስታውሰው፤ አምስት ሺህ 508ቱን ቤቶች አጠናቆ በማስተላለፍ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን አመላክተዋል።

የመምህራኑ መኖሪያዎች የትምህርት ቤቶቹ ንብረት በመሆናቸው የሥራ ዝውውር ቢፈጸም እንኳን በማንኛውም ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቶች የሚመደቡ መምህራን እንደሚጠቀሙባቸው አቶ ኤፍሬም አንስተዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ የሚገኙ መምህራን ደግሞ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው በክልሉ ፕሬዚዳንት አማካኝነት የወረደ መመሪያ መኖሩን ያነሱት አቶ ኤፍሬም፤ በተወሰኑ ከተሞች ላይ በማህበር እያደራጁ የቤት መሥሪያ ቦታዎች የመስጠቱ ሂደት መቀጠሉን ጠቅሰዋል፡፡

መምህራን በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲሠሩ ለማገዝ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ መምህራን በየትምህርት ክፍሎቻቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቃታቸውን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ስልጠናዎቹ መምህራኑ በየትኛውም ዘርፍ ላይ ክፍተት አለባቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚረዱ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በሚመለከት በክልሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተው፤ በበጀት ዓመቱ ሦስት ሺህ 410 ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ ከእቅድ በላይ አፈጻጸም በማስመዝገብ 4 ሺህ 627 ያህሉ ላይ የማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ 300 ሰዎችን አሳድሮ ማሰልጠን የሚያስችል ማዕከል መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ የሰው ኃይልና አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት በሪፎርም ሂደቱ በክልሉ የሚገኙ አንድ ሺህ 100 ሱፐርቫይዘሮችን በማሰጠልን ስምሪት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You