የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከሰጣቸው ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የሮተርዳም ማራቶን ከትናንት በስቲያ በኔዘርላንዳ ከተማ ተካሂዷል:: በሴቶች መካከል የተካሄደውን የ42 ኪሎ ሜትር ፉክክርም ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት አሸቴ በከሪ ቀዳሚ በመሆን አጠናቃለች::
ከውድድሩ የመጀመሪያ ኪሎ ሜትሮች አንስቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር ያደረገችው አትሌት አሸቴ፣ ሃያ አምስት ኪሎ ሜትሮችን 1፡21፡23 በሆነ ሰዓት ከተፎካካሪዎቿ ጋር ካገባደደች በኋላ በአስደናቂ ፍጥነት ጥላቸው ሄዳለች:: ሰላሳኛው ኪሎ ሜትር ላይም ከተፎካካሪዎቿ ጋር ያላትን ልዩነት በስምንት ሰከንድ ጨምራ በጊዜ አሸናፊ እንደምትሆን አሳይታለች::
በመጨረሻም የ35 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት በ2:19:30 ሰዓት በድንቅ አጨራረስ የ2024 የሮተርዳም ማራቶን አሸናፊ ለመሆን በቅታለች:: በ2018 ቫሌንሲያ እና በ2019 በርሊን ማራቶንን ያሸነፈችው አሸቴ በ2019 ይህንኑ የሮተርዳም ማራቶን 2:22:55 ሰዓት በማስመዝገብ ማሸነፍ እንደቻለች ይታወሳል:: ዘንድሮ በኔዘርላንዳ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰዓትም ከቀድሞው ከ3 ደቂቃ በላይ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል::
በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪነታቸውን ያሳዩት ኬንያውያኑ አትሌቶች ቪዮላ ኪቢዮት በ2:20:57 ሁለተኛ እና ሳሊ ቼፕዬጎን ካፕቲች በ2:22:46 ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በወንዶች መካከል የተካሄደውን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአሸናፊነት ጠንካራ ፉክክር ቢያደርጉም ቀዳሚውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ሳይችሉ ቀርተዋል::
ኔዘርላንዳዊው የኦሊምፒክ ማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊ አትሌት አብዲ ነገዬ በሀገሩ የተካሄደውን ውድድር በድንቅ ብቃት ለሁለተኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል:: ለድል የበቃበትን 2፡04፡50 ሰዓት ሲያስመዘግብም 2022 ላይ አሸናፊ ከነበረበት 2:04:56 ሰዓት በአስራ አንድ ሰከንድ የተሻለ ሆኗል:: ይህም በራሱ ተይዞ የነበረውን የኔዘርላንድስ ማራቶን ክብረወሰን ያሻሻለበት ነው::
ውድድሩን ቀዳሚ ሆኖ የማጠናቀቅ ትልቅ እድል የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ በ2:04:50 በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። እስከ መጨረሻዎቹ ጥቂት መቶ ሜትሮች ድረስ ውድድሩን ሲመራ የነበረው አምደወርቅ በትውልደ ሶማሌያዊው የኔዘርላንድ አትሌት አብዲ ነገዬ የተቀደመውም በአምስት ሰከንዶች ብቻ ነው:: ሌላኛው ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሀኑ ለገሰ ውድድሩን በ2:05:16 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል።
ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ባለፈው የካቲት ወር በደረሰ የመኪና አደጋ ህይወቱን በአሳዛኝ ሁኔታ ላጣውና ይህንን ማራቶን ለመሮጥ አስቀድሞ ወጥኖ ለነበረው የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቱ ኬንያዊ አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል። በርካታ አትሌቶችም አትሌቱን ለማሰብ ጥቁር ጨርቅ ክንዳቸው ላይ አስረው ውድድራቸውን አድርገዋል::
የማራቶን ባለክብረወሰኑ ኪፕተም በሀገሩ በገጠመው የመኪና አደጋ ሕይወቱን ባያጣ በዚህ የሮተርዳም ማራቶን አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን በዓለም አትሌቲክስ እውቅና የተሰጠው ከሁለት ሰዓት በታች በማጠናቀቅ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት የመሆን ፍላጎት ነበረው::
የሮተርዳም ማራቶን ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበበት እንደነበር ይታወሳል:: በላይነህ በ1988 የሮተርዳም ማራቶን ነበር ርቀቱን 2፡06፡50 በማጠናቀቅ በወቅቱ አዲስ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ያስመዘገበው:: በላይነህ ይህን ውድድር እኤአ 1987፣1988፣1989፣1996 አራት ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛ ታሪክ ያለው አትሌት ሲሆን፤ ከእሱ በኋላ በወንዶች ሮተርዳም ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበ አልተገኘም:: የውድድሩና የቦታው ክብረወሰን ግን 2021 ላይ በአብዲ በሽር 2፡03፡36 የተመዘገበ ነው:: በሴቶች የቦታው ክብረወሰን ደግሞ በለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ባለድሏ ኢትዮጵያዊት አትሌት ቲኪ ገላና 2012 ላይ በ2፡18፡58 ሰዓት እንደተመዘገበ ይታወሳል::
አትሌት አሸቴ በከሪ ለሁለተኛ ጊዜ የሮተርዳም ማራቶን አሸናፊ መሆን ችላለች፤
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም