ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልም ሆነ፣ በ2030 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጎራ ለመካተት የሚያስችሏትን ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ለዚህም በግብርናው፣ በማዕድን፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ እና በሌሎችም መስኮች እየሠራች ባለችው ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ነው፡፡
አንድ ሀገር ደግሞ ነጻነትና ሉዓላዊነቷ የተሟላ ሆኖ የሚቀጥለው፤ ያ ሀገር ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮቹን በራሱ መከወን የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ሲችል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የሀገር አንድነትና ነጻነቷን ያዘለቀችበትን የአውደ ግንባር ገድል የፈጸመች ቢሆንም፤ ይሄ በዋጋ የተገኘው ነጻነቷ ግን በኢኮኖሚው መስክ ባላት ደካማ አቅም ምክንያት ሲፈተን ኖሯል፡፡
ይሄን የሚፈትን ነጻነት ይዞ ደግሞ እንደ ሀገር የሚፈለገውን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እውን ማድረግ አይቻልም፡ ፡ በመሆኑም ቢያንስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑ ታምኖበት በዚህ ላይ በሚገባ ተሠርቷል፡፡ እናም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ከውጪ ማስገባት እንድታቆም ብቻ ሳይሆን፤ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ስንዴን ማቅረብ የቻለችበትን ተግባር አከናውናለች፡፡
በዚህ ረገድ በተለይ ከለውጡ ማግስት በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ከዘለቀው የኢትዮጵያ ግብርና የተሻገረ ሥራን መሥራት ተችሏል፡፡ የበጋ መስኖ ልማት ደግሞ ከእነዚህ ተግባራት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ምክንያቱም በመስኖ የሚለማ ሰፊ መሬት እና ይሄንን መሬት ማልማት የሚችሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ያሏት ኢትዮጵያ፤ ይሄንን አቀናጅታ ዜጎቿን መመገብ የምትችልበትን አቅም መፍጠር ተችሏል፡፡
ቀደም ሲል ያውም በተበጣጠሰ መልኩ በአስር ሺዎች ሄክታር ላይ ብቻ ይከናወን የነበረውን የመስኖ ልማት ሥራ፤ ዛሬ ላይ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይ መተግበር ተችሏል፡፡ በዚህም ከሺዎች ወደ ሚሊዮኖች ኩንታል ምርት ማግኘትም አስችሏል፡፡ ይሄው ተግባር ነው ኢትዮጵያን ስንዴ ከመለመን ወደ መስጠት፤ ስንዴን ከመሸመት ወደ መሸጥ እንድትሸጋገር ያደረጋት፡፡
ከሰሞኑ ከግብርና ሚኒስቴር የወጣ መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ውጥን ተይዞ፤ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህም ወደ 120 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዷል፡፡
ከሦስት ሚሊዮን ሄክታሩ ላይ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ውስጥም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ላይ ያለው ሰብል ተሰብስቦ፤ ከ58 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል፡፡ ቀሪው ሰብል የመሰብሰብ ሥራም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዘርፉ እየተከናወነ ያለው ተግባርም ሆነ እየተገኘ ያለው ውጤት ደግሞ የግብርና ምርትን በአይነትና በመጠን ከማሳደግ አኳያ ከፍ ያለ ሚና ያለው ሲሆን፤ የዜጎችን የምግብ ሥርዓት ለማሻሻልም ሆነ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ከግቡ እንዲደርስ የማይተካ ድርሻ አለው፡፡
በዚህ መልኩ በበጋ ስንዴ የታየውን ውጤት የበለጠ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ደግሞ፤ እንደ ሀገር የተሟላ ነጻነትንም፣ ብልጽግናንም እውን ለማድረግ ያለውን የመንግሥት ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በተለይ በአረንጓዴ ዐሻራም ሆነ በሌማት ትሩፋት ሥራዎች ያሉ ጅምሮችና ውጤቶቻቸው የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
ለምሳሌ፣ ከስንዴ ባሻገር በሩዝ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት እርባታና የእንስሳት ተዋፅኦዎች፣ በሻይ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ ዘርፎች የተሰሩትም፣ እየተሰሩ ያሉትም ሥራዎች በውጤት የታጀቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን በመቻል ቢያንስ ለርዳታ የሚዘረጉ እጆቿ ጫና ከመዳረግ ወጥተው፤ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ድጋፍ ማድረግ የምትችልበትን ሙሉ ነጻነት የሚያጎናጽፏት ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን፣ ይሄ ነጻነቷ የሚፈጥርላት ከፍ ያለ የማድረግም ሆነ የመደመጥ አቅም አለ፡፡ ይሄ አቅም ደግሞ የራሷን የልማት ሃሳብና ንድፍ ወደ ተግባር ለመቀየር በምታደርገው ጥረት ውስጥ ቢቻል ደጋፊ ኃይሎችን ለማሰባሰብ፤ ባይቻል ግን እጇን ሊጠመዝዛት የሚዳዳ ኃይል እንዳይኖር ማድረግ ያስችላታል፡፡ እናም አሁን ላይ በበጋ መስኖ የስንዴ ልማቱም ሆነ እሱን ተከትለው እየተመዘገቡ ካሉ ውጤቶች መረዳት የሚቻለው፤ እንደ ሀገር ተባብሮ እና በሙሉ አቅም ተግቶ መሥራት ከተቻለ እውን እንዲመጣ የሚፈለገው የተሟላ ብልጽግናን ከመሳካት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ነው!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም