ድሮ ድሮ በፌስታሎች ላይ ሳይቀር “ደንበኛ ንጉስ ነው” የሚል ጽሁፍ መመልከት የተለመደ ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደንበኛ ንጉስነት ተቀይሮ ይሆን ወይም በሌላ፣ ቢያንስ ጽሑፎቹን ማየት እየቀረ ነው:: በሀገራችን ደንበኛን ያማከለ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የግል ድርጅቶች በአንጻራዊነት የተሻሉ ናቸው::
ምንም እንኳን ከሀገራችን አንጻር የተሻሉ የተባሉት የግል ድርጅቶችም ቢሆኑ ካደጉት ሀገራት አንጻር ካየናቸው ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው:: በውጭ ሀገራት ድርጅቶች ደንበኛ ለገዛው እቃ መመለሻ በርካታ ጊዜ ከመኖሩም በላይ “የገዛሁት እቃ አልተመቸኝምና ገንዘቤን መልሱ″ ተብሎ ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሹ “ምን እናሻሽል″ እና “ለፈጠርንብዎ አለመመቸት ይቅርታ″ የሚል ነው::
እኛ ሀገር ግን በተቃራኒው ነው፤ በአብዛኞቹ የመሸጫ ቦታዎች “የተሸጠ እቃ አይመለስም” የሚል በጉልህ የሰፈረ ጽሑፍ መመልከት አዲስ አይደለም:: ምነው ቢሉ “የቤቱ ሕግ ነው”፤ በጣም የተሻለ ደንበኛ ያስተናግዳሉ ከተባለ እቃውን በሌላ እቃ መለወጥ ቢተባበሩ ነው:: እሱንም ቢሆን መጀመሪያ የተወሰደው እቃ ዋጋው እንደሚቀንስ በመንገር ለተመሳሳይ እቃ የዋጋ ጭማሪ መጠየቅ የተለመደ ሆኗል::
ያም ቢሆን በአንጻራዊነት የደንበኛ አያያዝ ጉዳይ በግል ተቋማት የተሻለ እንደሆነ ይነገራል:: በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት ንጉሱ ደንበኛው ሳይሆን እንዲያገለግል የተቀመጠው አካል መሆኑን በርካቶች በምሬት ያነሱታል:: ለዚህም መጉላላቱም ሆነ ፊት መነሳቱ የሚጀምረው የአገልጋዩን፣ የተገልጋዩን እንዲሁም የተቋሙን ደህንነት እንዲጠብቁ ከተመደቡ መግቢያ በር ላይ ከሚገኙ የጥበቃ አባላት ይጀመራል::
የእነሱን ማመነጫጨቅ አልፎ የሚመለከተው አካል ጋ የደረሰ ባለጉዳይ “ስብሰባ ላይ” እንደሆኑና መቼ እንደሚመለሱ እንደማይታወቅ ይነገረዋል:: “ለምን?” የማለት መብት የለውም:: በአብዛኛው ከቢሮ የሚወጡ ባለሙያዎችም ሆኑ አመራሮች ሰው ወክሎ ያለመሄድ ችግር ይስተዋልባቸዋል::
በዚህ የተነሳ ባለጉዳይ የግልም ሆነ የመንግሥት ሥራውን እየተወ መመላለስ ግድ ይለዋል:: ያኔ ታዲያ በር አካባቢ ለሚያንዣብቡና “ጉዳያችሁን በአጭር እንድንጨርስላችሁ ክፈሉ” ለሚሉ ደላሎች ይጋለጣል:: እነዚህ ጩልሌዎች እውነት ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጉዳይ ማስፈጸም የሚችሉበት ሰንሰለት ኖሯቸው ሊሆን የሚችሉበት በርካታ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ::
ከዚሁ በተቃራኒ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በተቋሞቹ በቂ መረጃ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ የሚፈጠረውን የሰው ምልልስ ለግል ጥቅማቸው ለመጠቀም በማሰብ ብቻ፤ ምንም በተቋሙ ከሚሰሩ አካላት ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው “ጉዳያችሁን እናስጨርስላችሁ፤ ውስጥ ሰው አለን” በማለት ከበርካቶች ብር ለሚቀበሉ አካላት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል::
የዚህ ሁሉ መነሻ በትክክል መረጃ የሚሰጥ አካል አለመኖር፤ ጉዳዩን የያዘው ባለጉዳይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢሮ በማይሆንበት ወቅት እንደ ተቋም ተተካክቶ መሥራት የሚቻልበት ሥርዓት አለመኖሩ ነው:: እንኳን ሌላ አገልግሎት ፈልጎ የሄደ የመንግሥት ቢሮዎች ተገልጋይ ይቅርና የተጠቀመበትን አገልግሎት ክፍያ ልክፈል ወይም ለማገኘው አገልግሎት ክፍያ ልክፈል የሚል ተገልጋይ ክፍያ ለመክፈል ደጅ መጥናት ይጠበቅበታል::
ከዚህ ውስጥ የአገልግሎት ክፍያ ልክፈል ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያመራ ተገልጋይ ክፍያውን ለመክፈል መብራት አለመኖሩን መስማት የተለመደ ነገር ነው:: በአቅራቢያው የሚገኙ ድርጅቶች የመብራት ችግርን ለመቅረፍ በጄኔሬተር መጠቀምን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን በአካባቢው የተነሱት ጄነሬተሮች በሚያወጡት ድምጽ መረዳት ቢቻልም፤ “ክፍያ ተቀበለኝ” የሚባለው ድርጅት ግን በብዛት ይሄን አማራጭ ሲወስድ አይታይም::
ሠራተኞቹም መብራት “ይመጣል ጠብቁ”፤ ወይም “ሌላ ቅርንጫፍ ሂዱ” የሚል ሃሳብ ከመስጠት በዘለለ “መች ይመጣል?” ሲባሉ “እኛ አናውቅም” የሚል መልስ በመስጠታቸው ምንም ቅሬታ አይሰማቸውም:: መብራት መች እንደሚመጣ ለማወቅ ከተቋሙ ሠራተኛ በላይ ለጉዳዩ የቀረበ ሰው ከወደ የት ይገኛል?
ሌላው በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ አገልግሎቶች እንዳይሻሻሉ የሚያደርገው ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢ ጆሮ ያለውና የሚያርም በቂ አካል አለመኖሩ ይመስላል:: በየቢሮዎቹ “በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ የተሰማዎትን አስተያየት ያስፍሩ” የሚሉ ትልልቅ፣ አቧራ የጠገቡና ተገልጋዩም አገልጋዩም በቅጡ የማያያቸው የመሰሉ አንዱ ጥግ የሚቀመጡ አጀንዳዎች ሃሳብን ለማስፈር ብዙም አይጋብዙም::
ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመኑ የማህበራዊ ሚዲያ ነውና በተቋማት አገልግሎት ተጉላልተናል፤ ቅሬታ ተፈጥሮብናል፤ እንዲሁም በደል ደርሶብናል፤ የሚሉ አካላት ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ሲመጡ እየተመለከትን ነው:: ታዲያ በዚህ ሂደት ወቀሳ የሚቀርብባቸው አካላት መልስ ካለመስጠት አንስቶ መልስ ሲሰጡም ጉዳዩን ከማጣራት ይልቅ “ስም የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብናል”ና መሰል ምክንያቶችን በመደርደር ጉዳዩን የማቃለል ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ::
መገልገል መብቱ የሆነ ተገልጋይ በተሰጠኝ አገልግሎት ቅሬታ ፈጥሮብኛል ሲል በደፈናው ተቋማችንን አናስነካም ከሚል ድርጊቱን ሳያጣሩ መካድ ቅሬታ ለሚቀርብበት ተቋምም አይጠቅምም:: እንደ አንድ ተራማጅ ተቋም፣ ለድርጅቱ የሚጠቅመው ጊዜ ወስዶ የቀረበው ቅሬታ እውነት ነው ወይስ ሐሰት፤ እውነት ከሆነስ በማንና እንዴት ሊፈጸም ቻለ የሚለውን አረጋግጦ ከነተወሰደው እርምጃ ሲገለጽ ነው:: ያኔ ለተገልጋይ ድርጅቱ ከተባለው ሕገወጥ ድርጊት ጋር ተባባሪ አለመሆኑንና ድርጊቱ በጥቂት ሕገወጦች የሚፈጸም መሆኑን ስለሚያሳይ ከድርጅቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዳይቋረጥ ያደርጋል::
ይህ ሳይሆን ሲቀርና ያለምንም ማጣራት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲፈረጁ በቀጣይ በደል የሚደርስባቸው አካላት ከመፈረጅ ውጪ ምንም አናመጣም በሚል በደላቸውን ለማፈን ይዳረጋሉ:: የድርጊቱ ፈጻሚዎችም ሀይ ባይ አካል እንደሌለ ስለሚሰማቸው በሕገወጥ ሥራቸው ለመግፋት ይበረታታሉ:: የደንበኞችን ቅሬታ ሰምቶ ጉዳዩን ከመሰረቱ የማጣራት ሥራ መስራት ፣ ጥፋት ሲፈጸምም የእርምት እርምጃዎች መውሰድ ሊለመድ ይገባል:: ያኔ በቀጣይ ሌሎች ሕገወጦችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳን መቀነስ ይቻላል::
ዛሬ፣ ዓለም አንድ እየሆነች ነው፤ በዚህ የተነሳም በሀገራችን ለውጭ ሀገር ድርጅቶችና ዜጎች ዝግ ሆነው የቆዩ የሥራ ዘርፎች ከዕለት ወደ ዕለት ክፍት እየሆኑ መምጣታቸው አይቀርም:: ያኔ ብቸኛ የአገልግሎት ሰጪ ሆነው በመቆየታቸው ያላዳበሩት ደንበኛን ያስቀደመ አገልግሎት መስጠት ለኛዎቹ ተቋማት ሲከብዳቸው፤ እድሜ ልካቸውን “ደንበኛ ንጉስ ነው!!!” እያሉ ደንበኛን ያማከለ አገልግሎት ሲሰጡ ለከረሙ የውጭ ተቋማት መልካም እድል ይፈጥርላቸዋል::
የመንግሥት ተቋማት ኅብረተሰቡ ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀር እንደሚቀጡት ሁሉ፤ መብቱን የሚጠይቅበት፣ ጊዜውን ሳያባክን የሚፈልገውን አገልግሎት አግኝቶ የሚሄድበት አሠራር ማስፈንን የአገልግሎታቸው አንድና አቢይ አካል ሊያደርጉ ይገባል::
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም