አብሮነት ያጸናው የታሪክ ሰነዳችን

የሀገር መሀል አንጓ ሆነው ከትውልድ ትውልድ ከተሻገሩ እውነቶች ውስጥ አብሮነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል:: ከዚህ ስም ጋር ዳብረንና ተዋህደን ፊተኛ ሀገርና ሕዝብ ስንሆን መነሻችን ወንድማማችነት ነው:: ርቀን በክብርና በሰብዓዊነት ማማ ላይ ስንሰቀል፣ የነፃነትና የፍትሕ ራሶች ስንባል መነሻችን አብሮነት ነው::

አብሮነት ለአንድ ሀገር እንደ ምሰሶ ነው:: ቤት በምሰሶ እንደሚቆም ሀገርም የምትቆመው በሕዝቦቿ የአንድነት መንፈስ ነው:: ይሄ እውነት ስማችን፣ ማንነታችን፣ መገለጫችንና አርማችን ሆኖ ከትላንት ወደዛሬ መጥቷል:: ወደነገም ይቀጥላል::

ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ ቀድሞ የሚነሳው አብሮነት ነው:: እንደ ዓድዋ ያሉ በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በአካዳሚ የሰለጠኑ ወታደሮችን ያሳፈረ፣ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያለ ብዙዎች በአይችሉም ሲስቁብን ችለን የማሳየታችን ዋናው ሚስጢር የህብረት ቡዳኔአችን ነው::

የታሪኮቻችን ደማቅ ገድሎች በወንድማማችነት የጸኑ እንደሆኑ ብዙ ታሪኮችን እንደማስረጃ መጥቀስ እንችላለን:: ተለያይተን ፊተኛ ሆነን አናውቅም:: እንድንለያይ የሚያደርጉ የታሪክ ውርርስም የለንም::

ተደጋግፈንና ተወራርሰን ከእኔ ለእናተ ከእናተ ለእኔ በሆነ የአብሮነት ስብጥር ጎጆ የቀለስን ነን:: እንዴት እና በምን ጥበብ ሀገርና ሕዝብ እንደሆንን ብንጠይቅ ድብልቅ ታሪክ፣ ቅይጥ ማንነትን ከዳበሩ ውርርስ ባሕሎቻችን ጋር እናገኛለን::

የእኔ የአንተ በሌለው የአብሮነት ባህል ውስጥ ተወልደን ስናድግ ተፍገምግመን እንድንቆም ሳይሆን ርቀን እንድንጓዝ ነው:: ኢትዮጵያዊነትን ከአባቶቻችን ስንቀበል በዘርና ብሔር ያልተቧደነ ትውልድ እንድንፈጥር ነው:: እዚም እዛም የምንሰማቸው የብሔር እሳቤዎች ህብረታችንን ከማላለት፣ አንድነታችንን ከማዛል ባለፈ ጥቅም አይሰጡንም::

በክብር ምንጣፍ ላይ ያራመዱን የአባቶቻችን እግሮች፣ በነፃነትና በሰውነት ሚዛን ላይ ያሳረፉን የፊተኞቻችን ልቦች በሀገር ፍቅር ጣይ የወጣባቸው፣ በአብሮነት እውነት የሰነዱ ናቸው:: እንደኔና እንደእናንተ ለማንም በማይበጅ የብኩርና ግፊያ ተጋፍተው የወደቁ ሳይሆኑ ተቃቅፈው የዘለቁ ነበሩ::

ሳንተቃቀፍና ይቅር ሳንባባል የአባቶቻችንን ሀገር አንዋሃዳትም:: ሳንያያዝና ሳንደጋገፍ ህልሞቻችንን ማስቀጠል የማይታሰብ ነው:: በነጣጣይ ትርክት የነጣጠሉን የሀገርና ሕዝብ ባላንጣዎች በእኛ አበሳ ውስኪ እየተጎነጩ እንደሆነ ብናውቅ፣ በአብሮነታችን ውስጥ ጥላቻን ያስቀመጡ የጨዋ እሾሆች የእኛ መነካከስ ለነሱ ልብ አንጠልጣይ ድራማቸው እንደሆነ ብናውቅ በሴረኞች ሴራ ጥንተ ፍቅራችንን ባላጎሽን ነበር:: መነሻው ፍቅርና አብሮነት የሆነ ሕዝብ ከየት ተነስቶ እዚህ እንደደረሰ የሚያውቅ ሕዝብ ነው በትንሾች ሴራ፣ በክፉዎች ተንኮል ክብሩን እንዲጥል ልዕልናው አይፈቅድም:: የለበስነው የክብር ልብስ፣ የተጎናጸፍነው የታሪክ ካባ ህብረ ብሔራዊነት የሸመነው የኢትዮጵያዊነት ሸማ ነው:: ማንም ሊያሳድፈው እና ሊያቆሽሸው አይቻለውም::

እኛ ለኢትዮጵያ ደመራ እንደሚያበራ ችቦ ነን:: በአንድ ተቋጥረንና አብረን ለሀገራችን ብርሃን የሆንን:: እሳቱ ከነኩት ያቃጥላል ከተጠቀሙበት ደግሞ ያበስላል… እኛም እንዲሁ ነን:: ሀገራችን ለእኛ መጠሪያና መድመቂያ ስማችን ናት:: በአንድነትና በወንድማማችነት ከዚም ከዛም ተሰባስበን ነው ሀገራችንን የማገርነው::

አንድነት ኢትዮጵያዊነት የተሠራበት ድርና ማግ ነው:: በታሪክ ድርሳን ላይ ባለታሪክ ሕዝቦች ተብለን የተጠራነው አንድም በህብረታችን አንድም ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ስለሆንን ነው:: በጋራ ተጉዘን ያልወጣነው ዳገት፣ ያላሸነፍነው መከራ የለም:: ለዚህ ኢትዮጵያዊነት ጠንስሶት አንድነት የወለደው ታሪካችን ምስክር ነው::

ትላንትን ተያይዘን እንዳለፍን ዛሬም ለገጠሙን ችግሮች መያያዝ ነው የሚያዋጣን:: ችግሮቻችን በልጠውን የመፍትሔ ሃሳብ አጥተን ባለመግባባት ውስጥ የቆምንው በጋራ ከመጓዝ ይልቅ ብቻነትን በመምረጣችን ነው:: የተጀመረው የእርቅና የሰላም ንቅናቄ ከዳር ደርሶ ታሪካችን ከጦርነት ወደ ሰላም ጥንፍ ከረገጠ ብሔርተኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲሸጋገር መያያዛችን ማስቀጠል አለብን::

ችግሮቻችን በመለያየታችን በኩል የገቡ ናቸው:: እነዚህ ቀዳዳዎች እስካልተደፈኑ ድረስ ሰላም ማምጣትም ሆነ ሰላማዊት ሀገር መፍጠር አይቻልም:: ቀዳዳዎቻችንን ድፍነን የጋራ ሀገር ለመፍጠር ከመለያየት ማጥ ውስጥ ወጥተን በጋራ መጓዝ ለነገ የማንለው ግብራችን ነው::

መለያየት ማቅ ያለብሳል:: መለያየት ሰላምን ነጥቆ የማንግባባባቸውን የንትርክ አጀንዳ ከመስጠት ባለፈ እርባና የለውም:: ከምንም በላይ ሰላም የሚያስፈልገን ሕዝቦች ነን:: ከምንም በላይ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል።

የተስፋ ጭላንጭሎች በሁላችንም ላይ ብርሃናቸውን እንዲረጩ ለሰላም ሂደቱ ሃሳብ በማዋጣት የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል:: አሁን ባለው ፖለቲካዊም ሆነ ሕዝባዊ ሁኔታ በጎ ትርክቶች ዋጋቸው የላቀ፤ ለእርቅና ለሰላም ሂደቱ ተጨማሪ ጉልበትን የሚሰጥ ነው::

ኢትዮጵያዊነት አንድነት ያሾረው የጋራ ድር ነው:: ሾረን ታሪክ ስንሠራ፣ ሥርዓት ስናበጅ በተዋጣ ሃሳብና ፈትል ነው:: ይሄ የሹረት ድር የጠነከረና የበረታ የሰማኒያ እና የከዛ በላይ መልክና ወዝ፣ ባህልና ወግ ጥምረት ነው:: እንዴትም በምንም ሊበጠስ አይችልም::

በአባቶቻችን የእውነትና የእምነት፣ የፍቅርና የአብሮነት እቅፍ የተገመደ ነው:: የበለጡን ሀገራት አንድነታቸውን አጠንክረው በመዝለቃቸው ነው:: ለዓለም ጥቁሮች የትንሳኤ ጮራ ነን እያልን ለራሳችን መሆን እንኳን እየቻልን አይደለም:: ችግሮቻችን ወደጦርነት እየወሰዱን ነው፣ በጋራ ተግባቦት በኢትዮጵያዊነት የምትጠራ አንድ ሀገር ለመፍጠር እየተንገዳገድን ነው::

ስለፍቅር ልዩነቶቻችንን በእርቅ እና በዳበረ ሃሳብ መፍታት የመጨረሻው እንደሀገር የመቀጠል አማራጫችን ነው:: አብሮነት በጠንካራ ልቦች ውስጥ የበቀለ በቅሎም የጸደቀ፣ ጸድቆም መቶ ያፈራ ምርጥ ዘር ነው:: ቆራጥነት ይጎለናል:: ከምኞት ባለፈ ሰላማችን እንዲመለስ፣ አብሮነታችን እንዲቀጥል የሚጠበቅብንን ዋጋ ስንከፍል አይታይም::

ሀገር የጥቂቶች የሃሳብ ዘር አይደለችም:: ስለአንድነቷና እድገቷ ብዙዎቻችን እናስፈልጋለን:: ቀጣይ በሚኖረው ሀገራዊ ምክክር እያንዳንዳችን አስፈላጊዎች ነን:: በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አያስፈልግም፣ አላስፈልግም የሚባል ሃሳብና ሰው የለም::

ከእኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ከቻልን በእኛ ኃላፊነት ውስጥ የሚስተካከሉ ብዙ ነገሮች አሉ:: በሁሉም መስክ ላይ እንደ ችግር ከሚነሱ ተግዳሮቶች ውስጥ የመጀመሪያው ራስን የማግለል ሁኔታ ነው:: ራሳችንን አግለን፣ አያገባኝምና አይመለከተኝም እያልን በልካችን የምንፈጥራት ሀገር የለችም::

እኛ ያልተሳተፍንበት፣ ሃሳብ ያላዋጣንበት ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ሰላምና አብሮነት የራስን ዐሻራ እንደ አለማሳፈር ተቆጥሮ ሊቆጨን የሚገባ ድርጊት ነው:: በሕይወታችን፣ በኑሯችን ውስጥ ድንቅ ነገር እንዲከሰት ከፈለግን ያለመነጋገር ደካማ ልማዶቻችንን ትተን የሃሳብ ልውውጥ እናድርግ::

ራሳቸውን በከፍታ ላይ ያስቀመጡ ታላላቅ ሀገራት በምንም ሳይሆን በሃሳብ የዳበሩ ናቸው:: የእኛ ማነስ፣ የእኛ ድህነት፣ የእኛ ኋላ መቅረት፣ የእኛ አለመግባባት፣ የእኛ ሰላም ማጣት፣ የእኛ ብሔርተኝነት፣ የእኛ ጎጠኝነት፣ የእኛ መለያየት መነሻው በዳበረ የሃሳብ ልዕልና ውስጥ አለማለፋችን ነው::

ዓለም የዘመናዊነት ካባ የደፋችው፣ ሕዝብ የስልጣኔን በትር የጨበጠው እኮ በሃሳብ በኩል ነው:: ተነጋግረን ካልተግባባንና በአብሮነት ሰላም ካላወረድን ስለሰላም ሌላ ምን መንገድ አለን? በሃሳብ እንዳብር:: ፖለቲካው በሃሳብ ይዳብር፣ ኢኮኖሚው በሃሳብ መሠረቱን ይጣል:: ማህበራዊ ጉርብትናው በሃሳብ ልውውጥ ይታደስ::

ሃሳብ አጥተን ስለፍቅርና ስለሰላም ጦር ብናነሳ፣ ፍቅር አጥተን በዘርና በብሔር ብንቧደን የዚህ ዘመን የመጨረሻው አላዋቂነት ነው:: ሰላምን በጦርነት ለማምጣት በመሞከራችን የብዙዎች መሳቂያ ሆነናል:: መለስ ብለን ራሳችንን መፈተሽ አለብን::

ምን አጣላን ? ከአለመግባባታችን ጀርባ እነማን አሉ? በምን እንዳንግባባ አደረጉን ? ስንል እንጠይቅ:: ከዚህ መጠይቅ በኋላ ዋጋ ባለው ሃሳብና ተራማጅ በሆነ እይታ ለእርቅና ለተግባቦት መቀመጥ ውጤት የሚመጣበት አካሄድ ነው:: የላቀ ሰውነት በላቀ ሃሳብ በኩል የሚታይ ነው::

የላቀ ሀገርና የላቀ መንግሥት በላቀ ሃሳብ በኩል የሚገለጥ ነው:: በእርስ በርስ ፉክክርና በወንድማማቾች ግፊያ እየወደቅንና እየተነሳን መከራችንን ስንበላ የኖርንው በዳበረ ሃሳብ ማጣት ነው:: በሃሳብ እንዳብር፣ በሃሳብ እንበልጽግ፣ በሃሳብ እንሸናነፍ::

ያለፉትን አራት እና አምስት ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ ስለሃሳብ ተነጋግረንባቸዋል:: በሃሳብ ስንሸናነፍ ግን አንታይም:: እየፈረስን ያለንው በሃሳብ ስላልተገነባን ነው:: ከፊታችን ያለው ብዙሃነት የሚንጸባረቅበት የብሔራዊ የእርቅና የተግባቦት መድረክ መነሻው ሃሳብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ተገልጿል:: በዚህ መንገድ ጀምረን ስንጨርስ ብቻ ነው ራሳችንን ነፃ የምናወጣው::

ያጸናው የታሪክ ሰነዳችን በአብሮነት ሃሳብ የዳበረ እንደነበር ነጋሪ አያሻንም:: ኢትዮጵያ ብለን ጀምረን ነው ፋና ወጊ የወጣን:: እኛ ብለን ተነስተን ነው ደማቆች የሆነው:: አሁን እኛነትን ወደእኔነት፣ ኢትዮጵያዊነትን ወደጎጠኝነት ቀይረን ተነጋግረን መግባባት የማንችልበት ራስን ብቻ የማድመጥ ጊዜ ላይ ደርሰናል::

ይሄ ለማንም የማይጠቅም ታሪክ የሚያበላሽ አብሮነትን የሚንድ እጅግ አደገኛ ነገር ነው:: ህልማችን ለውጥና ብልጽግና አብሮነትና ወንድማማችነት ከሆነ ከተዘፈቅንበት ሃሳብ አልባ ምናብ እንውጣ:: ራሳችንን ነፃ እስካላወጣን ድረስ ነፃ አውጪ የለንም:: ነፃ መውጣታችን የሚረጋገጠው ደግሞ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ፈትቶ አብሮነትን ማስቀጠል ሲቻል ነው::

ታሪክ ከመዝከር ወጥተን ታሪክ ሰሪ እንዲወጣን ከተቧደንበት የብሔር ሽኩቻ ተላቀን ወንድማማችነትን እናዳብር:: ጓዳ ጎድጓዳችን ቢፈተሽ ድብልቅና ውህድ ታሪክ እንጂ የብቻ ታሪክ አይገኝበትም:: ማንም ብቻው ጸንቶ ኢትዮጵያን አላጸናም:: አብረን ተጉዘን ነው ከዚህ የደረስነው ፤ አብረን ለመቀጠልም መያያዝ ያስፈልገናል::

ቀጣዩን ሀገራዊ ርምጃ ከሃሳብ እንጀምር:: ከጥልና ክርክር፣ ከጥላቻና ቂም ጀምረን ብዙ ያፈረስናቸው ታሪኮች አሉን:: የፖለቲካ ምህዳሩ በሃሳብ እንዲታነጽ፣ ማንም ምንም ይሁን በሃሳብ ልቆ መገኘትን የሕይወት መርሁ ማድረግ ይኖርበታል።

ማንም በፍቅር ካልሆነ ማንንም ታግሎ መጣል አይችልም:: የመሳሪያ አፈሙዛችንን መልሰን በፍቅር መቧደንን ቀጣይ መሪ እቅዳችን እናድርግ:: እኛው በእኛ እያለቀስንና እየተወቃቀስን እስከመች እንቀጥላለን ?።

ማንም መጥቶ የደፈረን የለም:: የምንደፋፈረው እርስ በርስ ነው፣ የምንሞተው፣ ጥርስ የምንነካከሰው እርስ በርስ ነው ከዚህ ታሪክ ወጥተን የፍቅር ቤት በመሥራት ከጉስቁልና የምንወጣበት ሁነኛ አቅጣጫ እናጽና::

በእኛ ፍቅር ማጣት ኢትዮጵያ ሀገራችን አይኗ እንባ ካቀረረ ቀይቷል:: እንባዋን ለማበስ ፍቅር መሐረባችን ይሁን:: ተወቃቅሰን ሳይሆን ተሞጋግሰን ሀገር እንሠራ:: ተነቃቅፈን ሳይሆን ተመሰጋግነን በጋራ መኖርን ባህል እናድርግ:: ተራርቀን ሳይሆን ተጠጋግተን፣ ተቀያይመን ሳይሆን ተነፋፍቀን፣ ተናንቀን ሳይሆን ተከባብረን የተስፋ መጻኢ ጊዜያችንን እንውለድ::

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You