በአማራ ክልል ከ385 ሺህ ኩንታል በላይ የበጋ ስንዴ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፦ በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ385 ሺህ ኩንታል በላይ የበጋ ስንዴ ምርት መሰብሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የግብርና ቢሮ የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ተሻለ አይናለም ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል ከ151 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል። በዚህም ከዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

በክልሉ ደጋማና ቆላማ አካባቢዎች የደረሰውን ሰብል የመሰብሰብ ሥራ ተጀምሯል ያሉት አቶ ተሻለ፤ 38 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው ስንዴ ተሰብስቧል፡፡ በአጠቃላይ እስከ አሁን ከ385 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ከበጋ መስኖ ስንዴ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ውጤታማነትን ተገንዝቦ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል ያሉት አቶ ተሻለ፤ ለአርሶ አደሩ የማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የውሃ ፓምፕ፣

የስልጠና እና የተባይ መከላከያ ኬሚካል እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ግብዓቶች በሙሉ እንዲሟሉ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እያደገ በመምጣቱ አርሶ አደሩ በመስኖ መሬት ላይ ከሁለት ጊዜ በላይ ማልማት እንዲችል አድርጓል ያሉት አቶ ተሻለ፤ ይህም በክልሉ የሚለማው የበጋ መስኖ ስንዴ የመሬት ሽፋን እንዲያድግ እና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ያሉት አቶ ተሻለ፤ የፀጥታ ችግር ባለባቸው ማለትም በጎንደር፣ ጎጃም እና በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴን ማልማት አልተቻለም። ይህም የምርት መጠኑ እንዲቀንስ አድርጎታል ብለዋል።

እንደ አቶ ተሻለ ገለፃ፤ ቢሮው በክልሉ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አቅዷል። ነገር ግን በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ሁሉንም መሬት ማልማት አልተቻለም። በቀጣይ ዓመት አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጣ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት ይደረጋል። ይህም ክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ የሚያለማውን የመሬት መጠን ያሳድጋል።

በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት የተጀመረው በ2013 ዓመተ ምህረት ሲሆን፤ በዚህም በየዓመቱ የሚለማው መሬት እና የሚገኘው ምርት እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You