“ኢትዮጵያ በቀጣናው የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነት መጠቀም እንዲቻል ሰፊ ተግባራት እያከናወነች ነው”- ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው የዓባይ ግድብ ቴክኒካል ቡድን ተደራዳሪ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው የውሃ ሀብቶችን በፍትሐዊነትና በእኩልነት መጠቀም እንዲቻል ሰፊ ተግባራት እያከናወነች ነው ሲሉ የዓባይ ግድብ ቴክኒካል ቡድን ተደራዳሪ ኢኒጅነር ጌድዮን አስፋው ገለጹ፡፡

የዓባይ ግድብ ቴክኒካል ቡድን ተደራዳሪ ኢኒጂነር ጌድዮን አስፋው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ በቀጣናው የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነትና በእኩልነት መጠቀም እንዲቻል ሰፊ ሥራዎች እየሠራች ነው፡፡

ኢንጂነር ጌድዮን አክለውም፤ የውሃ ሀብት ላይ ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ትብብሮችን እውን ለማድረግ የሀገሪቱ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ጉዞ በማድረግ ስለጉዳዩ ለማብራራት የሄዱበት ርቀት ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

80 በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቷ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ ናቸው ያሉት ኢንጂነር ጌድዮን፤ ከዚህ አኳያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጋር በሃይድሮ ዲፕሎማሲ ውስጥ መሳተፍም እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ አባይና ተካዜ ወንዞች ከሶማሊያ፣ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳንና ከግብፅ ጋር በጋራ ሀገሪቷ የምትጋራቸው ወንዞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን በተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት አብሮ ለመሥራት በሚያስችለው የትብብር ማዕቀፍ ተባባሪ እየሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ጌድዮን ገለጻ፤ የትብብር ስምምነቱ ያለፈውን የቅኝ ግዛት የውሃ ላይ ስምምነቶችን በአዲስ የስምምነት ማዕቀፍ የሚተካ ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ በኩል የተሳካ ዲፕሎማሲ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ግብጽ በቅርቡ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የዓባይ ግድብ ድርድር መቋረጡን ብታስታውቅም ኢትዮጵያ እንደ ሁልጊዜው ለውይይትና ያልተፈቱ የቴክኒክ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፈቃደኛ እንደሆነች አስረድተዋል፡፡

ከወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብሮችን በማጎልበት ሀብቶችን በፍትሐዊነትና በእኩልነት የውሃ ፖሊሲ እየተከተለች ነው ያሉት ኢንጂነር ጌድዮን፤ ይህም ለጋራ ተጠቃሚነት የምታከናውናቸው በጎ ተግባራትን የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ጌድዮን ገለጻ፣በውሃ ዲፕሎማሲ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ዩኒቨርሲቲዎች፣ዲያስፖራው እንዲሁም ወጣቱ የውሃ ፖሊሲ፣ስትራቴጂና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ መሥራት ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለወጣት ባለሙያዎች አስፈላጊውን ስልጠና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር መስጠት እንደሚገባና ለዚህም መንግሥት አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You