ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በቦስተን ማራቶን ለአሸናፊነት ይጠበቃሉ

የአሜሪካዊያን የነጻነት ቀን መታሰቢያ የሆነው 128 የቦስተን ማራቶን ዛሬ ይካሄዳል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የማሸነፍ ግምትን አግኝተዋል። የፕላቲኒየም ደረጃ በሚሰጠውና ከዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው የቦስተን ማራቶን ኬንያዊያን አትሌቶችም የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ረጅም እድሜ ባለው ትልቅ ውድድር 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች የገቡ 10 ወንድ አትሌቶች 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች የገቡ 9 የዓለማችን ምርጥ ሴት አትሌቶች የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል።

ከመቶ በላይ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ ከ30 ሺ በላይ ሰዎችን በሚያሳትፈው ወድድር በወንዶች የአምናው አሸናፊ ኬንያዊው አትሌት ኢቫንስ ቺቤት ትልቅ የማሸነፍ ቅድመ ግምትን ያገኘ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያዊው የቫሌንሺያ ማራቶን አሸናፊ አትሌት ሲሳይ ለማ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል። ኬንያዊው አትሌት በዚህ ውድድር የሚሮጠው የአምናውን ድል ለመድገም ብቻ ሳይሆን በመድረኩ ሦስት ተከታታይ ድል በማድረግ 5ኛው አትሌት ለመሆን ጭምር ነው። አትሌቱ ባለፈው ዓመት ውድድሩን 2፡5፡54 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሲሳይ ለማ፣ ሀፍቱ ተክሉ፣ ሹራ ቂጣታና ማሀመድ ኢሳ በትላልቅ የማራቶን መድረኮች ትልቅ ስም አላቸው። አትሌት ሲሳይ ለማ በቅርቡ በስፔን ቫሌንሺያ ማራቶን 2፡01፡48 በሆነ ሰዓት በማሸነፍ በወንዶች ታሪክ የምንጊዜም 4ኛ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቡ ይታወቃል። በ2021 በተካሄደው የለንደን ማራቶን እንዲሁ ማሸነፍ ችሏል።

የሁለቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን የተገመተው ሌላኛው ታንዛኒያዊው አትሌት ገብርኤል ጌአይ 2 ሰዓት 03 ደቂቃ ሰዓት ባለቤት በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ተፎካካሪ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ሀፍቱ ተክሉ በ2፡04፡34 እና ሹራ ቂጤታ 2፡40፡49 የሆነ ሰዓት የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት በመሆናቸው ፉክክሩን ከፍ አድርገዋል። እአአ በ2013 ባለድል የሆነው አትሌት ሌሊሳ ዴሲስ ሁለቴ ሲያሸንፍ በ2016 ለሚ ብርሃኑ ማሸነፍ ችሏል።

በሴቶች መካከል በሚደረገው አጓጊ ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ሔለን ኦብሪ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ብታገኝም ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ታዱ ተሾመና ህይወት ገብረማርያም ባላቸው የተሻለ ሰዓት ለአሸናፊት ከታጩት አትሌቶች ተርታ ተሰልፈዋል። አትሌት ታዱ ተሾመ በ2022 የቫሌንሺያ ማራቶን 2 ሰዓት ከ 17 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ምርጥ የግል ሰዓት ባለቤት ናት። ህይወት ገብረ ኪዳን 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ 23 ሰከንድ ምርጥ የግል ሰዓት አስመዝግባለች። በዚህም ቅድመ ግምቱ ለኦብሪ ቢሰጥም ኢዮጵያዊያዊያን በመድረኩ ባላቸው የተሻለ የአሸናፊነት ታሪክ እና ባላቸው ሰዓት ውድድሩን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

የሁለት ጊዜ የ5 ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮን የነበረችው ኦብሪ ከኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚጠብቃት ፉክክር ከባድ ይሆናል። የቦስተን ማራቶን የሁለት ጊዜ አሸናፊ ኤድና ኪፕላጋትና የ2018 አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ቀጥላ ትቀመጣለች። አትሌቷ የቤት ውስጥ ውድድሮች፣ የትራክና ሀገር አቋራጭ ውድድሮችን በማሸነፍ ወደር የማይገኝለት ሲሆን በ2022 የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን በኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶን አድርጋ 2፡25፡49 በሆነ ሰዓት ገብታለች። ከዚህ ውድድር 5 ወራት በኋላ በቦስተን በተካሄደ የተራራ ውድድር 2፡21፡38 ሰዓትን በማስመዝግብ አሸንፋለች። በሴቶች የውድድሩን ፈጣን ሰዓት ተመዝግቦ የሚገኘው በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ 2፡15፡51 የሆነ ሰዓት ነው።

ሰንበሬ ተፈሪ፣ አባብል የሻነህ፣ መሰረት በለጠ፣ ጥሩዬ መስፍን፣ ወርቅነሽ ኢዴሳ እና ዴራ ዲዳ ሌሎች በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች ይሆናል። አትሌት ፋጡማ ሩባ 1997-1999 ለሦስታ ተከታታይ ዓመታት በማሸነፍ ቀዳሚ አትሌት ነች። እአአ በ2016 አጸደ ባይሳ፣ ቡዙነሽ ዲሪባ በ2010 ጠይባ ኤርኬሶ የቦስተን ማራቶንን ያሸነፉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። ውድድሩ መካሄድ የጀመረው እአአ በ1897 ሲሆን 15 አትሌቶችን በማወዳደር ነው። ከአትሌቶች በተጨማሪ የተወዳዳሪዎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ደርሷል።በ1996 የተካሄደው ውድድር 38 ሺ ሰዎች ተመዝግቦ 36 ሺዎቹ ውድድሩን በመጀመር 35 ሺዎቹ ውድድሩን በመጨረስ በሪከርድነት ተመዝግቦ ይገኛል።

በውድድሩ የሚያሸንፉ አትሌቶች 150 ሺ ዶላር፣ 2ኛ ሆኖ የሚጨርሱ 75 ሺ ዶላር ሦስተኛ 40 ሺ ዶላር ይሸለማሉ። እስከ 10ኛ ደረጃን በመያዝ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ሪከርድ የሚያሻሽሉ አትሌቶች ተጨማሪ 50 ሺ ዶላር ይሸለማሉ።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You