በዚህ ጉዳይ ላይ ለብዙ ጊዜ ትዝብት አጋርቻለሁ። የማስተውለው ነገር ግን የሚረብሽ ስሜት አያጣውም። ሰሞኑን እንዲህ ሆነ።
ከውጭ ቆይቼ ወደ ቤት እየገባሁ ነው። የግቢው በር አካባቢ ስደርስ የተጎሳቆለ ልብስ የለበሰ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰውዬ እኔ በማልችለው ቋንቋ እያወራ ነው። ለካ እያናገረኝ ነበር። የተለመደው የልመና አይነት ነው ብየ ምንም ትኩረት ሳልሰጠው ገባሁና የግቢውን በር ዘጋሁ። ወዲያውኑ አንኳኳ! እሱ ሊሆን እንደሚችል ስለገመትኩ ቆጣ ብዬ ‹‹ምንድነው?›› ብየ ከፈትኩት። ይህኔ ነበር ውሎዬን ሲረብሸኝ የዋለው የጥፋተኝነት ስሜት ፀፀት የተከሰተው። የሚናገረውን ቋንቋ እንደማልችል ገብቶታል። ከሰሜኑ የሀገራችን ቋንቋዎች አንዱ ነው። እጁን ወደ አፉ እያለ እንደራበው በምልክት አሳየኝ። ቱታ ለብሼ ስለነበር የወጣሁት ከኪሴ ምንም የለም። እንዲጠብቀኝ በምልክት ነግሬው ቶሎ ቤት ገብቼ ትንሽ ነገር ሰጠሁት፤ ቋንቋውን በሚገባ ባልረዳውም በፊት ገጽታው በብዙ አመስግኖ ሄደ።
ወደቤት ከገባሁ በኋላ መጀመሪያ ላይ ባላዬ በማለፌ በመፀፀት፣ ቀጥሎ ደግሞ እየተባባሰ በመጣው እንዲህ አይነት ነገር ብዙ ሳስብ ቆየሁ። በሥራ ቀን ቤት የምውልበት አጋጣሚ የለም። ሰሞኑን ቤት ስለነበርኩ እንዲህ አይነት ነገሮችን እንደ አዲስ ነው እያየሁ ያለሁት። በር እያንኳኩ መለመን ተደጋጋሚ ነው። የልመና አይነቱ፤ አንዳንዱ አንኳኩቶ በቀጥታ መለመን ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ በር ላይ ሆኖ በተለያዩ የዜማ አይነቶች መጠየቅ ነው። ሁሉም ግን የችግሩን ሁኔታ ያሳያሉ።
ላምበረት አካባቢ ልብ ብላችሁ ከሆነ (እኔ ያስተዋልኩትን ማለቴ እንጂ በሁሉም ቦታ ነው) አብዛኞቹ የሚለምኑት ሕጻን ያዘሉ እና ልጆች ያስከተሉ እናቶች ናቸው። ገና ልጅ ሆና ልጅ ያዘለች ሴት ስትለምን በእያንዳንዱ እርምጃ ትታያለች።
አሁን አሁን በጣም ከመብዛቱና ከመለመዱ የተነሳ መደበኛ ሕይወት አድርገነዋል። ሁለትና ሦስት ሕጻናት ልጆች ይዛ የምትለምን እናት አይቶ የሚረበሽ ብዙም አይኖርም፤ ምክንያቱም ተለመደ፤ መደበኛ ሕይወት ሆነ። መንገድ ዳር ዝናብና ፀሐይ የሚፈራረቅባቸውን ሕጻናት ማየት እያስደነቀ አይደለም። ለዚህም ነው ሕጻናቱ አላፊ አግዳሚውን ልብሱን ይዘው ‹‹ጋሼ ዳቦ ግዛልኝ!›› ሲሉ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ልቀቀኝ!›› ወይም ‹‹ልቀቂኝ!›› በማለት እጃቸውን መንጭቀው የሚቆጧቸው። እነዚህ ሰዎች ምናልባትም ከሌላው ሰው በተለየ ሰብዓዊነት የሌላቸው ሞራለ ቢስ ሆነው አይደለም፤ መደበኛ ሕይወት ስለተደረገ ነው።
በሌላ በኩል፤ ችግራቸውን አያውቁላቸውም። የችግሩ ገፈት ቀማሽ ዘመድ አዝማድ የሌላቸው ሰዎች የሚያስቡት ሕጻናቱ የሚለምኑት በወላጆች ትዕዛዝ ብቻ ነው ብለው ነው። ወላጆች ደግሞ የሚያዝዟቸው ሥራ መሥራት ሰንፈው ለልመና ሱስ ብቻ ነው ተብሎ ይነገራል። የሚለምኑ ሰዎችን ‹‹ሠርተህ አትበላም?›› የሚል የተግሳጽ ምክር እንሰማለን፤ እየተባባሰ ሲሄድ እንጂ ችግሩን ሲቀርፍ ግን አልታየም።
ልመና እጅግ አፀያፊ ነገር ነው። የሚለምኑት ሰዎችም አፀያፊነቱን ያውቃሉ። ምናልባትም ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ይሆናል። ይህ ማለት ግን በስንፍና ብቻ የሚለምኑ የሉም ማለት አይደለም። እያወራን ያለነው ስለጠቅላላው የልመና ምክንያት ስለሆነ ነው።
ከልመና ምክንያቶች አንዱና ዋናው የሠላም እጦት ነው። ምንም ሰፊ ጥናትና ምርምር ሳያስፈልገው ማንም ሰው ማረጋገጥ የሚችለው ነው። አጠገባችሁ ያለች እናት ወይም ሕጻን ልጅ ከየት እንደመጡ እና ለምን እንደሚለምኑ ብትጠይቋቸው ከመጡበት አካባቢ ችግር ስለነበር ነው። ይህ ሲባል ወደ ብዙዎቻችን አዕምሮ የሚመጣው ምናልባትም የሰሜኑ ጦርነት ነው። ዳሩ ግን ልብ ያልተባሉ ብዙ የሰፈር ሽፍታዎች ሁሉ ማፈናቀል ጀምረዋል። ሰው እያገቱ ብር ያስልካሉ፤ በዚህ ምክንያት መገዳደል ይመጣል፤ በዚሁ ምክንያት ሰዎች ይሰደዳሉ። ይህ የሚሆነው ከሕጋዊ ውጭ ባሉ የመንደር ታጣቂዎች ነው። ለምን ዓላማ ሰው እንደሚገድሉ በማያውቁ ሽፍታዎች ነው። በዋናነት ግን የሰሜኑ ጦርነት ነው።
ሌላው የልመና ምክንያት ከማኅበራዊ ሕይወታችን የሚቀዳ ነው። ማኅበራዊ ሕይወታችን ብዙ አኩሪ እሴቶች እንዳሉት ሁሉ መቀረፍ ያለባቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም አሉበት። ለምሳሌ፤ ያለዕድሜ ጋብቻ እና ያለአቻ ጋብቻ የብዙዎችን ሕይወት አተረማምሰዋል። አንዲት ሴት ልጅ ያለዕድሜዋ ስትዳር ከአካላዊ ጉዳት ጀምሮ እስከ አዕምሯዊ ሕመም ትዳረጋለች። የዚች ልጅ ዕጣ ፋንታ የሚሆነው ጎዳና መውጣትና መለመን ነው።
በየመንገዱ ለልመና ከተዳረጉ እናቶች አብዛኞቹ ምናልባትም ተገደው ተደፍረው የወለዱ ናቸው። ያለአቻቸው በግዴታ ተድረው ግፍ ሲበዛባቸው ልመና ይሻላል ብለው ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ናቸው። የአካባቢያቸው ሕይወት ከልመና የከፋ ሆኖባቸው ሽሽት የመጡ ናቸው።
ከምንም በላይ የከፋ የሆነው ግን የሠላሙ ጉዳይ ነው። እኔ በማውቀው አካባቢ እንኳን ብዙ ሰዎች የተሰደዱት በመንደር ሽፍታዎች ነው። የመንደር ሽፍታ የቆመለት ዓላማ የለውም። ሰው ገድሎ ወይም ንብረት ዘርፎ ወይም አስገድዶ ደፍሮ ከሕግ ለማምለጥ ጫካ የገባ ነው። በእነዚህ ሽፍታዎች ምክንያት ብዙ ዜጎች እየተፈናቀሉ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለዝናብና ፀሐይ ተዳርገዋል። ወደ አዲስ አበባ መሸሽ ያልቻሉት ወይም የመጣው ይምጣ ብለው የተቀመጡት ከመንግሥት የሚፈልጉት ሠላምን እንዲያስከብርላቸው ነው።
ይህን አስከፊ የልመና መስፋፋት የምናስቀረው በመጀመሪያ ሠላም ሲሰፍን ነው። ሠላም የሚሰፍነው ደግሞ ሁላችንም ለሠላም ስንሠራ ነው። አንድ አካል ብቻ ሠላም እንዲያመጣ ከጠበቅን አይመጣም። ከመንግሥት በላይ ሠላምን ማምጣት የሚችለው ሕዝብ ነው። አንድ ጥሩ ምሳሌ ልጥቀስ!
የመንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ኅብረተሰቡ ገብተው ኅብረተሰቡን ወንጀለኞችን ጠቁሙ ሲባል አይጠቁሙም። እንዲያውም ወንጀለኛውን ለመደበቅ የሚተባበሩ ሁሉ አሉ። ይህ የሚሆነው አንዳንዶቹ በአድርባይነት፣ አንዳንዶቹ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ስለማይወስድ ለምን ከሽፍታው ጋር ቂም ውስጥ እገባለሁ በሚል በተስፋ መቁረጥ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባትም ከሽፍታው የሚያገኙት ጥቅም ስለሚኖር ነው። ይህ ሁሉ ጣጣ ስለሚኖር ሠላም ፈላጊዎች መንግሥትን መተባበር አለባቸው።
አለበለዚያ የትውልድ ክፍተት ይፈጠራል፤ ልመናም ሀገራችንን እያቃወሰ ነው። እነዚህ በየምግብ ቤቱ በር ላይ ያሉ ልጆች ትምህርት እየተማሩ አይደለም፤ ቀጣይ ሕይወታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ለማንም ቀላል ነው። ከዛሬ ምናምን ዓመታት በኋላ እነዚህ ልጆች ያልተማረ ዜጋ ነው የሚሆኑት። ከዛሬ ምናምን ዓመታት በኋላ ዓለም የት እንደምትደርስ ማሰብ ቀላል ነው። መጻፍና ማንበብ የማይችል ማኅበረሰብ የሚኖርባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች። ይህንን እያሰብን ነው መሥራት ያለብን።
በየአካባቢው ሠላም ከሰፈነ በኋላ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ይቻላል፤ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ይከፈታሉ። መሠረተ ልማቶች ሲሠሩ የዘመኑ ውጤት የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ ይሆናሉ። ያኔ የሰዎች አመለካከትም ዘመናዊ ይሆናል። ስለዚህ መንግሥትም ሕዝብም ለሠላም ይሥራ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም