በተንጣለለው የበጋ መስኖ ስዴ ማሳ መሐል ታዳጊዎች ከወዲህ ወዲህ ይሯሯጣሉ፤ ሩጫቸው ግን ለጨዋታ አይደለም፤ የግሪሳ ወፍን በማባረር ሥራ ተጠምደው እንጂ!። ይህን ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ የግሪሳ ወፍ ለመከላከል በማሳው የተለያዩ አካባቢዎች ለግሪሳው ማስፈራሪያ ሲባል የተተከለ ሰው መሳይ አካል /አሻንጉሊት/ እንዲቆም አድርጓል። ሌሎች ደግሞ ከኮባ ግንድ ደህና ተደርጎ የተገመደ አለንጋቸውን በሰማዩ ላይ ያወናጭፋሉ፤ ያሸከረክራሉ።
ባለሰቅጣጭ ድምፁ ግሪሳ ማንንም አልፈራም። እንዳሻው በቡድን ሆኖ ከአንዱ የስንዴ ማሳ ወደ ሌላኛው እየተመመ የስንዴ ዘለላ ቅንደባውን ተያይዞታል። ሕፃናትና ወጣቶችም ያለመታከት ሰብሉን ካሰፈሰፉት የግሪሳ ወፎች ለመታደግ ጥድፊያቸውን ቀጥለዋል።
ይሄ ከግሪሳ ጋር የሚደረገው ግብግብ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ጆሌ ሦስት ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ወጣት አርሶአደር ድንቁ ወረዳም ሆነ የሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች የሰሞኑ ውሎ ሆኗል። ወጣቱ አርሶ አደር እንደሚለው፤ ዘንድሮ የእሱና የአባቱ እንዲሁም የአጓራባች አርሶአደሮች ማሳ በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል። ምርቱ ደግሞ በእጅጉ የሚያጓጓና አበው የሚያጠግብ እንጀራ ከመሶቡ ያስታውቃል›› ይሉት አይነት ሆኖ ነው ያገኘው። ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ለአጨዳ እስከሚደርስበት ድረስ የእሱም ሆነ የመላ ቤተሰቡ እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች እንክብካቤ ያልተለየው በመሆኑም የስንዴው ዘለላ ውጤታማነቱን ከወዲሁ አረጋግጦለታል። ለዚህም ነው ከአጨዳ በፊት በግሪሳ ወፍም ሆነ በሌላ ነፍሳት ጉዳት እንዳይደርስበት እሱና ቤተሰቡ ሌት ተቀን እየታተሩ ያሉት።
ወጣቱ አርሶአደር በቀደሙት ዓመታት ቲማቲም፣ ሽንኩርትና መሰል የጓሮ አትክልቶችን ያለሙ እንደነበር ጠቅሶ፣ ዘንድሮ ግን በግብርና ባለሙያዎች ቀስቃሽነት በአምስት ሄክታር የአባቱ መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውስጥ መግባቱን ያስረዳል። ባለፈው ዓመት በአቅራቢያቸው የሚገኙ አርሶአደሮች ባልተጠበቀ ዝናብ ምክንያት የደረሰ ስንዴያቸው ተጎድቶባቸው እንደነበር አስታውሶ፣ በዚህ ምክንያት ዘንድሮ ስንዴ ለማልማት አንገራግሮ እንደነበር አይሸሽግም። ያም ሆኖ ባለሙያዎቹ ስንዴ ለራሱም ሆነ ለሃገር ያለውን ፋይዳ በሚገባ ስላስገነዘቡት በድፍረት ወደ ማልማት መግባቱን ያመለክታል።
‹‹ባለሙያዎቹ መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ፀረ-ተዋሕስያን መድኃኒቶች በፍጥነትና በምንፈልገው መጠን እንድናገኝ ስላገዙን ምርቱ ከጠበቅነው በላይ ውጤታማ ሆኖልናል›› የሚለው ወጣት ድንቁ፤ በሳምንት ሁለትና ሦስት ጊዜ ፀረ-ተባይ መድኃኒት ርጭት እንደሚካሄድ ተናግሯል። የአመራረት ሂደቱም በመካናይዜሽን የታገዘ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በኋላቀር አሠራር ምክንያት ያጋጥም የነበረው የምርት ብክነት ይኖራል ብሎ እንደማያምን ይገልጻል።
‹‹አሁን ላይ ሰብሉ ከጠበቅነው በላይ በሚያጓጓ ሁኔታ ደርሶልናል። በጥማድ 20 ኩንታል ሰንዴ ምርት እንጠብቃለን። የምናጭደውም በኮምባይነር ስለሆነ ብክነት ያጋጥመናል ብለን አናስብም›› ሲል ያስረዳል። ፈርተው ስንዴ ያላለሙ ግን ደግሞ የእነሱን ተሞክሮ ያዩ አርሶ አደሮች ቁጭት ውስጥ ገብተው ለቀጣይ ዓመት ስንዴ ለማልማት መነሳሳታቸውንም ነው የሚያስረዳው።
አቶ ጃቢር ጀማል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን የመስቃን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪና የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ወረዳው እንደወጣት ድንቁ ሁሉ በርካታ ወጣት አርሶአደሮችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው። በዋናነትም የአርሶአደሩንም ሆነ የሃገርን የኢኮኖሚ አቅም ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የግብርና ምርቶችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
‹‹በዋናነትም ከአራትና አምስት ዓመታት ወዲህ በሃገር አቀፍ ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የወረዳችን የመስኖ ልማት ሽፋን እየሰፋ ነው ያለው፤ የውሃ አማራጮች ባሉባቸው ቀበሌዎች ሁሉ አርሶአደሩ የመስኖ ልማትን ባሕል አድርጎ ይዟል፤ የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ እንደ በቆሎ፣ ሽንኩርት ቲማቲምና ሌሎች አዝርዕቶችን በስፋት በማልማት የገቢ አቅሙን እያሳደገ ይገኛል›› ሲሉ ያብራራሉ። ወረዳው በ2016 በጀት ዓመትም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ 331 ሄክታር እንዲሁም መደበኛ መስኖ ልማት 4 ሺ 620 ሄክታር መሬት ላይ የጓሮ አትክልት ለማልማት አቅዶ መሥራቱን ይጠቅሳሉ። በዚህ መሠረትም በአሁኑ ወቅት የእቅዱን 66 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያመለክታሉ።
‹‹ከበጋ ስንዴ አኳያ ሰፊውን ሽፋን የያዘው የክላስተር ሥራችን ነው፤ ይህም አርሶአደሩ ያለውን አነስተኛ መሬት በጋራ አቀናጅቶ በዘመናዊ መንገድ በማልማት፤ የሚያጋጥሙትንም ችግሮች በኅብረት በመፍታት ውጤታማ እንዲሆን እያደረገው ነው›› ሲሉም አቶ ጃቢር ያስረዳሉ። በመስቃን ወረዳ ጆሌ ሁለትና ሦስት ቀበሌ ውስጥ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በሌሎችም ቀበሌዎች ላይ ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ያብራራሉ።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በምሥራቅ ጉራጌ ዞንም ሆነ መስቃን ወረዳ የ2016 የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በይፋ የተጀመረው በእነ ድንቁ ማሳ ላይ ነው። የወረዳው ግብርና መምሪያ ለስንዴ ልማቱ ውጤታማነት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የሚያስፈልገውን የግብዓትም ሆነ የሙያ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። አሁን ያለው አያያዝን መነሻ በማድረግም በሄክታር 48 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በመደበኛ መስኖ በዘር ከተሸፈና ከ4 ሺ 600 ሄክታር ውስጥ የመጀመሪያ ዙሩ በ3ሺ 763 ሄክታር መሬት ላይ የለማውን ሰብል አዝመራ መሰብሰብ ተችሏል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ 850 ሄክታር ያህል የተሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም እስከ ግንቦት ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።
የመስኖ ልማቱ በወረዳው ከአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጭምር በር የከፈተበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ። ‹‹ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ አብዛኛው ወጣት ሥራ አጥ ነበር፤ የእርሻ መሬቱ ቢኖርም በግብርና ሙያ ላይ መተዳደር አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን ከሌሎች አርሶአደሮች ውጤቱን እያዩ በተለይ ያለንበት ቀበሌ ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃና የእርሻ መሬት ያለበት እንደመሆኑ መጠን ወጣት አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ ናቸው›› ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹በወረዳችን ከመደበኛ መስኖ ባሻገር በእዚሁ ቀበሌ 98 ሄክታር የስንዴ ማሳ አለን›› ሲሉም ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ሰፊ የሰው ኃይል በእርሻ ሥራ ላይ እንደመሆኑ በዚያው ልክ አካባቢውም ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያለበት መሆን መቻሉንም ጨምረው ያመለክታሉ። ቀበሌውም አጠቃላይ ሂደቱ ሲታይም መንግሥት ያስቀመጣቸውን እቅዶች በማሳካት ረገድ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀስ ይናገራሉ ።
እንደ አቶ ጃቢር ማብራሪያ፤ የስንዴ ልማት ከሌሎች የአትክልት ልማቶች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅም ነው። በገቢም ረገድ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሃገር ያለው ጠቀሜታ የላቀ ነው። ፖለቲካው ላይ ያለውን ትርጉም ታሳቢ በማድረግ ከአርሶአደሩ ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጎ መተማመን ላይ ተደርሷል። በመሆኑም በወረዳው ያለው አብዛኛው አርሶአደር አምኖበትና ፈቅዶ እያለማ በመሆኑ ውጤቱም አመርቂ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም አሁን ላይ በወረዳው ያሉትን የውሃ አማራጮች በሙሉ በመጠቀም በዓመት ሦስት ጊዜ የሚመረትበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ በ331 ሄክታር ውስጥ አንድ ሺ 31 አርሶአደሮች ይሳተፋሉ። ከዚህ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
‹‹በቀጣይ የምርት ዘመን ደግሞ ከ350 ሄክታር በላይ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። አሁን ላይ እንደወረዳ ያለንን አቅም አሳድገን ወደ ውጭ ለመላክም አቅደን እየሠራን ነው›› የሚሉት አቶ ጃቢር፤ አርሶአደሩ ካመረተው ምርት ቢያንስ 15 በመቶ የሚሆነውን ለመላክ መካናይዝ በሆነ መንገድ እየተሠራ መሆኑንም ያስረዳሉ። በተያዘው የምርት ዘመንም የሚሰበሰበው ምርት ከአካባቢው ገበያ ባለፈ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከእህል ተረካቢ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ። በአካባቢው ለሚገኙ ዱቄት ፋብሪካዎችና አግሮ ፕሮሰሲንግ ኩባንያዎች እንደሚቀርብም ነው የጠቀሱት።
በመስቃን ወረዳ እየለማ ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ላይ እያንዣበበ ያለውን የግሪሳ ወፍ ከመከላከል አኳያ እየተሠራ ስላለው ሥራ አቶ ጃቢር ተጠይቀው ‹‹ እስካሁን ባለው ሁኔታ የግሪሳ ወፉ በወረርሽኝ ደረጃ የሚጠቀስና ያን ያህልም ጉዳት ያመጣል ተብሎ የሚገመት አይደለም፤ ይሁንና አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች ተቀናጅተው የመከላከሉን ሥራ ሌት ተቀን እየሠሩ ነው›› በማለት ተናግረዋል። በሌላ በኩል አብዛኛው የስንዴ ማሳ ለአጨዳ መድረሱን ጠቅሶ፣ ቶሎ የመሰብሰብ ሥራ ስለሚከናወን ሰብሉ ጉዳት ይደርስበታል ተብሎ እንደማይታመን ነው ኃላፊው ያመለከቱት።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ በክልሉ ድህነትን ለመርታት የተጀመረውን ጉዞ ለማፋጠን ከሚያስችሉ ሥራዎች አንዱ ምቹ መሬት፣ የውሃ አማራጭ፣ የአየር ንብረት፣ በቂ አምራች ጉልበት እና ቴክኖሎጂ ነው። ከዚህ አንፃር የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ለግብርና ዘርፍ እምርታ እየተረባረበ ነው። በዋናነትም ዝግጁነት ያለው ታታሪው የክልሉ አርሶ አደር በጋውን ወደ ክረምት የቀየሩ በሚመስል መልኩ እየተጉ ይገኛሉ።
‹‹የትጋታቸውን ውጤትም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልት፣ በስራስር፣ በፍራፍሬ እና በሌማት ቱሩፋት ሥራችን እያፈሱ ይገኛሉ›› በማለትም አቶ ዑስማን ይጠቅሳሉ። በመስቃን ወረዳም ሆነ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የተገኘው ውጤት በማየት ሌሎች የክልሉ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ያሏቸውን ፀጋዎች በቁጭት ለመጠቀም መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ነው የሚያስረዱት።
እንደሃገርም የለውጡ መንግሥት በሃገሪቱ ያለውን ፀጋ ተገንዝቦ ወደ ልማት በመግባቱ ውጤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መታየት መቻሉን አቶ ዑስማን ያመለክታሉ። በዋናነትም የሃገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሲባል በየክልሉ እየተከናወኑ ባሉ የተቀናጀ ግብርና ሥራዎች ኢትዮጵያ ከውጭ እርዳታ ጠባቂነት ለማውጣት ተስፋ ሰጪ እምርታዎች እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ውጤት ተጠቃሽ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹የማይቻል ይመስል የነበረውን ስንዴን በበጋ መስኖ ማልማት እንደሚቻል በተግባር በማሳየት ውጤታማ መሆን ችለናል›› ሲሉም ጠቅሰዋል።
‹‹ በክልላችን የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነትና ውጤት የአምራቹን ተስፋ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ሳንጠቀም ያመለጠንን ጊዜም ጭምር በቁጭት በማሰብ የበለጠ ለመሥራት አነሳስቶናል›› የሚሉት አቶ ዑስማን ፤ በተለይም በተያዘውና በቀጣዩ የምርት ዘመን የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በእጥፍ በማሳደግ ክልሉ ከራሱ አልፎ ለሃገር ኢኮኖሚ እድገት ሁነኛ አቅም እንዲሆን ይሠራልም ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥም የግብርናውን ሥራ ማዘመን የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን ከመቀየስ፣ ግብቶችን በጊዜው በማቅረብ ረገድ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ። በተጓዳኝም መስቃን ወረዳ በተወሰነ ደረጃ የተስተዋለውን የግሪሳ ወፍ ከመከላከል አኳያ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት መቂና ሃዋሳ ላይ በሚገኙ ሄሊኮፕተሮች የመድኃኒት ርጭት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል። ይሁንና የተጠቀሱት ቦታዎች ርቀት ያላቸው መሆናቸውን በክልሉ ለእዚህ አገልግሎት የሚውል የሄሊኮፕተር ማረፊያ እንዲዘጋጅ የክልሉ መንግሥት ከግብርና ሚስቴር ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ነው አቶ ዑስማን አስታውቀዋል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም